2020.04.20 coppia matrimonio 3 2020.04.20 coppia matrimonio 3 

ባለ ትዳሮች፣ በቤተሰብ ሐዋርያዊ አገልግሎት በኩል እንክብካቤ ሊደረግላቸው ይገባል ተባለ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የጎርጎሮሳዊያኑ 2021 ዓ. ም. የቤተሰብ ዓመት እንዲሆን ማሳሰባቸው ይታወሳል። ከዚህም ጋር በተያያዘ በምስጢረ ተክሊል እና በጋብቻ ሕይወት መካከል ያለውን ግንኙነት ይበልጥ ለመረዳት እንዲያግዘን “የፍቅር ሐሴት” የሚለው የቅዱስነታቸውን ሐዋርያዊ መልዕክት በድጋሚ መመልከት እንደሚያስፈልግ በጣሊያን የአንኮና-ኦሲሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ካርዲናል ኤዱዋርዶ መኒኬሊ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“የፍቅር ሐሴት” በሚል አርዕስት ይፋ የሆነው የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ አምስተኛ ዓመቱን የሚያስቆጥረው በመጋቢት 10/2013 ዓ. ም. ሲሆን፣ በጎርጎሮሳዊያኑ 2021 ዓ. ም. የተጀመረው የቤተሰብ ዓመት የሚገባደደው በጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ሰኔ 26/2022 ዓ. ም. በሮም ሊከበር በታቀደው በአሥረኛው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ በዓል መሆኑ ታውቋል።

በጣሊያን የአንኮና-ኦሲሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ኤዱዋርዶ መኒኬሊ እንደገለጹት ከዚህ በፊት በቤተሰብ ጉዳይ ላይ ሁለት የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ፣ እንደ ጎርጎሮስዊያኑ የቀን አቆጣጠር በ2014 እና በ2015 ዓ. ም. መካሄዳቸውን አስታውሰዋል። የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ ለቤተክርስቲያን ትልቅ መባረክ መሆኑን የገለጹት ካርዲናል ኤዱዋርዶ፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለቤተሰብ የሚሰጡት ትኩረት ከፍተኛ መሆኑን እና ቤተክርስቲያንም ከቤተሰብ የምታገኘው አክብሮት እንደዚሁ ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል። “የፍቅር ሐሴት” እና “የቤተሰብ ማኅበር” በሚል አርዕስት ይፋ የሆኑት የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እና የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ሐዋርያዊ መልዕክቶች ከሌሎች ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳት መልዕክቶች ጋር ለቤተሰብ የሚሰጡት ልዩ ክብር ምዕመናን ለቤተሰብ አስፈላጊውን አገልግሎት እና እንክብካቤን እንድናበረክትለት የሚጋብዙን መሆኑን ካርዲናል ኤዱዋርዶ አስረድተዋል።

“የፍቅር ሐሴት” በሚል አርዕስት የሚታወቀው የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ በስምንተኛው ምዕራፍ ላይ የተጠቀሰው ሃሳብ ከፍቺ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ጋብቻን የሚፈጽሙትን የሚመለከት ቢሆንም የእምነታችንን እውነት መሠረት በማድረግ የምሕረት እና የእውነት አገልጋዮች በመሆን ሐዋርያዊ የቤተክርስቲያን ምስጢራትን ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ ጋር በማዛመድ በስፋት እንድንመልከተው የሚጋብዘን መሆኑን ካርዲናል ኤዱዋርዶ መኒኬሊ አክለው አስረድተዋል።

የቤተሰብ ሐዋርያዊ አገልግሎት ሰፊ እና ብዙ ሥራን የሚጠይቅ፣ ውጤቱም በአጭር ጊዜ የሚታይ አለመሆኑን የገለጹት ካርዲናል ኤዱዋርዶ፣ ሰፊ ሐዋርያዊ የአገልግሎት ዘርፍ ያለው በመሆኑ ትምህርታዊ፣ ሥነ-ምግባራዊ፣ ማኅበራዊ እና የአስተማሪነት ይዘት ያለው መሆኑን አስረድተዋል። ምንም እንኳን ረጅም ጊዜ የወሰደ ቢሆንም በቂ ግንዛቤን ለመጨበጥ የሚያስችል የቅዱሳት ምስጢራት ጸጋ፣ ምስጢረ ጥምቀት እና ምስጢረ ተክሊል ለሚቀበሉት፣ በሕይወታቸው ውስጥ በተግባር ለሚኖሩት ጸጋን እንደሚያጎናጽፋቸው ገልጸው፣ በእነዚህ ሁለቱ ምስጢራት ላይ መሠረቱን ያደረገው ቤተሰብ ከቅዱስ ቁርባን በሚያገኘው ጸጋ ሕይወትን ያገኛል ብለዋል።

በምስጢረ ተክሊል እና በጋብቻ ሕይወት መካከል ያለው ግንኙነት በብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ በስፋት ውይይት የተደረገበት መሆኑን ብጹዕ ካርዲናል ኤዱዋርዶ ገልጸው፣ ሁለቱም ለቤተክርስቲያን ዕድገት ሐዋርያዊ አገልግሎት የሚሰጥባቸው ምስጢራት መሆናቸውን አስረድተዋል። “የፍቅር ሐሴት” የሚለው የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ መልዕክትን በድጋሚ በመመልከት አዲስ ጉዞን መጀመር እንደሚያስፈልግ አሳስበው፣ ለቤተሰብ የሚቀርብ ሐዋርያዊ አገልግሎት በክርስቲያን ማኅበረሰብ ዘንድ በተግባር የሚከናወን በመሆኑ መላው የክርስቲያን ማኅበረስብ እንደሚሳተፍበት ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። 

05 January 2021, 09:51