የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ቁጥጥር እና የሙቀት መጠን ልክ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ቁጥጥር እና የሙቀት መጠን ልክ 

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት ወደ አፍሪካ ሳይዘገይ ይደርስ ይሆን?

አውሮፓ እና አሜሪካ ለሕዝቦቻቸው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት ለማዳረስ በቁርጠኝነት እየሠሩ መሆኑ ስታወቅ፣ አፍሪካም በጎርጎሮሳዊያኑ 2021 ዓ. ም. አጋማሽ ላይ ከፍተኛ መጠን ያለውን ክትባት እንድምትቀበል ይጠበቃል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተደጋጋሚ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት ወደ ሁሉም ዘንድ እንዲደርስ ሲያሳስቡ መቆየታቸው ይታወቃል። በቅርቡ ተከብሮ ባለፈው የአውሮፓዊያኑ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓልን በማስመልከት ለሮም ከተማ እና ለመላው ዓለም ባስተላለፉት የመልካም ምኞት መግለጫ መልክታቸው፣ በዚህ ጨለማ እና ፍርሃት በነገሠበት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት፣ መድኃኒቱ መገኘቱን የሚያበስር የተስፋ ብርሃን መታየቱን ገልጸው፣ ነገር ግን ይህ የተስፋ ብርሃን ለሁሉም እንዲበራ እና መከላከያ ክትባቱ ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን ያስፈልጋል ብለዋል።

ለመሆኑ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት ወደ አፍሪካ አህጉር እንዲደርስ እየተደረገ ያለው ጥረት እና ተስፋ ምን ያህል ነው? በቫቲካን ምክር ቤት የአፍሪካ ኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ስርጭት ግብረ ኃይል አስተባባሪ፣ እንዲሁም በአፍሪካ የኢየሱሳዊያን ማኅበር ከፍተኛ ጉባኤ የሚመራ የፍትሕ እና የሥነ-ምሕዳር ዳይሬክተር የሆኑት ክቡር አባ ሻርል ቺሉፊያ፣ በአፍሪካ ውስጥ የሚታዩትን ውስብስብ ችግሮች በማስመልከት ከቫቲካን ዜና ገልግሎት ጋር ቃለ ምልልስ አድርገው ነበር።

አባ ሻርል ቺሉፊያ እንዳስረዱት፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ክትባት በአፍሪካ ውስጥ በስኬታማነት ማዳረስ እንዲቻል በቅድሚያ ከአገር ውስጥ እና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር መፍታት የሚገቡ በርካታ ርዕሠ ጉዳዮች መኖራቸውን አስረድተዋል። የመጀመሪያው የክትባቱን ስርጭት የሚመለከት ስሆን፣ ሃብታም አገሮች ከወዲሁ በማደግ ላይ ያሉ ድሃ አገሮችን በመቆጣጠር ላይ ይገኛሉ። ሁለተኛው ባሁኑ ጊዜ ተገኘ የተባለው ክትባት የባለ ቤትነት ሕጋዊ መብት መድኃኒቱን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማቅረብ ካለው ፍላጎት ጋር ይጋጫል። በሦስተኛ ደረጃ ዓለም አቀፍ ትብብርን የሚጠይቅ ሲሆን፣ የዓለም የጤና ድርጅት ክትባቱን በመላው ዓለም ማድረስ የሚቻልበትን ዓለም አቀፍ ትብብር ማስተባበር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። እንቅፋትን የሚፈጥሩ ቢሮክራሲያዊ አካሄዶች መኖራቸውን የገለጹት አባ ሻርል ቺሉፊያ፣ ቢሆንም የጤና እንክብካቤን ማግኘት የእያንዳንዱ ሰው መብት እና በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌ፣ በአንቀጽ 25 ላይ መጠቀሱን ገልጸው፣ ይህም ለጥቂት ሰዎች ብቻ የሚቀርብ ምርጫ ሳይሆን ሁሉም ሰው ማግኘት ያለበት ግዴታ ነው ብለዋል። ቢሮክራሲያዊ እንቅፋቶች ቢኖሩም በዓለም አቀፍ ውይይቶች ሊፈቱ እንደሚችሉ ገልጸው፣ የክትባቱ ዋጋ መሻቀቡ ከታካሚው የገንዘብ አቅም ጋር የማይመጣጠን ቢሆንም በዓለም አቀፍ ስምምነት መሠረት ለሁሉም እንዲዳረስ ማድረግ ይቻላል ብለዋል።  

አማራጮችን መስጠት

በዓለም ንግድ ድርጅት የሚጸድቁ ስምምነቶችን ማድረግ ይቻላል ያሉት አባ ሻርል ቺሉፊያ፣ ከንግድ ጋር የተያያዙ አዕምሯዊ ንብረት መብቶች መኖራቸውን አስታውሰው፣ ፈቃድ የመስጠት ብቃት ያለው የመንግሥት ባለሥልጣን የባለቤትነት መብቱን ለሶስተኛ ወገን ወይም ለመንግሥት ወኪል ፈቃድ እንዲሰጥ ያስችለዋል ብለዋል፡፡ ስለዚህ መንግሥታት ብዙውን ጊዜ አማራጭ መድኃኒት ተብሎ የሚጠራውን ለሕይወት ተስማሚ እና ርካሽ የሆነ የመድኃኒት ስሪቶች ፈቃድ ማውጣት ይችላሉ ብለው በርካታ የአፍሪካ አገሮችም ይህን የመድኃኒት ማምረቻ መንገድን የሚከተሉ መሆኑን አስረድተዋል። የአፍሪቃ አገሮች መድኃኒት የማምረት ፍቃድ ቢያገኙም በቂ የማምረቻ መሣሪያዎች አቅርቦት እና የተመቻቸ ስፍራ ላይኖራቸው እንደሚችል ገልጸው፣ እነዚህ አገሮች እ.አ.አ 2001 ዓ. ም. በዶሃ በተደረሰው ስምምነት መሠረት ከመድኃኒት አምራች አገሮች ማስገባት ይችላሉ ብለዋል።

ኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመግታት በአገሮች ዘንድ ትብብር ሊኖር ይገባል

የሕዝብ ጤናን በዓለም አቀፍ ደረጃ መጠበቅ እንዲቻል አገሮች ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባ የጠቆሙት   አባ ሻርል ቺሉፊያ፣ ወረርሽኙን በአፍሪካ ውስጥ መቆጣጠር ካልተቻለ ሌላውም የዓለማችን ክፍሎች ተመልሰው ሊጠቁ ይችላሉ ብለው፣ እንደሚታወቀው ችግሩ የአንድ አገር ችግር ብቻ ሳይሆን የመላውን ዓለም ሕዝብ የጤና ችግርን የሚነካ ነው ብለዋል። በመሆኑም ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በመካከላቸው ኅብረትን በመፍጠር የግል ጥቅማቸውን ከማስቀደም ይልቅ ለጋራ ጥቅም ቅድሚያን ሰጥተው ወረርሽኙን ከምድር ገጽ ለማስወገድ እንዲጥሩ፣ ይህም ወደ ፊት በዓለም የጤና እንክብካቤ ላይ መልካም ኅብረት እንዲፈጠር ያግዛል ብለዋል።    

05 January 2021, 16:55