ኢየሱስ ከተወለደ ከስምንት ቀን በኋላ ወላጆቹ የሙሴን ሥርዓት ለመፈጸም እና የግርዘት ስርዓት ለማስፈጸም ኢየሱስን ይዘውት ወደ ቤተመቅደስ ሄዱ ኢየሱስ ከተወለደ ከስምንት ቀን በኋላ ወላጆቹ የሙሴን ሥርዓት ለመፈጸም እና የግርዘት ስርዓት ለማስፈጸም ኢየሱስን ይዘውት ወደ ቤተመቅደስ ሄዱ 

ከኢየሱስ ግርዛት ምን እንማራለን?

ዛሬ ጥር 6/2013 ዓ.ም ሲሆን ይህም ኢየሱስ ኢየሱስ ከተወለደ ከስምንት ቀን በኋላ ወላጆቹ የሙሴን ሥርዓት ለመፈጸም እና የግርዘት ስርዓት ለማስፈጸም ኢየሱስን ይዘውት ወደ ቤተመቅደስ ሄዱ፡፡ ከተወለደ ስምንት ቀን ካለፈው በኋላ ስሙ “ኢየሱስ” ተስሎ ተጠራ፡፡ ይህ እርሱ ገና ሳይጸነስ በፊት መልአኩ የሰጠውና ያወጣለት ስም ነው (ሉቃ. 2፣21)።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ዕብራውያን እግዚአብሔር  ሕዝብ እንደመሆናቸውና ከሌሎች የዓለም ሕዝቦች እንዲለያቸው ብሎ ምልእክት ይሆነው ዘንድ ግርዛትን ሰጣቸው፡፡ እንግዲህ በግርዛት ሕዝቡ መሆናቸውን አሳወቃቸው፡፡ በመጽሐፈ ሌዋውያን ውስጥ በሙሴ በአገልጋዩ በኩል እንደተጻፈው “ሕፃን በስምንተኛው ቀን እንዲገረዝ ይሁን” (ዘሌዋዊያን 12፡3) ሲል አዘዛቸው፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ “አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) በፍጹም ልብህና በፍጹም ነፍስህ እንድትወደው፣ በሕይወትም እንድትኖር፣ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የአንተንና የዘርህን ልብ ይገርዛል” (ዘዳግም 30፡6) አላቸው፡፡ እንዲሁም “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በልቡና በሥጋው ያልተገረዘ ባዕድ በእስራኤላውያን መካከል የሚኖር ቢሆንም እንኳ ወደ መቅደሴ አይግባ” (ሕዝ. 44፣9) በማለት ለእዝቄል ይናገራል።

ግርዛት ለእስራኤላውያን ከትልልቅ ሥርዓቶች አንዱ ነበር፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶሰ ምንም እንኳ ግርዛት የማያስፈልገው ቢሆንም ሕግን ለመፈጸመ እንደ ሙሴ ሕግ የግርዛት ሥርዓትን እንደ ማንኛውም ተራ ሕፃን ፈጸመ፡፡ “ሰው ሆነ ያለኃጢአት የሰውን ሥራ ሁሉ ፈጸመ” ጊዜው ሲደርስ እግዚአብሔር ከሴት የሚወለድ በሕግም የሚሄድ ልጁን ላከው፡፡ የኢየሱስ ግርዛት ሁለት ነገሮችን ያስተምሩናል፡፡

1.     ሕግን ማክበር እንደሚገባን

ኢየሱስ የብሉይ ኪዳንን ሕግ ለመሻር በደንብ ይችል ነበር ነገር ግን አልፈለገም፤ አከበረው እንጂ አልናቀውም፤ ከዚህ የቃል ኪዳን ሕግ አልወጣም፡፡ የማይመለከተኝ ቢሆንም ለአዳም ልጆች ምሳሌና ትምህርት እንዲሆን ልፈጽመው አለና ፈጸመው፡፡ “ሕግንና የነቢያትን ቃል ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ለመፈጸም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም” (ማቴ. 5፡17) በማለት ኢየሱስ ተናግሯል። እርሱ አምላክ እና ከሕግ በላይም ሆኖ እያለ ሁሉን ሕግ ለመፈጸሙ ለእኛ የሕግን አክብሮት ምሳሌ ይሰጠናል፡፡ እኛ ብዙ ጊዜ በቀላሉ ደጋግመን ሕግን እንጥሳለን እናፈርሳለን፡፡ ይህ ሕግ ይህ ሥርዓት የድሮ በመሆኑ ጊዜ ያለፈበት ነው፣ ጥሩ አይደለም፣ አይጠቅምም የማይረባ ስለሆነ ብናፈርሰውና ብንጥሰው ምንም ጉዳት አያመጣም፣ የሚያሰጋ አይደለም በሚል ደካማ መንፈስ ንቀን እንረግጠዋለን፡፡ ባለን አቅም ተግባራዊ እንዳናደርገው ምክንያት በመፍጠር እንሸሻለን፡፡ በደኀንነትና በፍጽምና ጐዳና ወደፊት እንዳንገሰግስ የሚያግደንን አደገኛ የሆነውን ስንፍና ማስወገድ ከፈለግን ኢየሱስን አተኩረን አንመልከት እንከተለውም፡፡

2.     መንፈሳዊ ግርዛት ማለት ከኃጢአት መንጻት እንደሚገባን

መንፈሳዊ ግርዛት የሥጋ ግርዘትን መንፈሳዊነት ማመልከት አለበት፡፡ እግዚአብሔር ዕብራውያን ከሥጋ ግርዘት ጋር የመንፈስ ግርዘት እንደሚያስፈልጋቸው ያስጠነቅቃቸው ነበር፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን በተመለከተ ሲናገር “ግዝረትም ግዝረት የሚሆነው በተጻፈው ሕግ ሳይሆን፣ በመንፈስ የልብ ግዝረት ሲኖር ነው። እንዲህ ያለው ሰው ምስጋናው ከሰው ሳይሆን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው” (ሮሜ 2፡29) በማለት ይናገራል። እግዚብሔር የሕዝቡን ልብ ከኃጢአት ሊገርዝ ሊጠራ ይፈልግ ነበር፤ የልብ ግርዘት የእግዚአብሔር ያልሆኑ ነገሮችን ማስወገድ ነው።

ቅዱስ ሐዋርያው ጳዎሎስ አክሎም ሲገልጽ “እናንተም የገዥነትና የሥልጣን ሁሉ ራስ በሆነው በክርስቶስ ሙሉ ሆናችኋል። በእርሱ ሆናችሁ በእጅ ባልተደረገ መገረዝ ተገረዛችሁ፤ በክርስቶስም መገረዝ የሥጋን ኀጢአታዊ ባሕርይ አስወገዳችሁ፤ በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችሁ፣ እርሱን ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር ኀይል በማመን ከእርሱ ጋር ደግሞ ተነሣችሁ” (ቆላስይስ 2፡10 13) በማለት ይናገራል።

ቅዱስ አውጉስጢኖስም ደግሞ “ወንድሞቼ ሆይ! እኛ ደኀንነትን ብንፈልግ መገረዝ ያስፈልገናል፡፡ መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ ብንፈልግ ሥጋችንን መቅጣት ያስፈልገናል” እያለ ይመክረናል፡፡

በመንፈስ ሳንገረዝ ለእግዚአብሔር ብቁዎች ለመሆን አንችልም፡፡ አስራኤላውያን በግርዘት የእግዚብሔር የተመረጠ ሕዝብ ሆኑ፤ ለእርሱ ተሰጡ፡፡ እኛ ከኃጢአት ከተገረዝን ለእግዚብሔር ብቁዎች እንሆናለን፡፡ ልባችን ከክፉ ሐሳብና ምኞት ከነጻ በኋላ በጸጋ ያጌጠ ማኀደረ ስለሚሆን እርሱ በእዚህ ዓይነቱ ስፍራ ተደስቶ ያርፋል፡፡ መንፈሳችን ከዓለም በተገረዘ የእግዚብሔር መንፈስ ይሞላልና ሕይወታችን ከፈቃዱ ተስማምቶና ተግባብቶ ይሄዳል፡፡

14 January 2021, 15:17