በሶርያ ውስጥ በጦርነት ምክንያት የወደመች ቤተክርስቲያን በሶርያ ውስጥ በጦርነት ምክንያት የወደመች ቤተክርስቲያን 

በስደት እና በመከራ ውስጥ የሚገኙ 340 ሚሊዮን ክርስቲያኖች የጸሎት እገዛን በመጠየቅ ላይ ናቸው ተባለ

“ኦፐን ዶር” የተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በዓመታዊ ሪፖርቱ በዓለም ዙሪያ በክርስቲያኖች ላይ የሚፈጸም ግፍ እና ስቃይ እየጨመረ መምጣቱን አስታወቀ። ድርጅቱ በክርስቲያኖች ላይ የሚደርሰውን ስቃይ የሚያሳይ የፎቶ ግራፍ ምስል ለጣሊያን የተወካዮች ምክር ቤት አሳይቷል። ድርጅቱ በሪፖርቱ እንዳስታወቀው ባለፈው የጎርጎሮሳዊያኑ 2020 ዓ. ም ብቻ በእምነታቸው ምክንያት የተገደሉ ክርስቲያኖች ቁጥር 4,761 መሆኑን አስታውቆ፣ በሃይማኖት ነፃነት ላይ የሚጣሉ ገደቦችም እየጨመሩ መሆኑን አስታውቋል። በመሆኑም ክርስቲያኖች የጸሎት እርዳታን እና ለዓለም አቀፉ ዲፕሎማሲያዊ ማኅበረሰብ መማጸናቸውን የድርጅቱ ዳይሬክተር አቶ ናኒ አስታውቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በዓለማችን ውስጥ ከባድ መከራ እና ስቃይ የሚደርስባቸው ክርስቲያኖች ቁጥር ከ340 ሚሊዮን በላይ መድረሱ ሲነገር፣ ከእነዚህ መካከል ከስምንቱ ውስጥ በአንዱ ከፍተኛ አድልዎ እና ስቃይ እንደሚደርስበት ታውቋል። በተለይ በ50 አገሮች ውስጥ በሚገኙ 309 ሚሊዮን ክርስቲያኖች ላይ የሚደርስ ስቃይ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ዓለም አቀፍ ታዛቢ ቡድን በጎርጎሮሳዊያኑ 2021 ዓ. ም. ይፋ ባደረገው ዝርዝሩ አስታውቋል።

የወረርሽኙ አውድ

“ኦፐን ዶር” የተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ሰራተኞች በጋራ ባቀረቡት ጥናታዊ ሪፖርት፣ በዓለማችን በመቶ አገሮች ውስጥ በሚገኙ ክርስቲያኖች ላይ የሚደርስ መከራ እና ስደት እየከፋ መሆኑን እና በተለይም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ረዳት የሌላቸው አቅመ ደካማ የሆኑ ክርስቲያኖችን ለስቃይ የተጋለጡ መሆናቸው ታውቋል። በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በሃይማኖት ነፃነት ላይ ገደቦች እንዲጣሉ፣ አክራሪ እና ወንጀለኛ ቡድኖችን እንዲፈጠሩ ምክንያት መሆኑ ታውቋል።

የክርስቲያኖች ግድያ እየጨመረ መጥቷል

የድርጅቱ ዓመታዊ ሪፖርት በግልጽ እንዳስታወቀው ፀረ-ክርስትና አቋም እና በክርስቲያኖች ላይ የሚደርስ ስደት እጅግ እያደገ መሆኑን ገልጾ፣ እ.አ.አ 2020 ዓ. ም. የተገደሉት ክርሲያኖች ቁጥር 4,761 መድረሱን እና ይህም በቀን የሚገደሉት ክርስቲያኖች ቁጥር በአማካይ 13 መሆኑን አስታውቋል። በርካታ ክርስቲያኖች ከሚገደሉባቸው አሥር ከሰሃራ በታች ያሉ አገሮችን ጨምሮ ናይጄሪያ ብዙ ክርስቲያኖች የሚገደሉባት አገር መሆኗን ሪፖርቱ ገልጿል። ያለ ማስረጃ ተይዘው ወደ እስር ቤት የሚገቡ የክርሲያኖች ቁጥር 4,277፣ ታፍነው የሚወሰዱት 1,710 ሲሆኑ ያለ ምክንያት የሚዘጉ ቤተክርስቲያኖች ቁጥር፣ ጥቃት እና ውድመት የሚደርስባቸው የቤተክርስቲያን ንብረት የሆኑ ትምህርት ቤቶች እና ሆስፒታሎች ቁጥር ባለፈው ዓመት 9,488 የነበረው ዘንድሮ ወደ 4,488 መቀነሱ ታውቋል። 

በክርስቲያኖች ላይ ስደት የሚካሄድባቸው ቦታዎች

በክርስቲያኖች ላይ ከፍተኛ ሰደትን በማድረስ የሚታወቁ አገሮች ቁርጥር አድጎ ወደ 12 መድረሱን የገለጸው ሪፖርቱ ከእነዚህ አገሮች መካከል እስካሁን የመጀመሪያ ደረጃን ይዞ የቆየው ሰሜን ኮሪያ፣ ቀጥለውም አፍጋኒስታን፣ ሶማሊያ፣ ሊቢያ እና ፓክስታን መሆናቸውን ሪፖርቱ አስታውቆ በእነዚህ አገራት ውስጥ ፀረ-ክርስትና ተግባራት፣ አመጽ እና በክርስቲያኖች ዕለታዊ ሕይወት ውስጥ መድልዎ እንደሚደረግባቸው ታውቋል። የኮቪድ-19 ወረርሽኝም በበኩሉ በክርስቲያኖች ላይ የሚታዩ የፖለቲካ፣ የርዕዮተ ዓለም፣ የዘር፣ የሐይማኖት እና የብሔር ልዩነቶችን በማጉላት በዓለማችን ውስጥ በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ክርስቲያኖች ላይ የሚፈጸሙ ማኅበራዊ፣ ኤኮኖሚያዊ እና የዘር ልዩነቶችን ገሃድ አድርጎታል።

የቤት ውስጥ አመጽ እየጨመረ መጥቷል

“ኦፐን ዶር” የተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ዓመታዊ ሪፖርት በማከልም የቤት ውስጥ አመጽ በከፍተኛ ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ገልጾ፣ ሐይማኖታቸውን ወደ ክርስትና የለወጡት ሰዎች በቤት ውስጥ ተዘግተው እንዲቀመጡ መገደዳቸውን ሪፖርቱ ገልጿል። በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ክርስቲያኖች ሥራ፣ ትምህርት እና ከቤት ወጥተው የሚያከናውኗቸው ዕለታዊ ተግባራት፣ ከቤት ውስጥ ጥቃት እንዲሁም ከአካላዊ ፣ ከስሜታዊ ፣ ከቃል እና ከስነልቦናዊ ጥቃት ነጻ በማውጣት እፎይታን እንደሚሰጣቸው መታየቱን ሪፖርቱ አስረድቷል።

ክርስቲያኖች በብዙ አገሮች ውስጥ በመጨረሻ ደረጃ እንዲታዩ ይደረጋል

በቁጥር አነስተኛ የሆኑ ክርስቲያኖች በሚገኙባቸው አገሮች ውስጥ የነበረውን መድልዎ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጉልህ ማድረጉን፣ በጣሊያን የ “ኦፐን ዶር” ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ክርስቲያን ናኒ ለቫቲካን ዜና እንደገለጹት በሕንድ፣ ሚያንማር እና ባንግላዴሽ በነሳሰሉት አገሮች ውስጥ የሕክምናም ሆነ ሌሎች የዕርዳታ አገልግሎቶችን በማከፋፈል ሂደት ላይ ክርስቲያኖች የመጨረሻ ዕድል ተጠቃሚዎች እንደሚሆኑ ገልጸዋል። የክርስትና ሕይወት ከእምነት ጋር ያለውን የጠበቀ ግንኙነት የሚመለከት መሆኑን ያስታወሱት አቶ ክርስቲያን ናኒ፣ ቤተሰብም ቢሆን በውስጡ ያለውን እምነት እንዴት እንደሚኖር፣ ከዚያም ማህበራዊ ሕይወትን እና በሥራ ዓለም ያለውን ግንኙነት እና ብሔራዊ አንድነት እያከበሩ ቢኖሩም በክርስቲያን ማህበረሰብ እና በሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎቻቸው ላይ እገዳን በማድረግ ስቃይ ሲደርስባቸው ይታያል ብለዋል።

በግልጽ የሚታዩ አዝማሚያዎች

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ካስከተለው ቀውስ በተጨማሪ በጎርጎሮሳዊያኑ 2020 ዓ. ም. የታዩ አንዳንድ አዝማሚያዎች መኖራቸውን የገለጹት የ “ኦፐን ዶር” ዳይሬክተር አቶ ክርስቲያን ናኒ፣ በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ አመጽን የሚቀሰቅሱ እስላማዊ ሚሊሻዎች ቁጥር ማደጉ፣ ለምሳሌ ቱርክ እና ሕንድን በመሳሰሉ አምባገነናዊ መንግሥታት በክርስቲያን ማኅበረሰብ ላይ ያላቸው አስተያየት እና የሚያደርጉት ቁጥጥር እየጠበቀ መምጣትን ገልጸዋል።

ክርስቲያኖች የህብረተሰቡ አለኝታ ናቸው

የ “ኦፐን ዶር” ዳይሬክተር፣ ክቡር አቶ ክርስቲያን ናኒ፣ በዓለም ዙሪያ ስደት እና መከራ የሚደርስባቸው ክርስቲያኖች ሳይዘነጉ የጸሎት እርዳታን እና የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እገዛን እየተመጽኑ መሆናችውን ገልጸው፣ በአገራት መካከል ባለው ግንኙነት በኩል የሐይማኖት ነጻነት እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል። በመጨረሻም ሐይማኖት በአንድ በኩል ለስደት እና ለመከራ ተጋላጭ ቢያደርግም በሌላ ወገን ጥላቻ እና አመጽ የሚወገድበት መንገድ፣ አብያተ ክርስቲያናት እና አገልጋዮቻቸው የኅብረተሰቡ አለኝታ በመሆን ተስፋን እና መረጋጋትን በማምጣት ቁልፍ ሚናን መጫወት የሚችሉ መሆናቸውን የ “ኦፐን ዶር” ዳይሬክተር፣ ክቡር አቶ ክርስቲያን ናኒ አስረድተዋል። 

14 January 2021, 13:46