የታኅሣሥ 4/2013 ዓ.ም ሰንበት /ዘአስተምሕሮ 5ኛ/ ዕለተ ስንበት አስተንትኖ የታኅሣሥ 4/2013 ዓ.ም ሰንበት /ዘአስተምሕሮ 5ኛ/ ዕለተ ስንበት አስተንትኖ 

የታኅሣሥ 4/2013 ዓ.ም ሰንበት /ዘአስተምሕሮ 5ኛ/ ዕለተ ስንበት አስተንትኖ

“የሕይወት ጨለማን ለማብራት ይቻለን ዘንድ የእምነትን መብራት ማብራት ይኖርብናል!”

የእለቱ ምንባባት

1.     1ቆሮ 15፡12-32

2.     2ጴጥ 3፡10-18

3.     ሐዋ 20፡28-38

4.    ሉቃስ 12፡ 32-40

የእለቱ ቅዱስ ወዱስ ወንጌል

እናንተ አነስተኛ መንጋ የሆናችሁ መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ መልካም ፈቃድ ነውና አትፍሩ፤ ያላችሁን ሽጡና ለድኾች ስጡ፤ ሌባ በማይሰርቅበት፣ ብል በማይበላበት፣ በማያረጅ ከረጢት የማያልቅ ንብረት በሰማይ አከማቹ፤ ልባችሁ፣ ንብረታችሁ ባለበት ቦታ ይሆናልና።

ነቅቶ መጠበቅ

“በአጭር ታጥቃችሁ ተዘጋጁ፤ መብራታችሁም የበራ ይሁን፤ ጌታቸው ከሰርግ ግብዣ እስኪመለስ እንደሚጠባበቁና መጥቶም በር ሲያንኳኳ ወዲያው ለመክፈት ዝግጁ የሆኑ ሰዎችም ምሰሉ። ጌታቸው በሚመጣበት ጊዜ ነቅተው የሚያገኛቸው አገልጋዮች ብፁዓን ናቸው፤ እውነት እላችኋለሁ፤ ጌታቸውም በአጭር ይታጠቃል፤ በማእድ ያስቀምጣቸዋል፤ ቀርቦም ያስተናግዳቸዋል። ከሌሊቱ በሁለተኛውም ሆነ በሦስተኛው ክፍል መጥቶ እንደዚያው ነቅተው ቢያገኛቸው፣ እነዚያ አገልጋዮች ብፁዓን ናቸው። ይህን ግን ዕወቁ፤ ሌባ በምን ሰዓት እንደሚመጣ የቤቱ ባለቤት ቢያውቅ ኖሮ፣ ቤቱ ሲቈፈር ዝም ብሎ ባላየ ነበር። እናንተም ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ፤ የሰው ልጅ ባላሰባችሁት ሰዓት ይመጣልና።”

የእለቱ አስተንትኖ

በክርስቶስ የተወደዳችሁ የግዚአብሔር ቤተሰቦች እና በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

የዛሬው ንባባት ጠቅለል ባለ መልኩ ስንመለከተው አንድ ወጥ በሆነ ሐሳብ ላይ ያተነጥናሉ ይህም ሰው ከሞተ በኋላ ምን ይሆናል? የሚለው ነው። ይህ ሞት የምንለውስ ነገር በምን መልኩ እንረዳዋለን? ይህ ሞት የምንለውን ነገር በምን መልኩ እንጠብቀዋለን የሚሉትን ሐሳብ ያካትታል። በመጀመሪያው ንባብ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ አንዳንድ የቆሮንጦስ ሰዎች “ከሞት በኋላ ሕይወት የለም” ብለው እንደሚያምኑ ይጠቅሳል። ይህ አመለካከት በአብዛኛው የግሪክ ፍልስፍና ይከተሉ በነበሩ ሰዎች የሚዘወተር ሐሳብ ነበር፣ እንዲሁም በእስራኤል ይኖሩ ከነበሩ በዚህ በግሪክ ፍልስፍና የተሳቡ ሰዱቃውያን ተብለው የሚጠሩ አንድ የአይሁድ ኅብረተሰብ ይህንን አመለካከት ያራምዱ ነበር ወይም ደግሞ ትንሳኤ ሙታን የሚባል ነገር የለም ብለው ያምኑ ነበር።   

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ይህ የተሳሳተ ሐሳብ መሆኑን ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ራሱን በመጥቀስ ያስረዳቸዋል።  ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ከሞተ በሶስተኛው ቀን በነፍስ እና በሥጋ መነሳቱን ይጠቅስላቸዋል። “የሙታን ትንሣኤ” የክርስትና እምነት መሠረት የሆነ ትልቁ እውነታ ነው። የሙታን ትንሣኤማ ባይኖር ክርስትና የሚባል እምነት ባልኖረ ነበር፣ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በዚሁ ትንሣኤው የኀጢአት ውጤት የሆነውን ሞትን ድል በመንሳቱ ኀጢአታችን ሁሉ ተደምሦ ሞት የሰው ልጅ የመጨረሻ መቋጠሪያ እንዳልሆነ ተረጋገጠ። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን በተመለከተ ሲናገር “ነገር ግን በምሕረቱ ባለጠጋ የሆነ እግዚአብሔር ለእኛ ካለው ከታላቅ ፍቅሩ የተነሣ፣ 5በበደላችን ሙታን ሆነን ሳለ፣ በክርስቶስ ሕያዋን አደረገን፤ የዳናችሁት በጸጋ ነው” (ኤፌ 2 ፡ 4-5) ይለናል። ስለዚህ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ሕይወትን ሊሰጠን የቻለው የእርሱን ሕይወት የቀማውን ሞት ድል በመንሳቱ ነው፣ ሞትን ድል በማድረጉ ነው። ይህማ ባይሆን ይላል  ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ራሱ በዚሁ ምዕራፍ ቁጥር 14 ላይ “ስብከታችንም እምነታችንም ከንቱ ነው” ይላል። ነገር ግን  ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል በማድረጉ ኀጢአታችንንና በደላችንን መደምሰስ ብቻ ሳይሆን ዘለዓለማዊ ሕይወትንም አወረሰን።

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ከሞት ለመነሳት የበኩር እንደሆነ ይናገራል፣ ይህም የሚያሳየን እስራኤላውያን የበኩር የሆነውን ሁሉ ለእግዚአብሔር በመሥዋእትነት እንደሚያቀርቡትና በዛም በኩል የቀረው ሁሉ እንደሚባረክላቸው እንዲሁም ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በራሱ ሥልጣን ከሞት ለመነሳት የበኩር በመሆኑና ራሱንም ለእግዚአብሔር መሥዋእት አድርጎ በማቅረቡ እኛ ተቀደስን ከኀጢአታችን ተፈታን የዘለዓለማዊ ሕይወት ተቋዳሾች ሆንን ሞት በአዳም በኩል እንደገባ ዘለዓለማዊ ሕይወት ደግሞ በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በኩል መጣ። ሰዎች ሁሉ በአዳም በኩል ኀጢአተኛ ሆነው እንደተወለዱና በዚሁም ምክንያት ሞት እንደተፈረደባቸው በክርስቶስ አማካኝነት ደግሞ ጻድቃን ይሆናሉ፣ በስተመጨረሻም የጽድቅን አክሊል ዘለዓለማዊ ሕይወትን ይወርሳሉ ማለት ነው።  

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚያሳስበን ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ከውልደቱ እስከሞቱና ትንሣኤው ድረስ አባቱን ማክበር ዓለምና በርሷ ያሉትን በስተመጨረሻም ራሱንም ጭምር ለአባቱ ማስገዛት እንደሆነ ይነግረናል። ይህ እንግዲህ እኛም በየትኛውም አካሄድ ለዕለታዊ እንቅስቃሴ በማህበራዊ ሕይወት በቤተሰባዊ ትስስር ሁሉ እግዚአብሔር በእኛ ውስጥ እንዲከብር ማድረግ መሆኑን ያመላክታል።  ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በሁለተኛ መለክቱ ላይ ሲነበብ እንደሰማነው ሁላችን የጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ዳግም ምፅአት መጠበቅ ያለብን በሁሉም እንቅስቃሴዎቻችን በሙሉ እግዚአብሔር በሕይወታችን እንዲክብር የሚያደርጉ መሆን እንዳለባቸው ያሰምርበታል። የጌታ ቀን በድንገት እንደሌባ እንደሚመጣ ያሳስበናል፣ ይህ ማለት በሌላ አነጋገር ሁሌም እንደእውነተኛ የእግዚአብሔር ልጆች ከኀጢአት ርቀን በእርሱ ጸጋ እንመላለስ ማለት ነው። ይህንን ማለቱ ነው ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በቁጥር 14 ላይ “ስለዚህ ወዳጆቼ ሆይ ይህን እየጠበቃችሁ ያለውና የለነቀፋ በሰላም ለመኖር ትጉ”እያለ ምክሩን የሚለግሰን።

ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ደኅንነት ሲመጣ በስራችን ማፈርና መሸማቀቅ የለብንም ሕይወታችንን በቅድስና፣ በትገዕስት፣ በእምነትና በጽናት የምንኖረው ከሆነ የሚያሸማቅቀን ነገር የለም። አንድ ሰው እንደ እውነተኛ ክርስቲያን የሚኖር ከሆነ እርሱ እውነተኛ የክርስቶስ ተከታይ ነው፣ ክርስቶስን መከተል ማለት ደግሞ ሌላ ብዙም ሐተታ የለውም፣ የእርሱን ትእዛዝ መፈጸም ነው፣ ትእዛዙ ደግሞ እግዚአብሔርንና ባለእንጀራን እንደእራስ አድርጎ መውደድ ነው። ይህ አካሄድ ብቻነው በመጨረሻ ጊዜ በልበ ሙሉነት በእግዚአብሔር ፊት ያለ ምንም መሸማቀቅ እንድንቆም የሚያደርገን። የዛሬው ቅዱስ ወንጌል ንባብም እንዴት አድርገን የዚህ የታላቁ ግብዣ ተካፋይ እንደምንሆን ይነግረናል። እግዚአብሔር የዚህ ግብዣ ተካፋዮች ሊያደርገን መልካም ፈቃዱ ነው፣ ስለዚህ በዚህ ግብዣ ላይ ተካፋይ እንዳንሆን ከሚያደርጉን ነገሮች እንድንሸሽ ይመክረናል። ለብዙ ኀጢአቶች መነሻና መድረሻ የሆነውን ገንዘብን የምናይበት ሁኔታ በሚገባ እንድናጤን ይመክረናል። ገንዘብ በመሠረቱ ለሰው ልጅ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው ተገቢ ቢሆንም ገንዘብን ከሚገባው በላይ በሕይወታችን ላይ እንዲነግስ መፍቀድ በራሳችን ላይ፣ በትዳራችን ላይ ሠይጣንን ግብዣ እንደመጥራት ይቆጠራል። ገንዘብ ይሁዳን ጌታውን እንደሸጠና ለጠላቶቹ አሳልፎ እንዲሰጥ አድርጎታል እዚህ ጋር ገንዘብ ስንል ከእርሱ ጋር ዝምድና ያላቸውን ነገሮች ሁሉ ይጨምራል። ማንኛውም ነገር ከልኩ አልፎ ሲሄድ በስተኋላ የሚያመጣብን ጠንቅ እንዳለ በሚገባ ማስተዋል ይኖርብናል።

 ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን በተመለከተ ሲናገር “የገንዘብ ፍቅር የክፋት ሁሉ ሥር ነው፤ አንዳንዶች ባለጠጋ ለመሆን ካላቸው ጒጒት የተነሣ ከእምነት መንገድ ስተው ሄደዋል፤ ራሳቸውንም በብዙ ሥቃይ ወግተዋል”  (1ጢሞ 6፡10 )።  ሐብትን ማከማቸት በእግዚአብሔር ዘንድ ነው ለምድራዊውም ለሰማያዊውም ቤት ያገለግላልና፣ ሀብትን በምድር ማከማቸት ምድራዊውንም ሰማያዊውንም ጉዞ ያፈርሳል። ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ “ልባችን የእግዚአብሔር፣ የጌታችን እየሱስ ክርስቶስ፣ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ እንደሆነ” (ኤፌ 3፡17)  ይናገራል፣ ነገር ግን ልባችን በገንዘብና በሐብት ሐሳብ ብቻ ከሞላ ይህ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ የተባለው ልባችን የገንዘብና የሐብት ባንክ ይሆናል ማለት ነው። ይህ ደግሞ በሌላ አነጋገር ሲታይ ልክ ይሁዳ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ለገንዘብ ሲል እንደሸጠው እኛም ለገንዘብና ለሐብት ብለን እርሱን አስወጥተን በገንዘብ ሐብት ሞላነው ማለት ነው፣ ይህ እኛንም ከይሁዳ ተርታ የሚያሰልፈንና የክርስትና ኑሮአችንን የሚያበላሽብን በመጨረሻም ተጠያቂ የሚያደርገን ይሆናል። 

በዛሬው የቅዱስ ወንጌል ምንባብ ውስጥ (ሉቃስ 12፡32-40 ይመልከቱ) ኢየሱስ ደቀ-መዛሙርቱን በቋሚነት ነቅተው ይጠብቁ ዘንድ ያሳስባቸዋል። ለምን? በአንድ ሰው ሕይወት ውስጥ የእግዚአብሔርን ጉዞ ለመረዳት ይቻል ዘንድ ነው፣ ምክንያቱም እግዚአብሔር ያለማቋረጥ ወደ ሕይወታችን ውስጥ ይገባል። እናም ነቅተን ለመኖር የምንችልባቸውን መንገዶች በማሳየት “በአጭር ታጥቃችሁ ተዘጋጁ፤ መብራታችሁም የበራ ይሁን” (ሉቃስ 12፡35) ይለናል። ይህ ቅድመ ሁኔታ ነው። በመጀመሪያ “በአጭር ታጥቃችሁ ተዘጋጁ” የሚለው ሐረግ በራሱ ለጉዞ የሚደረገውን ዝግጅት የሚያመለክት ሲሆን በአጠቃላይ ጉዞ ለማደረግ ዝግጁ ሆኖ መጠበቅን ያመለክታል። ምቾት በሚሰጡን ነገሮች እና ደህንነታችንን በሚያረጋግጡ ምቹ በሆኑ ግንቦች ውስጥ ተከልሎ መኖር እና ሥር መሰረታችንን በእነዚህ ነገሮች ላይ እንዳናደርግ የሚያሳስበን ሲሆን ነገር ግን ከእነዚህ ነገሮች ተላቀን በሕይወታችን ውስጥ ወደሚቀጥለው እግዚአብሔር ወደ ሚመራን ግብ በመራመድ የእግዚአብሔርን ፈቃድ በመፈጸም፣ እግዚኣብሔር በሕይወታችን ውስጥ ይመላለስ ዘንድ በእምነት እና በትህትና ራሳችንን ለእርሱ ክፍት ማደረግ ማለት ነው። በዚህ አስቸጋሪ የሕይወት ጉዞ ውስጥ ስህተት እንዳንሥራ ጌታ ሁል ጊዜ እጃችንን በመያዝ ከእኛ ጋር አብሮ ይጓዛል። በእውነቱ ፣ በእግዚአብሄር የሚታመኑ ሰዎች የእምነት ሕይወት እንዲሁ ዝም ብሎ ቀጥ ብሎ የቆመ ነገር ሳይሆን ተንቀሳቃሽ የሆነ ነገር መሆኑን ይረዱታል። የእምነት ሕይወት-ጌታ ራሱ በየቀኑ ወደ ሚያመለክተው ወደ አዳዲስ ደረጃዎች የሚወስድ ቀጣይ ጉዞ ነው። ምክንያቱም እርሱ አስገራሚ፣ አዳዲስ ነገሮችን የሚፈጽም፣ እውነተኛ የሆኑ አዳዲስ ነገሮች በሕይወታችን ውስጥ እንዲከሰቱ የሚያደረግ ጌታ ነው።

በቀዳሚነት የነበረው ቅድመ ሁኔታ “በአጭሩ ታጥቃችሁ ጠብቁ” የሚለው ሲሆን ከእዚያ በመቀጠል ደግሞ የሌሊት ጨለማን ማብራት ይቻል ዘንድ “መብራትችሁ የበራ ይሁን” ይለናል። የሕይወትን “ሌሊቶች” ብርሃን ማብራት የሚችል እውነተኛ እና የበሰለ እምነት እንዲኖር ተጋብዘናል። ሁላችንም ብንሆን በሕይወት ሂደታችን ውስጥ የጨለሙብን መንፈሳዊ ሕይወት እንደ ነበረ እናውቃለን። የእምነት አምፖሎቻችንን ለማብራት እንችል ዘንድ ከኢየሱስ ጋር ከልብ በመጸለይ እና ቃሉን በማዳመጥ ሕይወታችንን በእምነት ብርሃን ሁል ጊዜ መመገብ ይጠይቃል። ከእዚህ ቀደም ብዙን ጊዜ ደጋግሜ የተናገርኩትን አንድ ነገር ዛሬም ቢሆን በድጋሚ ለማንሳት እፈልጋለሁ፣ አንዲት ትንሽ የሆነች መጽሐፍ ቅዱስ ሁልጊዜ በኪሳችሁ እና በቦርሳችሁ ውስጥ አድርጋችሁ በመሄድ አንብቡት። ይህም ከኢየሱስ እና ከቃሉ ጋር ቀጣይነት ባለው መልኩ እንድትገናኙ ይረዳችኋል። በጸሎት እና መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ ከኢየሱስ ጋር የተገናኘ ይህ መብራት ለሁሉም ሰዎች መልካም አገልግሎት ይሆን ዘንድ እንድናውለው በአደራ ተሰጥቶናል፣ ስለሆነም ማንም ሰው የራሱን ድነት ብቻ በእርግጠኝነት አይመለከትም፣ የሌሎች ሰዎችን ድነት ጭምር የመለከታል። አንድ ሰው የራሱን ውስጥ ብቻ በራሱ ኃይል ማብራት ይችላል ብሎ ማመን በራሱ ቅዤት ነው። እውነተኛ እመንት ራሱን ለሌሎች ክፍት ያደርጋል፣ ከወንድሞቹ ጋር መልካም የሆነ ሕበረት ይፈጥራል፣ በተለይም ደግሞ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ካሉ ሰዎች ጋር ግንኙነትን መፍጠር ያለመክታል። እናም ኢየሱስ ይህንን አመለካከት በሚገባ እንድንገነዘብ ለማድረግ ከሠርጉ ሲመለስ የጌታውን መምጣት የሚጠባበቁትን አገልጋዮች ምሳሌ (ሉቃስ 12፡36-40) በመናገር ነቅተን የምንጠብቀበትን ሌላ መንገድ በመጠቆም፣ በመጨረሻው ቀን ከጌታ ጋር ለመገናኘት በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ሆነን መጠበቅ እንደ ሚገባን ያመለክታል። እያንዳንዳችን በእዚያ የመጨረሻ ቀን ከእርሱ ጋር ፊት ለፊት መገናኘታችን አይቀሬ ነው። እያንዳንዳችን በመጨረሻው ቀን ከኢየሱስ ጋር የምንገኛኝበት ቁርጥ ቀን እንዳለን መዘንጋት አይኖርብንም። ኢየሱስ “ጌታቸው በሚመጣበት ጊዜ ነቅተው የሚያገኛቸው አገልጋዮች ብፁዓን ናቸው፤ እውነት እላችኋለሁ፤ ጌታቸውም በአጭር ይታጠቃል፤ በማእድ ያስቀምጣቸዋል፤ ቀርቦም ያስተናግዳቸዋል። ከሌሊቱ በሁለተኛውም ሆነ በሦስተኛው ክፍል መጥቶ እንደዚያው ነቅተው ቢያገኛቸው፣ እነዚያ አገልጋዮች ብፁዓን ናቸው” (ሉቃ 1፡37-38) በማለት ይናገራል። በእነዚህ ቃላት ጌታ ሕይወት ወደ ዘላለማዊነት የሚደረግ ጉዞ መሆኑን ያስታውሰናል፣ ስለዚህ “ምክንያቱም በዚህ ቋሚ ከተማ የለንም፤ ነገር ግን ወደ ፊት የምትመጣዋን ከተማ እንጠብቃለን” (ዕብ 13፡14) የሚለውን በፍጹም ሳንዘነጋ ለእኛ የተሰጡን መክሊቶች ፍሬ እንዲያፈሩ ማደረግ ይኖርብናል። በዚህ አተያይ፣ እያንዳንዱ ጊዜ ውድ ይሆናል፣ ስለሆነም በእዚህ ምድር ላይ በምንኖርበት ወቅት ሁሉ ለሰማይ ቤት ያለንን ከፍተኛ ናፍቆት በመግለጽ ልንኖር ይገባናል፣ እግሮቻችንን በእዚህ ምድር ላይ በማደረግ፣ በእዚህ ምድር ላይ በመጓዝ፣ በእዚህ ምድር ላይ ሆነን በመሥራት፣ በእዚህ ምድር ላይ ሆነን መልካም የሚባሉ ተግባራትን በማከናወን፣ ልባችን እና አእምሮዋችን የሰማይ ቤትን እንዲናፍቁ ማደረግ ይኖርብናል።

ይህ ታላቅ ደስታ ምንን እንደሚያካትት በትክክል መረዳት አንችልም፣ ሆኖም ኢየሱስ ጌታቸው በተመለሰበት ሰዓት እና ወቅት ነቅተው ያገኛቸውን አገልጋዮቹን “እውነት እላችኋለሁ፤ ጌታቸውም በአጭር ይታጠቃል፤ በማእድ ያስቀምጣቸዋል፤ ቀርቦም ያስተናግዳቸዋል” (ሉቃ 12፡37) ብሎ ጌታው የተናገረው ቃል በእኛም ላይ እንደ ሚተገበር ለመገመት ይቻላል። የሰማይ ቤት ዘላለማዊ ደስታ በዚህ መንገድ ይገለጣል፦ ሁኔታው ወደ ጌትነት ይቀየራል፣ እናም አገልጋይ የሚባል ሰው አይኖርም፣ እግዚአብሔር እኛን ለማገልገል ራሱን ለእኛ ያቀርባል። አሁን ኢየሱስ ለእኛ እያደረገ የሚገኘው ጉዳይ ይህ ነው፣ ኢየሱስ ስለ እኛ ይጸልያል፣ ኢየሱስ ወደ እኛ ይመለከታል፣ ስለእኛ ወደ አባቱ ጸሎቱን ያቀርባል፣ ኢየሱስ አሁንም ቢሆን እኛን እያገለገለን ይገኛል፣ እርሱ የእኛ አገልጋይ ነው። እናም ይህ ትክክለኛ ደስታ ይሆናል። በመጨረሻው ዘመን በምህረት ከተሞላው ከእግዚኣብሔር ጋር መገናኘታችንን ማሰቡ በራሱ በተስፋ ይሞላናል፣ ንጹህ እና ነቀፋ የሌለብን ሆነን ለመገኘት ቀጣይነት ባለው መልኩ እንድንተጋ ያነሳሳናል። የበለጠ በፍትሐዊነት እና በወንድማማችነት መንፈስ የተሞላ ዓለም እንድንገነባ ያነሳሳናል።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ይህንን ጥረታችንን በእናታዊ አመላጅነቷ እንድትደግፈው ልንማጸናት ይገባል።

ምንጭ ሬዲዮ ቫቲካን የአማርኛ የስርጭት ክፍል

አቅራቢ፡ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

12 December 2020, 12:50