መጥመቁ ዮሐንስ መጥመቁ ዮሐንስ  

የታኅሳስ 11/2013 ዓ.ም የሁለተኛው ስብከተ ገና ሳምንት ቅዱስ ወንጌል እና አስተንትኖ

የስብከተ ገና ወቅት መንፈሳዊ ለውጥ የምናመጣበት ወቅት ሊሆን ይገባል!

የእለቱ ምንባባት

1.      ኢሳያስ 40፡1-5

2.    መዝሙር 84

3.    2 ጴጥሮስ 3፡8-14

4.    ማርቆስ 1፡1-8

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

የመጥምቁ ዮሐንስ ስብከት

የእግዚአብሔር ልጅ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መጀመሪያ። በነቢዩ በኢሳይያስ፣ እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል፤ “እነሆ መንገድህን የሚያዘጋጅ መልእክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ፤‘የጌታን መንገድ አዘጋጁ፤ ጥርጊያውንም አስተካክሉ እያለ በበረሓ የሚጮኽ ድምፅ’።” ስለዚህ መጥምቁ ዮሐንስ በበረሓ እያጠመቀና ለኀጢአት ስርየት የንስሓ ጥምቀት እየሰበከ መጣ። የይሁዳ አገር በሞላ፣ የኢየሩሳሌም ሰዎች በጠቅላላ ወደ እርሱ በመሄድ ኀጢአታቸውን እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ እጅ ተጠመቁ። ዮሐንስ የግመል ጠጒር ይለብስ፣ በወገቡ ጠፍር ይታጠቅ፣ አንበጣና የበረሓ ማር ይበላ ነበር። ስብከቱም፣ “እኔ ጐንበስ ብዬ የጫማውን ማሰሪያ መፍታት ከማይገባኝ፣ ከእኔ የሚበልጥ ከእኔ በኋላ ይመጣል፤ እኔ በውሃ አጠምቃችኋለሁ፤ እርሱ ግን በመንፈስ ቅዱስ ያጠምቃችኋል” የሚል ነበር።

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

የዚህ እሁድ ቅዱስ ወንጌል ምንባብ (ማርቆስ 1፡1-8) የመጥምቁ ዮሐንስን ግለሰባዊ ማንነት እና ሥራ ያስተዋውቀናል። እሱ የስብከተ ገና ወቅት ለእኛ ከሚያቀርበው ጋር ተመሳሳይነት ያለው የእምነት የጉዞ መስመር ለእርሱ በዘመኑ ለነበሩ ሰዎች ይገልጻል - በገና ጌታን ለመቀበል ራሳችንን እንድናዘጋጅ ይመክረናል። ይህ የእምነት መንገድ ጉዞ የመቀየሪያ መንገድ ነው። ‘መለወጥ’ የሚለው ቃል ምን ማለት ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ፣ ከሁሉም በፊት እና ከሁሉም በላይ አቅጣጫ እና ባሕሪይ መለወጥ ማለት ነው፣ እናም እንዲሁም የአንድን ሰው አስተሳሰብ መቀየር ማለት ነው። በሥነ ምግባር እና በመንፈሳዊ ሕይወት መለወጥ ማለት ራስን ከክፉ ወደ መልካም ፣ ከኃጢአት ወደ እግዚአብሔር ፍቅር መለወጥ ማለት ነው። እናም መጥምቁ በይሁዳ ምድረ በዳ ውስጥ “በበረሓ እያጠመቀና ለኀጢአት ስርየት የንስሓ ጥምቀት እየሰበከ መጣ” (ማርቆስ 1፡4)። ምስጢረ ጥምቀት መቀበል የእርሱን ስብከት አዳምጠው ንስሐ ለመግባት የወሰኑ ሰዎች የመለወጫቸው ውጫዊና የሚታይ ምልክት ነበር። ያ ጥምቀት በዮርዳኖስ ወንዝ በውኃ ውስጥ ከመጥለቅ ጋር የተከናወነ ቢሆንም ዋጋ ቢስ ሆኖ ተገኝቷል፣ እሱ አንድ ምልክት ብቻ ነበር እናም ለንስሃ እና ህይወትን ለመለወጥ ፈቃደኝነት ከሌለ ዋጋ የለውም ነበር።

መንፈሳዊ ለውጥ ለማምጣት በቅድሚያ በፈጸምነው ኃጢአቶች ማዘን፣ ከእነሱ ነፃ የመሆን ፍላጎት እና ለዘላለም ኃጢአትን ከሕይወታችን ውስጥ አስወጥተን የመኖር ዓላማን ያካተተ መሆን ይኖርበታል። ኃጢአትን ለማስቀረት ደግሞ ከኃጢአት ጋር የተዛመዱትን ነገሮች ማስወገድ እጅግ አስፈላጊ ነው፣ ከኃጢአት ጋር የተዛመዱና የውድቀታችን ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮች - ዓለማዊ አስተሳሰብ ፣ ከመጠን በላይ የሆነ ምቾትን መመኘት፣ ለመዝናናት ከፍተኛ የሆነ ፍላጎት ማሳደር፣ ሐብት ለማጋበስ እና ጥሩ ኑሮ ለመኖር ከፍተኛ ጉጉት መፍጠር እነዚህ ሁሉ ከኃጢአት ጋር የተዘመዱ ነገሮች ናቸው። ይህንን የሚያሳየው ምሳሌ በዛሬው እለት በተነበበው ቅዱስ ወንጌል ውስጥ በመጥምቁ አማካይነት እንደገና ወደ እኛ መጥቶልናል ፤ ከመጠን በላይ የሆነ ምቾትን የማይመኝ ነገር ግን አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ብቻ የሚመኝ ሰው መሆን ማለት ነው። ይህ የመለወጥ የመጀመሪያ ደረጃ ነው -ከኃጢአት እና ዓለማዊነት መራቅ-ከእነዚህ ነገሮች የመነጠል ጉዞን መጀመር የመጀመሪያው እርምጃ ነው።

ሌላኛው የመንፈሳዊ ለውጥ ማምጫ ሁለተኛው መንገድ ደግሞ እግዚአብሔርን እና የእርሱን መንግሥት መፈለግ ነው። ከዓለማዊ ነገሮች መገለል እና እግዚአብሔርን እና መንግስቱን መፈለግ። ዓለማዊ የሆኑ ምቾቶችን መተው እና ዓለማዊ አስተሳሰብን ማስወገድ በራሱ ግብ አይደለም፣ ንስሐ መግባቱ ብቻ በራሱ በቂ አይደለም፣ አንድ ክርስቲያን “ሚስኪን” ሰው መሆን የለበትም። ነገሩ ሌላ ነው። ከዓለማዊ ነገሮች ራስን መነጠል በራሱ ግብ አይደለም፣ ነገር ግን ከእዚያ ባሻገር እጅግ የላቁ ነገሮችን ማለትም የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማግኘት ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ለመፍጠር ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ወዳጅነት ለማጠናከር በንቃት መስራት ማለት ነው። ነገር ግን ይህ ቀላል አይደለም፣ ምክንያቱም ከኃጢአት ጋር በቅርበት የሚያስተሳስሩን ብዙ ነገሮች አሉ ፤ ቀላል አይደለም .... ፈተና ሁል ጊዜ ወደ ታች ይጎትተናል፣ ጨምድዶ ይይዘናል፣ ወደ ኃጢአት እንድንጠጋ የሚያደርገንን ትስስር ይፈጥርልናል - አለመተማመን ፣ ተስፋ መቁረጥ ፣ ክፋት ፣ ጤናማ ያልሆኑ አካባቢዎችን ማዘውተር ፣ መጥፎ ምሳሌዎችን መከተል። አንዳንድ ጊዜ ለጌታ ያለን ፍላጋጎት በጣም ደካማ ነው፣ እናም እግዚአብሔር ዝም ያለ ይመስላል። የመጽናናት ተስፋዎቹ ለእኛ እንደ ሩቅ እንደ ሆኑ በዛሬው የመጀመርያም ምንባብ ላይ እንደ ተገለጸው “አጽናኑ፤ ሕዝቤን አጽናኑ፤ ይላል አምላካችሁ” (ኢሳያስ 40:1) በማለት ኢሳያስ በትንቢቱ አንደ ገለጸው እግዚአብሔር ለእኛ አሳቢ እና እውነተኛ እረኛ እንዳልሆነ ሁኖ ይሰማናል፣ ወይም ይታየናል። እናም በእዚህ የተነሳ አንድ ሰው በእውነት መንፈሳዊ መለወጥ ማምጣት አይቻልም ብሎ በማሰብ ፈተና ውስጥ ይወድቃል። ይህንን የመሰለ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ምን ያህል ጊዜ ተሰምቶናል! “አይ ፣ እኔ ማድረግ አልችልም። በጭንቅ እጀምራለሁ ከዚያም ወደ ኋላ እመለሳለሁ” በማለት ማሰብ እንጀምራለን። እናም ይሄ መጥፎ የሆነ ነገር ነው። ነገር ግን ይቻላል፣ በሚገባ ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል። የእዚህ ዓይነት ተስፋ አስቆራጭ ሐሳብ በሚያጋጥማችሁ ወቅት በእዚህ ሐሳብ ውስጥ ገብታችሁ እየቆዘማችሁ አትኑሩ፣ ምክንያቱም ወድቀታችንን የሚያቀላጥፍ ነገር ስለሆነ ነው። አንድ ሰው ወደ ፊት መሄድ ቢፈልግም ነገር ግን እሱ ወይም እሷ ማድረግ እንደማትችል ወደ ፊት መጓዝ እንደ ማትችል ሆኖ በሚሰማው ወቅት በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ ምን ማድረግ እንችላለን? በመጀመሪያ መንፈሳዊ ለውጥ ማምጣት በራሱ ፀጋ መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል፣ ማንም ሰው በራሱ ኃይል ወይም በራሷ ኃይል መለወጥ አይችሉም። ጌታ ለእኛ የሚሰጠን ጸጋ ነው፣ ስለሆነም እግዚአብሔር ይህንን ጸጋ እንዲሰጠን አጥብቀን ልንጠይቀው ይገባል። ወደ እግዚአብሔር ውበት ፣ ቸርነት ፣ ርህራሄ እራሳችንን በምንከፍትበት ደረጃ እኛን እንዲቀይረን እግዚአብሔርን በትህትና መጠየቅ ይኖርብናል። ስለ እግዚአብሔር ርህራሄ አስቡ። እግዚአብሔር መጥፎ አባት ፣ ደግነት የጎደለው አባት አይደለም ፣ በፍጹም እንድህ አይደለም። የመጨረሻውን የመንጋውን አባል እንደሚፈልግ እንደ ጥሩ እረኛ እርሱ በጣም ይወደናል። ፍቅር ነው ይህ ደግሞ መለወጥ ነው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው። መራመድ ትጀምራለህ ፣ እንድትሄድ የሚገፋፋው እሱ ስለሆነ ፣ እንዴት እንደሚመጣም ታያለህ። ጸልዩ፣ ተራመዱ ሁልጊዜ አንድ እርምጃ ወደ ፊት ለመንቀሳቀስ ሞክሩ፣ ለውጡን ታያላችሁና።

ያለ አዳም አጢአት የተጸነሰች እጅግ ንጽሕት የሆነቸው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እራሳችንን ለእግዚአብሄር ፣ ለቃሉ ፣ ለሚለውጠው እና ለሚያድነው ለእርሱ ፍቅር ራሳችንን ለእርሱ ለመክፈት ከኃጢአትና ከዓለማዊነት የበለጠ ለመለየት ትረዳን ዘንድ አማላጅነቷን መማጸን ይኖርብናል።

ምንጭ፡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በኅዳር 27/2013 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮ አደባባይ ካደረጉት አስተንትኖ የተወሰደ።

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

19 December 2020, 13:24