ኃጢአታችንን ይቅር እንዲለን  ወደ እግዚአብሔር እንጸልይ ኃጢአታችንን ይቅር እንዲለን ወደ እግዚአብሔር እንጸልይ 

ኃጢአት ምንድነው?

“በአዳም ምክንያት ወደ ዓለም ወረደ ኃጢአትም የዘለዓለም ሞትን አስከተለ (ሮሜ  5፣12) ይላል ቅዱስ ጰውሎስ፡፡ ኃጢአት አንድ ጊዜ በአዳምና በሔዋን ከተጀመረ በኃላ እየቀጠለ ሄደ፡፡ “ኃጢያት ማድረግ ማለት በዘለዓለማዊ ሕግ አንጻር ክፉ ማድረግ፣ መናገር፣ ማሰብ ነው” ይላል ቅዱስ አውጉስጢኖስ፡፡ ቅዱስ ቶማስ ስለ ኃጢአት  ሲገልጽ «እግዚአብሔርን በመተው ወደ ፍጡር መመለስ ነው” ይላል፡፡ ቅዱስ አምብሮስዮስ ደግሞ «ኃጢአት የእግዚአብሔር ሕግ መጣስ ነው፣ ትእዛዛቱን እምቢ ማለት ነው እያለ ይናገራል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ኃጢአት ስንሰራ ከደጉ አባታችን ከእግዚአብሔር ጋር እንጣላለን፡፡ ኢየሱስ ኃጢአት እንዴት ያለ ታላቅ በደል መሆኑንና የሚያደርገውንም እንዴት ባለ አሳዛኝ ሁኔታ እንደሚጥለው ሊያስረዳን ጠፎቶ የተገኘውን ልጅ ምሳሌ ሰጥቶናል፡፡ ይህ ልጅ አንድ ቀን ጠግቦ አባቱን «አባባ ከሀብትህ ከፍለህ ድርሻዬን ስጠኝ” (ሉቃ.  15፣12) አለው፡፡ አባቱም እያዘነ ሳይወድ ፍላጐቱን ፈጸመለት፡፡ ልጁ የፈለገውን ያህል ተቀብሎ የአባቱን ፍቅር ንቆ  ገንዘቡንም ይዞ ወደ ሩቅ አገር ኰበለለ፡፡ በዚህ አገር እርሱን ከመሰሉ ወሮበሎች ጋር ሆኖ የተቀበለውን ገንዘብ በሙሉ አጠፋው፡፡ ባዶ እጁን ከቀረ በኃላ በአገሩ ረሃብ ሆነ እና ስራም ስላጣ የሰዎችን አሳማዎች መጠበቅ ግድ ሆነበት፡፡ ከረሃቡም ብዛት የተነሳ ምግብ አጥቶ ለአሳማዎች ይሰጥ የነበረውን ጥራጥሬ ሊበላ ይመኝ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህንንም እንኳን ሊያገኝ አልቻለም፡፡

እኛም በኃጢአት ስንወድቅ በጣም ከሚወደን፣ ከሚያስብልን ከአባታችን ከእግዚአብሔር ጉያ ውስጥ በፍላጐታችን ኰብልለን ወደ ሰይጣን እንሄዳለን፡፡ በሰይጣን ሥልጣን ሥር ከወደቅን በስንት ትግልና ጥረት ያካበትነውን መንፈሳዊ ሃብትና ጸጋ ተገፈን እራቁታችን እንቀራለን፡፡ የታላቁ ንጉስ ልጆች፣ ሀብታሞችና ክቡራን የነበርን በኃጢአት ምክንያት የሰይጠን ባሪያዎችና አገልጋዮች፣ ድሆችና መከረኞች እንሆናለን፡፡ በውስጣችን ደግሞ ይህ ነው በማይባል የመንፈስ ድኽነት እንሰቃያለን፡፡

ሰው ንጉሥ ሳለ ንጉሥ መሆኑን አላወቀም፣ ክቡር እያለ ክብሩን ባለመገንዘብ እንደ እንሰሳት ሆኖ ራሱን አዋረደ፡፡ በገዛ ፈቀዱም ባሪያ ሆኖ ሊገዙት የማይገባቸው ጌቶች ገዙት፡፡ ሰው ሀብታም እያለ ባለማወቅ ሀብቱን ናቀ፡፡ በገዛ ፈቃዱ ራሱን አደኸየ ሰው ብርሃን የለበሰ ሳለ ሥጋው ራቁቱን እንዲሆን አደረገ ቆዳ ለበሰ፡፡ ሰው ከአምላክ በታች የዓለም ገዥ፣ ንጉሥ ሳለ እጁን ዘርግቶ የተከለከለውን ፍሬ ቀንጥሶ በላ (.አኰቴተ ቁርባን ዘቅ. አትናቴዎስ (መጽ.ቅዳሴ) ይላል ቅዱስ አትናቴዎስ።

ኃጢአት ከመስራታችን በፊት መጥፎው ነገር ደስ የሚል ሆኖ ይሰማናል፣ ቀስ በቀስም ይስበናል፣ ከሠራው በኋላ ግን በፍጥነት ራሱ ይወቅሰናል፣ ያሰቃየናልም፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ ልሳነ ወርቅ «ኃጢአት ከሠራኸው ወዲያው በፍጥነት በአንተ ላይ ፈራጅ ይሆናል ብሏል፡፡ ሁላችን አጣርተን እንደምናውቀው አንድ ጨካኝ ጌታ ብርቱ ጠላታችን ነው፡፡ «ክፋትን የሚወድ ነፍሱን ይጠላል (መዝ. 10፣5) ይላል ዘማሪው ዳዊት።እንደዚሁም ቅዱስ ያዕቆብ ኃጢአት ከሰራ በኋላ ሞትን ያመጣል (ያዕ. 1፣15) በማለት ተናግሯል፡፡ ኃጢአት በዚህ ዓለም ላይ ስቃይን ያመጣብናል፣ በሚመጣው ዓለም ደግሞ የባሰ ስቃይ ያመጣብናል፡፡ በዚህ ዓለም ሳለን ካሳ ካልከፈልን በሚመጣው ዓለም ካሳው ይከብደናልም፡፡

ታናሽ ኃጢአት ከሆነ በንስሐ ቦታ እንክሰዋለን፣ ታላቅ ኃጢአት ከሆነ ግን ለዘለዓለም በገሃነመ እሳት ስንሰቃይ እንኖራለን፡፡ የዚህን ካሳ ኃይለኛ ስቃይ ስለሆነ ምንጊዜም ራሳችንንም መርዳት አንችልም፡፡ የገሃነመ እሳት ቅጣት ወይም ይቅርና ከንስሐ ቦታ ካሳም የዚህ ዓለም ቅጣት በዚህ ዓለም መካሳ እጅግ ይሻላል፡፡ ምክንያቱም በዚህ ዓለም ሁሉም ነገር ቀላል ነው፣ በወዲያኛው ዓለም ግን ሁሉም ነገር መጠን የሌለው ብርቱ ነው ይከብደናል፡፡ ስለዚህ ገና በሕይወታችን ሳለን የኃጢአትችንን ዕዳ መክፈል ይሻለናል።

ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ «ኃጢአትን የሚሰራ ሰው የኃጢአት ባሪያ ነው (. 1ኛ ዮሐ. 3፣4) ይላል&ቀጥሎም «ኃጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው (1ኛ ዮሐ. 3፣8) ይለናል፡፡ እኛ ግን የእግዚአብሔር ነን፣ የተከበርን የነፃነት ልጆች ስለሆንን በገዛ ራሳችን ትልቅነታችንን አናበላሽ፣ የኃጢአት ባሪያዎች አንሁን፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ክርስቶስ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርበን እርሱ ፃድቅ ሆኖ ስለ ዓመጻኞች አንድ ጊዜ በኃጢአት ምክንያት ሞቶአልና (1ኛ ጴጥ. 3፣18) ስለሚለን እንደገና በድጋሚ በኃጢአታችን አንሙት፣ እንደገና ወደ ኃጢአት አንመለስ፡፡

መድኃኒታችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሽባውን «ከዚህ የባሰ ነገር እንዳይደርስብህ ከእግዲህ ወዲህ ኃጢአት አትሥራ (ዮሐ. 5፣10) በማለት እንዳስጠነቀቀው እኛንም ተመልሰን ወደ ኃጢአት እንዳንወድቅ ያስጠነቅቀናል። ኃጢአት ለጌታ ትልቅ በደል ለእኛም ትልቅ ጉዳት ነው፣ገዳያችንም ነው፡፡ እንግዲህ በልባችን እንጥላው፣ ከእርሱም እንራቅ በተቻለን መጠን ወደ ኃጢአት እንዳንወድቅ በርትተን ጠንክረን እንዋጋ፡፡

ነገር ግን ደካማነት አሸንፎን ወይም በሆነ ምክንያት ብንወድቅ ቶሎ ብለን በፍጥነት ንስሐ እንግባ፣ ይቅርታ እንጠይቅ፣ ቁርጥ ፈቃዳችንን ለመፈፀም እንበርታ፡፡ «ኢትፍርኀዋ ለሞት ፍርኀዋ ለኃጥአት” ኃጢአትን እንጂ ሞትን አትፍሩ የሚለውን ምክር በመንፈሳዊ ሕይወታችን ውስጥ ዘወትር የምንጠቀምበት መመሪያችን ይሁን።

16 December 2020, 12:54