ብርሃነ ልደቱ፤ ብርሃነ ልደቱ፤ 

የ2013 ዓ. ም. ብርሃነ ልደት፥ የተስፋ ብርሃን በጨለማ ውስጥ ይበልጥ የሚበራበት ነው።

የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ልደት በፍርሃት ተይዞ በጨለማ ውስጥ ለሚገኝ እና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስጋት ውስጥ ለገባው ዓለማችን ኃይለኛ ምልክት የተገለጠበት የተስፋ መልዕክት ነው። በዚህ የተስፋ ብርሃን ወቅት የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች እና ክርስቲያናዊ በጎ አድራጊ ድርጅቶች አስተባባሪዎች “ማንም ቢሆን ብቻውን ሊድን አይችልም” በማለት ካስተጋቡት መልዕክቶች መካከል የሚከተለውን እንመለከታለን፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን 

የተስፋ ብርሃንን እና ምሕረትን ወደ ዓለም ይዞ የመጣውን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ለማክበር በምንዘጋጅበት ወቅት፣ በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የገዳማዊያት ዓለም አቀፍ ኅብረት ዋና ዳሬክተር የሆኑት እህት ፓትሪሲያ ማሬይ፣ በብርሃን መመራትን ለሚፈልጉ በሙሉ የሚከተለውን ጸሎት አቅርበዋል።    

"መንገዳችሁ በጥላቻ የተሞላ ከሆነ በኢየሱስ ክርስቶስ ጥበቃ ሥር በመሆን ጨለማው ተወግዶ ብርሃን ይሙላበት፤ መንገዳችሁ በአመጽ የተሞላ ከሆነ በኢየሱስ ክርስቶስ ጥበቃ ሥር በመሆን ፍቅር ነግሦ ጥላቻ ይወገድ፤ መንገዳችሁ በጭንቀት የተሞላ ከሆነ በኢየሱስ ክርስቶስ ጥበቃ ሥር በመሆን ሰላም ነግሦ ፍራቻ ይወገድ፤ ጌታ ሆይ! ያንተን መምጣት ለዘመናት በተስፋ ጥብቀነዋል። ጨለማ ወርሶን ነበር፤ ቶሎ በእኛ መካከል እንድትሆን እንመኛለን፤ አንተ ከእኛ ጋር ከሆንክ የከበበንን ጨለማ ፈጽሞ አንፈራም፤ በሌሊት ከስቃይ በኋላ የሚሰማ የደስታ ድምጽ፣ ተስፋም በዓለማችን ላይ እንዲወርድ ጠብቀናልና"።

መሠረቱን በኢየሱስ ክርስቶስ ያደረገ ዓለም አቀፍ የገዳማዊያት ኅብረት፣ በመላው ዓለም የሚገኙ ገዳማዊያት ማኅበራትን የሚወክል ነው። ዓላማውም በልዩ ልዩ ገዳማዊያት ውስጥ የሚታየውን ሐዋርያዊ ሕይወት መመስከር እና ለሌሎች ማሳወቅ ነው። የዓለም አቀፍ ገዳማዊያት ኅብረት ዋና ተልዕኮ ርቀት እና ድንበር ሳያግደው አባላቱ በኅብረት እርስ በእርስ እንዲገናኙ የሚያስችሉ ድልድዮችን መገንባት ነው። ዓላማውም የገዳማዊያት ሕይወት በሌሎች ዘንድ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግ አባላቱን በተለያዩ የአገልግሎት መስክ በማሰማራት ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን መዋጋት፣ የስደተኞችን ደህንነት መጠበቅ፣ በሐይማኖት ተቋማት መካከል የውይይት ባሕልን ማሳደግ፣ ትምህርትን ማዳረስ፣ ፍትህን እና ሰላምን ማሳደግ እና ለፍጥረታት በሙሉ አስፈላጊውን እንክብካቤን ማድረግ ነው።                    

23 December 2020, 20:51