የኅዳር 6/2013 ዓ.ም ሰንበት ዘአስተምሕሮ 1ኛ ወንጌል እና የዕለቱ መልዕክቶች አስተንትኖ የኅዳር 6/2013 ዓ.ም ሰንበት ዘአስተምሕሮ 1ኛ ወንጌል እና የዕለቱ መልዕክቶች አስተንትኖ 

የኅዳር 6/2013 ዓ.ም ሰንበት ዘአስተምሕሮ 1ኛ ወንጌል እና የዕለቱ መልዕክቶች አስተንትኖ

የእለቱ ምንባባት

1.ሮሜ፡   5፡ 10-21

2. 1ዮሐ  2፡1-17

3.ሐዋ.ሥ 22 1-11

4. ማቴ 6፡5-15

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ስትጸልዩ እንደ ግብዞች አትሁኑ፤ እነርሱ ለሰዎች ለመታየት ሲሉ በየምኵራቡና በየመንገዱ ማእዘን ላይ ቆመው መጸለይ ይወዳሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፤ ሙሉ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። አንተ ግን ስትጸልይ ወደ ክፍልህ ግባ፤ በሩንም ዘግተህ በስውር ወዳለው አባትህ ጸልይ፤ በስውር የተደረገውን የሚያይ አባትህም ዋጋህን ይከፍልሃል። ስትጸልዩ፣ ከንቱ ቃላት በመደጋገም ጸሎታቸው የሚሰማላቸው እንደሚመስላቸው አሕዛብ ነገራችሁን አታስረዝሙ። እነርሱን አትምሰሏቸው፤ አባታችሁ ከመለመናችሁ በፊት ምን እንደሚያስፈልጋችሁ ያውቃልና።

“እናንተ ግን እንዲህ ብላችሁ ጸልዩ፤ “ ‘በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች፣ እንዲሁ በምድር ትሁን። የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን። እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል፣ በደላችንን ይቅር በለን። ወደ ፈተናም አታግባን ከክፉው አድነን እንጂ፣ መንግሥት፣ ኃይል፣ ክብርም፣ ለዘለዓለሙ ያንተ ነውና፤ አሜን። እናንተ የበደሏችሁን ይቅር ብትሉ የሰማዩ አባታችሁ ደግሞ እናንተን ይቅር ይላችኋል። ነገር ግን የሰዎችን ኀጢአት ይቅር የማትሉ ከሆነ፣ አባታችሁም ኀጢአታችሁን ይቅር አይልላችሁም።

የእለቱ የእግዚአብሔር ቃል አስተንትኖ

የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እና በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

በዚህም ዕለት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በተለያዩ ንባቦች አማካኝነት ወደ እያንዳዳችን በመምጣት የሚያስፈልገንን ይሰጠናል የጎደለውን ሁሉ ይሞላልናል በእርሱም ቃል እንድንኖር ያበረታታናል።

የአምልኮ ሥርዓታችን ዘመነ ጽጌ (የአበባ ወቅት) የሚባለውን ወቅት ጨርሶ በዚህ ሰንበት ዘአስተምሕሮ የሚባለውንና ለመጪዎቹ አምስት ሳምንታት የሚዘልቀውን ወቅት ጀምረናል። የምሕረት ወይም (ዘአስትምሕሮ) የትምህርት ዘመን የሚል አንድምታ እንዳለው ቢነገርም ሁሉም ግቡ የእሱን ምሕረት ማዳረስ ስለሆነ የክርስቶስ ልደት ከመከበሩ በፊት ስለ እግዚአብሔር ምሕረት በተለያዩ መልኩ እንድናስተነትን ይጋብዘናል።

በተለይም በእዚሀ ወቅት ከእግዚአብሔር ጋር ባለን ግንኙነት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ለማድረግ አንዳንድ ጊዜ በተለመደው ተግባራችን ውስጥ ትንሽ ለውጥ ማድረግ አለብን ፡፡ በዚህም መሰረት የእግዚአብሔር ምሕረት ነፍሳችን ላይ ጠብ እንዲልና የረሰረሰ መንፈሳዊ ሕይወት እንዲኖረን በዋነኝነት የሚያግዘን የጸሎት ሕይወታችን ነው። በዚህም መሠረት የዛሬው ወንጌል ስለጸሎት የሚለን ነገር አለው። መጀመሪያ ላይ "ስትጸልዩም እንደ ግብዞች አትሁኑ፤ ለሰው ይታዩ ዘንድ በምኩራብና በመንገድ ማዕዘንቆመው መጸለይን ይወዳሉና" ሲል እንዳንጸልይ ሰበብ የሚያዘጋጅልን ይመስላል። ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን ተሰባስቦ መጸለዩ፣ በየመንገዱ ማማተቡና መስገዱን ትርጉም የለሽ እያደረግን ከጸሎት ለማፈግፈግ ይዳዳን ይሆናል። ነገር ግን ክርስቶስ በሕዝብ ፊት መጸለይን በራሱ አላወገዘም፤ የተቃወመው የምንጸልይበት ሀሳብን ነው:- "ስትጸልዩም እንደ ግብዞች አትሁኑ፤ ለሰው ይታዩ ዘንድ በምኩራብና በመንገድ ማዕዘን ቆመው መጸለይን ይወዳሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል።" የሚጸልዩበት ዓላማ በሰው ይታዩ ዘንድ ስለሆነ ከእግዚአብሔር ጋር መገናኘትን አላሰቡም ስለዚህም ይህ ዓይነቱ ጸሎት ዋጋ እንደሌለው ነው ወንጌሉ የሚያስተምረን።

በማቴ. 11:25 እና በዮሐ. 11:45 ላይ እንደምናገኘው ክርስቶስ ራሱ በሕዝብ ፊት ጸልይዋል። እንዲሁም ጳውሎስ በሐዋ. ሥራ 27:35 ላይ እንደምናነበው በሕዝብ ፊት ጸሎት አድርጓል። ቁም ነገሩ በሕዝብ ፊት ሳይሆን በእግዚአብሔር ፊት መገኘታችንን ማሰቡ ላይ እንድናተኩር ነው። በአጭሩ መልእክቱ እንዴት የሚለውን እንጂ የት እንጸልይ የሚለውን እንድናስብ አይደለም።

የሚቀጥለው የወንጌል ጥቅስ ይበልጥ የላይኛውን ሀሳብ ያብራራልናል:- "አንተ ግን ስትጸልይ፥ ወደ እልፍኝህ ግባ መዝጊያህንም ዘግተህ በስውር ላለውአባትህ ጸልይ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል።" የጸሎታችን ግብ ወደ አባታችን መጸለይ ነው፤ ለእይታ፤ ለቃላት ድርደራ... ችሎታ ሳይሆን ናፋቂ አባት እንዳለው የሚያምን ልጅና አባቱን እንደሚናፍቅ ልጅ ሆነን ማንነታችንን በፊቱ እንድናደርግ ነው። ስለዚህም ክርስቶስ ያስተመረን ትልቁ የመጀመሪያ ነጥብ "ወደ እልፍኝህ ግባ" የሚለው ነው፤ ያም ወደ ልብህ ግባ፤ ውስጥህን ስማ፤ ከውስጥህ በሸሸህ ቁጥር ከእግዚአብሔር ትሸሻለህና ወደ እልፍኝህ ግባ ይለናል። ልባችን ውስጥ የተከማቸው የሚያስጠላ፣ ጥሩ ስሜት የማይፈጥርልን ወይም ደስ የማይል ነገር ይሆናል፤ ሆኖም ግን እግዚአብሔር ያንን ማንነታችንን ይፈልገዋል። ምክንያቱም እሱ ካልሆነ ሌላ ማንም ሊያሳምርልን የሚችል የለምና ልባችንን ደብቀን በውጫዊ ነገር ብቻ ልናገኘው አንችልም። ባለመጸለያችን ከርሱ የሸሸን መስሎን ወደ ሌላ ነገሮች በሄድን ቁጥር ውስጣችን እጥፍ ሸክም ይሆንብናል። ብንደብቀውም እንኳ እሱ ያውቀዋል ግን የደበቅነው መስሎን ራሳችንን እናታልላለን እንጂ መፍትሔው እንካ ደካማነቴን ማለት ነው። ዳዊት ይህን እውነት በተረዳ ጊዜ እንዲህ አለ:-

"ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ? ወደ ሰማይ ብወጣ፥ አንተ በዚያ አለህ። ወደ ሲኦልም ብወርድ፥ በዚያ አለህ። እንደ ንስር የንጋትን ክንፍ ብወስድ፥ እስከ ባሕር መጨረሻም ብበርር፥ በዚያ እጅህ ትመራኛለች፥ ቀኝህም ትይዘኛለች።" መዝ. 139:7-10

ጸሎት ከተውኩ ስንት ዓመቴ፣ አሁን ሌላ ዓለም ላይ ነው ያለሁት ምናልባት ወደፊት እድሜየም ገፋ ሲል ወደ ጸሎት እመለሳለሁ...የሚል ሰው ሊኖር ይችላል። ይህ ዓይነት አስተሳሰብ ግን ከራስና ከእግዚአብሔር የመሸሽ ሕይወት ነውና ጎዶሎነትን ያለማምደናል። በዛሬው ወንጌሉ ክርስቶስ ያን ዓይነት ኑሮ አይመኝልንም። ወደ ልብህ ግባ በዚያም አባትህን አናግር። የሚያስብላቸው አምላክ እንደሌላቸው ሰዎች አትባክን። በጣም ቅርብህ የሆነ አባት አለህ ይለናል።

አንድ ካህን ላለመጸለይ ያሉንን ምክንያቶች እንዲህ ጽፍውታል :-

ቀጣይ የሆነ የጸሎት ሕይወት መጓዝ አዳጋች ነው። አንዳንድ ምክንያቶች ግልጽ ናቸው:- የሥራ ብዛት፣ ድካም፣ ዘወትር የሃሳብ መበታተን (ቀጣይ ራስን መሰብሰብ ያለመቻል)፣ የመንፈሳዊ ሕይወት ስንፍና (ሀኬት)፣ የሚያሰለቸን ዓይነት ሥርዓተ አምልኮ፣ ምንም ትርጉም የማይሰጡን ዓይነትና የማይስቡጸሎት አደራረጎች ሊሆኑ ይችላሉ። ሌላ የምክንያት ዓይነትም አለ። ይህም ስለ ጸሎት ያለን ግንዛቤ ሲሆን ጸሎት ደስ የሚል፣ የሚስብ፣ የሚያነቃቃ መሆን አለበት ብለን እናስባለን። ሆኖም ግን ሁል ጊዜ ይህን ዓይነት ጸሎት ማድረግ አይቻልም። ለመጸለይ ውስጣዊ ተነሳሽነትና ፍላጎት አይኖረንም፤ ሆኖም ጸሎት ግን ይህን ሁሉ ተፈጥሯችንን ያከብራል።

ጸሎት ቅልል ሲለን፣ ሀሳብችንና ልባችን ወደ እግዚአብሔር ሲያቀና ብቻ፣ ከመሰላቸት፣ ከቁጣ፣ መጥፎ ከምንላቸው ስሜቶቻችን ነጻ ስንሆን የሚጸለይ ቢሆን ምን ያህል ቀናት ብቻ መጸለይ ይቻል ነበር ብለን ማሰብ አለብን። እንዲህማ ከሆነ እግዚአብሔር እኛ ጥሩ ስንሆን ብቻ ሊያየን የሚፈልግ አባት አደረግነው ማለት ነው።

በእውነት በሕይወታችን ውስጥ የሚካሄደውን መሸፈን ፈልገን መሆን የሚገባውን ብቻ መጸለይ እንዳለብን እናስባለን። ጸሎት ማለት እግዚአብሔር መስማት ያለበትን ለመንገር ዝግጁነት ነው ብለን ስናስበው መጸለይ ይከብደናል።

ስለዚህ ስለ ጸሎት ያለንን ግንዛቤ እንመርምር፤ እግዚአብሔር የሚጠብቀን፣ የሚሳሳልን፣ የሚናፍቀን አባት ነው እንጂ በዚህ ገባህ በዚህ ወጣህ ብሎ ሊያስጨንቀን የፈጠረን አምላክ እይደለም። እሱ አስቀድሞ እጅግ ስላፈቀረን እንድናፈቅረውና እንድንቀርበው ይጠብቀናል።

ለኛ ለክርስቲያኖች ጸሎት በሕይወታችን ውስጥ ከምናደርጋቸው ብዙ ነገሮች ውስጥ አንዱ ብቻ ምናልባት ጥቂት ደቂቃዎች የምንሰጠው ጉዳይ ሳይሆን ሕይወታችን ራሱ ጸሎት መሆን እንደሚገባው እናስብ። ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ "ሳታቋርጡ ጸልዩ" የሚለውን ስናነብ ለጸሎት ጊዜን ሳይሆን ለጸሎት ሕይወትን መስጠት እንዳለብን ያሳስበናል። ይህም ማለት መግባት መውጣታችን፣ መሥራት መድከማችን፣ ከሰው ጋር መገናኘት ብቻነታችን፣ ወዘተ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት መሆኑን ማስታወስ ማለት ነው። ቀሪ ጊዜያቶቹን እንደሚገባ ካልኖርናቸው አንድ ሰዓት፣ ሁለት ሰዓት ወይም ከዚያ በላይ በጸሎት ማሳለፍ ብቻ ትርጉም ላይኖረው ይችላልና ሳታቋርጡ ጸልዩ የተባልነው ሳናቋርጥ የእርሱን ፈቃድ ማሰብ መሆኑን አውቀን እንደፈቃዱ መኖርን እናዘውትር።

እሱ ሁሌ ከእኛ ጋር አለ፤ ሸሽተን ከማንደበቀው አምላካችን ለየቀኑ ስጦታው በጸሎትና በመሥዋዕት ይልቁንም ከጸሎቶች ሁሉ ጸሎት በሆነው በልጁ መሥዋዕት ማለትም በቅዳሴ እንቅረበው፤ በልባችን ውስጥ ትንሽም ቢሆን ቦታ እንስጠው ብቻም ሳይሆን ልባችንን እንስጠው።

የፀጋው ጉዞ ተከታዮች እና ድምጹንም ማዳመጥ የምንችልበትን ንቃተ ህሊና ለማግኘት እንድንችል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የእውነተኛ ሕይወት ምንጭ የሆነውን ልጇን  በቅርበት የምንከተልበትን  ኃይልና ብርሃንና  ታሰጠን የሰማነውን ቃል በተግባር ለማዋል እንድንችል ከጎናችን ሆና ታበረታታን እንደ ወትሮው ሁሉ ደግሞ በእግዚአብሔር ፊት ጠብቃችን ሁና ትቁምልን።

ምንጭ፡ ሬዲዮ ቫቲካን የአማርኛ የስርጭት ክፍል

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

13 November 2020, 11:39