የጥቅምት 22/2013 ዓ.ም ሰንበት ዘጽጌ 4ኛ የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የጥቅምት 22/2013 ዓ.ም ሰንበት ዘጽጌ 4ኛ የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ 

የጥቅምት 22/2013 ዓ.ም ሰንበት ዘጽጌ 4ኛ የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የእለቱ ምንባባት

1.      1ቆሮ. 10,1-18

2.    ራዕ 14፡1-5

3.    ሐዋ 4፡ 19-30 

4.    ማቴ. 12፡ 1-21

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ሰንበትን ስለ ማክበር

ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በሰንበት ቀን በእህል ዕርሻ ውስጥ አለፈ፤ ደቀ መዛሙርቱም ስለ ራባቸው እሸት ቀጥፈው ይበሉ ጀመር። ፈሪሳውያንም ይህን አይተው፣ “እነሆ፣ ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ቀን መደረግ የሌለበትን እያደረጉ ነው” አሉት።

እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች በተራቡ ጊዜ እርሱ ምን እንዳደረገ አላነበባችሁምን? 4ወደ እግዚአብሔር ቤት ገባ፤ ለካህናት እንጂ ለእርሱም ሆነ አብረውት ለነበሩት ያልተፈቀደውን የተቀደሰ ኅብስት በላ። ወይስ ካህናት ሰንበትን ሽረው በቤተ መቅደስ ውስጥ ሥራ ቢሠሩ በደል እንደማይሆንባቸው ከኦሪት ሕግ አላነበባችሁም? ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ከቤተ መቅደስ የሚበልጥ በዚህ አለ። ‘ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እወዳለሁ’ የሚለው ቃል ምን ማለት እንደሆነ ብታውቁ ኖሮ፣ በንጹሐን ላይ ባልፈረዳችሁ ነበር። የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና።”

ከዚያ ስፍራ ዕልፍ ብሎ በመሄድ ወደ ምኵራባቸው ገባ፤ በዚያም አንድ እጁ ሽባ የሆነ ሰው ነበር፤ ኢየሱስን ሊከሱት ምክንያት ፈልገው፣ “በሰንበት ቀን መፈወስ ተፈቅዶአል?” ብለው ጠየቁት።

እርሱም፣ “ከእናንተ መካከል የአንዱ ሰው በግ በሰንበት ቀን ጕድጓድ ቢገባበት በጉን ከገባበት ጕድጓድ ጎትቶ አያወጣውምን? ታዲያ ሰው ከበግ እጅግ አይበልጥምን? ስለዚህ በሰንበት ቀን በጎ ማድረግ ተፈቅዶአል” አላቸው።

ከዚያም ሰውየውን፣ “እጅህን ዘርጋ” አለው፤ ሰውየውም እጁን ዘረጋ፤ እንደ ሌላኛውም እጁ ደህና ሆነለት። ፈሪሳውያን ግን ከዚያ ወጣ ብለው ኢየሱስን እንዴት እንደሚገድሉት ተማከሩ።

እግዚአብሔር የመረጠው አገልጋይ

ኢየሱስ ሐሳባቸውን አውቆ ከዚያ ዘወር አለ። ብዙ ሕዝብም ተከተለው፤ ሕመምተኞችን ሁሉ ፈወሰ፤ ማንነቱን ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው። ይህም የሆነው በነቢዩ በኢሳይያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ነው፤“እነሆ የመረጥሁት፣ የምወደውና በእርሱ ደስ የሚለኝ አገልጋዬ፣ መንፈሴን በእርሱ ላይ አኖራለሁ፤ እርሱም ለአሕዛብ ፍትሕን ያውጃል። አይጨቃጨቅም ወይም አይጮኽም፤ ድምፁም በአደባባይ አይሰማም። ፍትሕን ለድል እስኪያበቃ ድረስ፣ የተቀጠቀጠውን ሸምበቆ አይሰብርም፤ የሚጤሰውንም የጧፍ ክር አያጠፋም። አሕዛብ በስሙ ተስፋ ያደርጋሉ።”

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

በክርሰቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ ዛሬ እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር ዘጽጌ 4ኛ የተሰኘዉን ሰንበት እናከብራለን። በዚህም ዕለት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በተለያዩ የዕለቱ ንባባት አማካኝነት መልዕክቱን ያስተላልፍልናል እናም የሰማነውን መልዕክት በተግባር ላይ ለማዋል እንድንችል አሁንም ጸጋና በረከቱን በላያችን ላይ ያፍስስልን። ቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ በዛሬው ለቆሮንጦስ ሰዎች በጻፈው መልዕክቱ ምንም እንኳን የቆሮንጦስ ሰዎች በትውልድ አይሁዳውያን ባይሆኑም በኣዳምና በሔዋን እንዲሁም በኣብርሃም ኣማካኝነት ሁላችን የኣንድ ኣባት ልጆች በመሆናችን የቀድሞ ኣባቶቻችን እያለ ያስረዳቸዋል። ሙሴ ኣይሁዳውያንን ከግብፅ ባርነት እየመራ ሲያወጣቸው እግዚኣብሔር ሕዝቡን ከበላያቸው ደመና ሆኖ ይመራቸው ነበር ኦሪት ዘጸኣት 13፡21 ቀይ ባሕርን ሲሻገሩ ባሕሩን ከሁለት በመክፈል እስራኤላውያኑን በደረቅ መንገድ ኣሻገራቸው ከጠላቶቻቸውም ታደጋቸው ኦሪት ዘጸኣት 14፡21-31 በተራቡ ጊዜ መናን ከሰማይ በማውረድ በተጠሙም ጊዜ ከዓለት ውኃን በመፍለቅ ጥማቸውን ቆረጠላቸው ኦሪት ዘጸኣት 16 እና 17። ቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ ዛሬ ይህንን የኦሪትን ክስተት ከቆሮንጦስ ሰዎች ጋር ሲያነጻጽረው ሙሴ የኣይሁድን ሕዝብ እንደመራ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ እንዲሁ በኣራያ ሥላሴ የተፈጠሩትን የእግዚኣብሔርን ልጆች ሁሉ ከዓለት ንቃቃት ወደ ለመለመው መስክ ይመራል በመስቀሉ ኣማካኝነት ከኃጢኣት ባርነት ወደ መንፈሳዊ ነፃነት ይመራል በመንፈስ በተራቡም ጊዜ ሥጋውን በተጠሙም ግዜ ክቡር ደሙን በመስጠት መንፈሳዊ ጥማቸውን ኣርክቷል። እስራኤላውያኑ ከእግዚኣብሔር ጋር ስለሚጓዙ ምንም የጎደለባቸው ነገር ኣልነበረም እንደውም የሚጓዙበት ቦታ ምንም በረሃና ሰው የመይገኝበት ቢሆንም እንኳን የእርሱ ኣጋዢነት ከእነርሱ ጋር ስለነበረ ኣንዳችም የጎደላባቸው ነገር ኣልነበረም። ይህን ነገር ታዲያ ቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንጦስ ሰዎችም ሆነ ለእኛ የእርሱ ተከታዮች ከእግዚኣብሔር ጋር መጓዝ በሁሉም ረገድ ትልቅ በረከት እንዳለው ያስረዳናል። ይህንን የእስራኤላውያኑን ታሪክ ስንመለከት እግዚኣብሔር በሁሉም ኣኳሃን ከጎናቸው በመሆን ኣብሮኣቸው ይጓዝ ነበር በችግራቸው ጊዜና የእርሱ እርዳታ ባስፈለጋቸው ጊዜ ሁሉ ከእነርሱ ጋር ኣብሮኣቸው ይቆም ነበር እንግዲህ ዛሬ ይህ  ታሪክ የሚያስተላልፍልን መልዕክት እግዚኣብሔር ለእርሱ ለታመኑት ዘወትር የሚያስፈልጋቸውን ነገር በሙሉ እንደሚሰጣቸው ከክፉ ሁሉ እንደሚጠብቃቸው በቀናዉም መንገድ ሁሉ እንደሚመራቸው ነው። እስራኤላውያኑ ግን በዚሁ ከእግዚኣብሔር ጋር በነበራቸው መልካም ግንኙነት ኣልቀጠሉበትም ምክንያቱም ልባቸው ሸፈተ እግራቸውም ከዳ። እግዚኣብሔር ከግብፅ ባርነት ኣውጥቶኣቸው በሚያስፈልጋቸው ነገር በሙሉ እየተንከባከባቸው እነርሱ ግን እርሱን ትተው ሌላ ጣዖትን ማምለክ ፈለጉ ዝሙትንም ፈፀሙ እግዚኣብሔር ኣምላካቸውን በእጅጉ ተፈታተኑት ኣሳዘኑትም። የእግዚኣብሔር ኣጋርነት ከእነርሱ በተለየ ጊዜ ብዙ ዓይነት መቅሰፍት ደረሰባቸው ኣብዛኞቹም በእባብ ተነድፈው እንደሞቱ ኦሪት ዘኁልቅ በምዕራፍ 25፣ 1-9 ላይ ይናገራል። እግዚኣብሔር ለእስራኤላውያን በብዙ መልኩ ፍቅሩንና ምሕረቱን ኣሳይቷቸዋል ጥበቃውንና እንክብካቤዉንም ኣብዝቶላቸዋል በመካከላቸውም አያሌ ተኣምራትንና ድንቅ ሥራዎችን ኣሳይቶቸዋል ነገር ግን እነሱ ለእግዚኣብሔር ታማኝ ለመሆን ኣልቻሉም ስለዚህ በራሳቸው ምርጫ ላደረጉት ድርጊትና ለመረጡት የተሳሳተ መንገድ እግዚኣብሔር ወደዘጋጀላቸው ወደ ተስፋይቱ ምድር ሊደርሱ ኣልቻሉም። ይህ እንግዲህ እንደ ሓዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ አመለካከት ለእኛ ለሁላችን ለቆሮንጦስ ሰዎችም ሆነ በዛሬ ጊዜ የክርስቶስ ተከታዮች ነን ብለን ለምንናገረው ትልቅ ትምሕርትና ማስጠንቀቂያ ነው ምክንያቱም እስራኤላውያኑ ከእግዚኣብሔር ትዕዛዝ በመውጣታቸው ከፍቃዱ ውጭ በመሄዳቸው የደረሰባቸውን ተመልክተናል እኛም ዛሬ እግዚኣብሔር ኣንድያ ልጁን በመላክ የሚያስፈልገንን ጸጋና በረከት ሰጠን በጸጋ ላይ ጸጋን ጨመረልን ወደ መንግሥተ ሰማይ የሚወስደውን መንገድ ኣሳየን ወደዛም ለመድረስ የሚያስችለንን ጉልበትም ሆነ ኃይል የሚሰጠንን ምሥጢራትን ኣደለን ከዚህ በኋላ ምርጫው የእያንዳዳችን ነው እርሱ ባሳየን መንገድ የምንራመድ ከሆንን እርሱ ባስተማረን ትምሕርት የምንመራ ከሆንን እርሱ ባደለን ምሥጢራት የምንጠቀም ከሆንን በስተመጨረሻ ወደ ተዘጋጀልን ወደ ኣዲሲቱ እየሩሳሌም ወደ ዘለዓለም ሕይወት እንገባለን ይህ ከልሆነ ደግሞ በራሳችን ምርጫ ራሳችንን ከዚህ ውጪ እናደርጋለን። አይሁዳውያን እኛ እኮ የኣብርሃም ዘር ነን የተመረጥን ነን ብለው ያስባሉ በዚህም ምክንያት ሁሌም ጸንተው የቆሙ ይመስላቸው ነበር። ቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ ግን የቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ እያለ ያስጠነቅቀናል ይህም ማለት እኔ የኣብርሃም ዘር ነኝ እኔ የጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ተከታይ ነኝ ማለቱ ለማንም ለምንም አይጠቅምም ምክንያቱም እንዲህ ዝም ብሎ በቃል ብቻ የኣብርሃም ዘር ነኝ የጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ተከታይ ነኝ ማለቱ ምንም ዋጋ ኣይኖረውም በተግባራችን በዕለታዊ ኑሮኣችን ኣብርሃምና ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የፈፀሙትን ያከናወኑትን መልካም ነገር ሁሉ መፈፀም ይኖርብናል። የእነሱን ኣብነት መከተል ስንችል ይህ ነው እውነተኛ የኣብርሃም ልጅ የጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ተከታይ የሚያሰኘን ለመንግሥተ ሰማይም የበቃን ኣዲስና ነጩን ልብስ ለመልበስ የሚያዘጋጀን።

በዛሬ በሁለተኛው ንባብ ቅዱስ ሓዋርያው ዮሓንስ በራዕዩ የእግዚኣብሔር መንግሥት ምን እንደሚመስልና በዙሪያውም ስለሚኖሩት ነጭ ልብስ ለብሰው እርሱን ስለሚያገለግሉት መላዕክት ይናገራል። ይህም የሚያመላክተን ጉዳይ ሁላችንም በዚህ በምድራዊ ሕይወታችን እግዚኣብሔር በሰጠን ቃል ተመርተን የእርሱን መንገድ ተከትለን የእግዚኣብሔር ክብርና ኃይል ወደሚገለፅበት ቅዱስ ዮሓንስ በራዕዩ ወዳመላከተን ቦታ ለመድረስ እንድንችል ከወዲሁ እንድናስብበትና ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በምናገኘው ጸጋ ኣማካኝነት ለተግባራዊነቱም የሚቻለንን ሁሉ በማድረግ ጥረታችንን እንድንቀጥል ነው። በዛሬው በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 12 ላይ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ሰንበት ሰለሰው ክብር ተሠራ እንጂ ሰንበት በራሱ ብቻ ከሰው ልጅ በላይ የሆነ ነገር እንዳልሆነ ተናግሯል። በእስራኤላውያን ባሕል መሠረት በሰንበት ቀን ምንም ዓይነት ሥራ መሥራት ኣይቻልም እንዲህ ብለው ስለሚያምኑ ሓዋርያቶች ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ጋር በእርሻ መካከል ሲያልፉ ተርበው ነበርና እሸት እየቀጠፉ መብላት ጀመሩ በዚህም ሰበብ በኣይሁዳውያኑና በሙሴ ሕግ መምሕራን ሰንበትን እንደማያከብሩ ሰንበትን በመተላለፍ የሙሴን ሕግ በመፍረስ ተከሰሱ። ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ግን የሰው ልጅ ከሰንበትም በላይ መሆኑን ሊያስረዳቸው ፈልጎ ስለራሳቸው ንጉሥ ስለ ንጉሥ ዳዊት ኣሳሰባቸው ንጉሥ ዳዊት በተራበ ጊዜ ከካህናት በስተቀር መብላት ያልተፈቀደውን የተቀደሰ እንጅራ በላ ከእርሱም ጋር ለነበሩት ሰጣቸው። 1ኛ ሳሙ 21, 1-6 ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በሰንበት ቀን ማንም ሰው እንዲራብ ኣይፈልግም ማንም ሰው እንዲያዝን ኣይፈልግም እንደውም በኣንፃሩ ደስተኛ ሆኖ እግዚኣብሔርን እንዲያመሰግን ይፈልጋል ለዚህም ነው ሰው በሰንበት ቀን ለራሱም ሆነ ለእግዚኣብሔር ደስ የሚያሰኝ ሥራ እንዲሰራ በዛው መጠን ደግሞ ደስተኛ ሆኖ እንዲያሳልፍ ይህንንም ደስታ በዙሪያው ላሉ ወንድሞቹና እህቶቹ እንዲያጋራ የሚያስተምረን። ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ንጉሥ ዳዊት ህብስቱን በመብላቱ ካህናቱ ደግሞ በሰንበት ቀን መሥዋት ለማቅረብ የሚያደርጉት ያ ሁላ ውጣ ውረድ እንደ ሥራ ኣለመቆጠሩ የሰው ልጅ ለሰንበትም ጌታዋ መሆኑን ያመላክታል ኣሁን ደግሞ ከዳዊትም ሆነ ካካህናቱ የሚበልጥ እዚህ ኣለ ይላል እርሱ ሰንበትንም የፈጠረ ነውና በሰንበትም ላይ ሥልጣን እንዳለው ኣስቀምጧል። ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በሰንበት ቀን ዋና የሚፈልገው ነገር መልካም ሥራ መሥራትና ከክፉ ሥራ መራቅ ነው ምክንያቱም እግዚኣብሔር ደስ የሚሰኘው በንጹህ ልብ ለሰው በምናደርገው መልካም ሥራና ምሕረት እንጂ በሰንበት ዕለት ልባችን በክፋት ተሞልቶ በምናቀርበው መሥዋዕት ኣይደለም። በሰንበት ዕለት ሥራን ባለመሥታችን ብቻ በቤታችን ብንቀመጥ ደስተኛ ኣይሆንም ይልቁኑም የምሕረት ሥራዎችን ብናከናውን እርሱ ደስተኛ ይሆናል እኛም በረከትን እናገኛለን።

በዚህ በተመሳሳይ ወንጌል ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በሌላ የሰንበት ቀን የሽባዉን እጅ በመፈወሱ ኣይሁዳውያኑ በእርሱ ላይ በጣም ተቆጡ ሊገድሉት የሚችሉበትንም ነገር ማሰላሰል ቀጠሉ ይህም ማለት ኣይሁዳውያኑ የሚያምኑት መልካም ነገር ምንድን ነው የሚለዉን ነገር በመጠየቅና በማመዛዘን ሳይሆን በቃ ሕግ ሕግ ስለሆነ ብቻ ቢጠቅምም ቢጎዳም መከበር ኣለበት የሚለውን ነው እርሱ ግን ይህ ትክክል የሆነ ኣካሄድ እንዳልሆነ ለማሳየት በዚህ ጉዳይ የበለጠ ሊከሱት እንደተዘጋጁ ቢያስተውልም የእጀ ሽባውን እጅ ከመፈወስ ወደ ኋላ ኣላለም። እነዚህ ኣይሁዳዉያን በሰንበት ቀን እሸት ቀጥፎ መብላት ሰውን ከተለያየ ደዌ መፈወስ በሞት የሚያስቀጣ ወንጀል መሆኑን ኣጥብቀው ይናገሩ እንጂ ከእነርሱ መሃል ኣንዱ የገዛ በጉ በሰንበት ቀን በጉድጓድ ቢገባ ያልምንም ጥርጥር ያወጣዋል ይህንን በማድረጋቸው ግን ሕግን መተላለፍ ተደርጎ ኣይቆጠርባቸውም እንግዲ ይህንን ማስመሰላቸውን ነው ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የኮነነው በሰው ፊት በገሃድ እንዲታይ ያደረገው ስለዚህ እነርሱ እርሱን ለማጥፋት የጀመሩት ሥም የማጠልሸት እርምጃ እውነትም እርሱ የሚናገረው ነገር የተሳሳተ ስለሆነ ኣልነበረም ወይንም ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ እውነትም እነርሱ እንደሚሉት ወንጀለኛ ስለሆነ ሳይሆን የእነርሱን የተሳሳተ ኣካሄድ በኣደባባይ በማጋለጡ ብቻ ነው በሚያከብረን ማኅበረሰብ ውስጥ ኣሳጣኸን ከሚል ተራ ኣስተሳሰብ በመነሳት ነው። ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በሰንበት ቀን መልካም ስለመሥራት መልካም ስለማሰብ ሲያስተምር ኣይሁዳውያኑ ግን በዚሁ በሰንበት ቀን እንዴት ኣድርገው እርሱን እንደሚያጠፉት ይማከሩ ነበር ይህን ነው እግዚኣብሔር የማይፈልገው ምሕረትን እንጂ መሥዋዕትን ኣልፈልግም የሚለው። ሰው መልካም ሥራ ሲሰራ በእርሱ ላይ ማመጽ ክፋት ማሰብ በእርግጠም ሰይጣናዊ ኣስተሳሰብ ነው ቢቻል እርሱንና ሓሳቡን በመደገፍ እኛም እንደእርሱ ለመሆን እርሱን ለመምሰል ጥረት ማድረግ ሲገባ በኣፃሩ ግን ክፋትን ማሰብ እርሱን ለማጥፋት ማሴር በእርግጥም ከሰይጣን የሚመነጭ ክፉ ሓሳብ ነው። ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ግን በየዕለቱ ከእስራኤል ዙሪያ ይመጡ የነበሩትን በጣም ብዙ በሽተኞችን ይፈውስ ነበር ኣጋንንት የያዛቸውን ሰዎች እርኩስ መንፈሱን ያስወጣላቸው ነበር ስለመልካምነትም ያስተምራቸው ነበር ምክንያቱም  ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ወደ እዚህ ምድር የመጣው የሰውን ልብ ለመቀየርና በመልካምነት ለመሙላት በዚህም መልኩ የሰውን ልጅ ሁሉ ለዘለዓላማዊ ሕይወት ሊያዘጋጀው ነው ነገር ግን ሁሌም ቢሆን የእኛ መልካም ፈቃድ ወሳኝነት ኣለው ምክንያቱም ልባችን እንደ ኣይሁዳውያኑ ከደነደነና ካለንበት የተሳሳተ መንገድ ተጸጽተን ካልተመለስን በገዛ እጃችን ዘለዓለማዊ ሞትን መርጠናል ማለት። ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ግን ይህ እንዲከሰት ኣይፈልግም ሁሌም ቢሆን ተስፋ ባለመቁረጥ በተቻለው መጠን እኛን ወደ ትክክለኛ መሥመር ለማምጣት በጸጋው ይጎበኘናል በበረከቱም ይሞላናል። እግዚአብሔር ምንም እንኳን ደካሞች ብንሆንም የልብ ቅንነት ያላቸውን ሰዎች ይወዳል ለተንኮል ራሳቸውን የማያዘጋጁትን ሰዎች ያቀርባል ለንስሃ የተዘጋጁትን ልቦች የፈውሳል ምስክሮቹም ያደርጋቸዋል። ስለዚህ እኛም ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ እንዳለው እንደ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በእግዚአብሔር ጸጋ በመታመን እንደ እርሱ ፈቃድ ለመኖርና ለመመላለስ በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር ምስክሮቹ ለመሆን እንድችል በረከቱን በልባችን ይሙላልን፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የክርስቲያኖች ረዳት የሆነች ጸጋና በረከቱን ከልጇ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ታሰጠን የሰማነውንም  የእግዚአብሔር ቃል በሕይወታችን ለመተርጎም እንድንችል ልባችንን ያነሳሳልን መንፈሳችንንም ያጠንክርልን።

31 October 2020, 20:15