በፊሊፒን የሚገኙ ምዕመናን በጸሎት ላይ ሆነው፤ በፊሊፒን የሚገኙ ምዕመናን በጸሎት ላይ ሆነው፤  

"ፊሊፒን ከደረሰባት ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ችግር እንድትወጣ መጸለይ ያስፈልጋል"!

የእስያ አገር በሆነች ፊሊፒን ሰላም እንዲወርድ፣ ከደረሰባት በርካታ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች እንድትወጣ በማለት ሦስት ሳምንት የሚቆይ የጸሎት ሥነ ሥርዓት እንዲካሄድ፣ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሶቅራጠስ ቪሌጋስ ጥሪ አቅርበዋል። ሊቀ ጳጳስ ቪሌጋ በማከልም “የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እርዳታ እያለ በችግር አንወድቅም” ብለዋል።

የቫቲካን ዜና፤

በፊሊፒን የሊንጋዬን-ዳጉፓን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሶቅራጠስ ቪሌጋስ ለምዕመናን ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት አገራቸውን እያጠቃ ያለው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንዲወገድ፣ አገራቸው ከሌሎችም ችግሮች እንድትወጣ በማለት የሦስት ሳምንት የጸሎት ሥነ ሥርዓት እንዲደረግ ማሳሰባቸው ታውቋል። የጸሎት ሥነ ሥርዓቱ የሚጀምረው የቀርሜሎስ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ በዓል ከሚከበርበት ከሐሙስ ሐምሌ 9/2012 ዓ. ም. ጀምሮ እስከ ረቡዕ ሐምሌ 29/2012 ዓ. ም.፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ ክብረ በዓል ድረስ፣ መሆኑ ታውቋል።

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሶቅራጠስ ቪሌጋስ፣ በአገሪቱ ብጹዓን ጳጳሳ ጉባኤ ማኅበራዊ መገናኛ ድረ ገጽ በኩል ሀገረ ስብከታቸው ካህናት በላኩት መልዕክታቸው፣ በአገራቸው ውስጥ የሚታየው የብቸኝነት እና የተስፋ መቁረጥ ስሜት፣ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለደረሰብን የጤና መቃወስ እና ለሌሎች ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች ፈጣን መፍትሄን ማግኘት የማንችል መሆናችንን ቢገልጽም፣ እንደ ሐይማኖት አባቶች፣ በችግር ውስጥ እንደሚገኙ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት በጸሎት መበርታት ይኖርብናል ብለዋል። በምንም ዓይነት መከራ ውስጥ ብንገኝም “የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እርዳታ እያለ በችግር ውስጥ አንወድቅም” ብለዋል።

ለሦስት ሳምንታት የሚቆየው የጸሎት ሥነ ሥርዓት ረቡዕ ሐምሌ 29/2012 ዓ. ም. በማናኦዋግ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ ውስጥ በሚካሄድ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ ሥርዓት የሚደመደም መሆኑ ታውቋል። በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በዕለቱ በሚደረገው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ የሀገረ ስብከቱ ካህናት፣ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት ብቻ የሚካፈሉ መሆናቸውን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሶቅራጠስ ቪሌጋስ አስታውቀዋል። ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ በቀጥታ የሚሰራጨውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ ሥርዓት ምዕመናን በማኅበራዊ ሚዲያዎች በኩል መከታተል የሚችሉ መሆኑን አስታውቀዋል። ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሶቅራጠስ ቪሌጋስ በመጨረሻም “በደረሱብን በርካታ ችግሮች ተስፋን ሳንቆርጥ፣ ወደ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ በመቅረብ፣ በእምነት የእርሷን እገዛ በጸሎት ልንማጸናት ይገባል” ብለዋል። 

16 July 2020, 18:27