ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ወቅታዊ ሁኔታዎችን አስመልክተው ያስተላለፉት መልእክት
ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን 49ኛው የጳጳሳት ጉባኤ መጠናቀቅን እና ወቅታዊ ሁኔታዎችን አስመልክተው ያስተላለፉት መልእክት
"ባልንጀራዬ ማን ነው?" (ሉቃ. 10፡29)
ለካቶሊካውያን ካህናት፣ ደናግል፣ ወንድሞች፣ እህቶች፣ ምእመናን እና በጎ ፈቃድ ላላቸው ሰዎች ሁሉ
ከሁሉ በማስቀደም የእግዚአብሔር ሰላም ከእናንተ ጋር ይሁን።
እኛ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ከሰኔ 29 እስከ ሐምሌ 3 በአዲስ አበባ ከተማ መደበኛ ጉባኤያችንን አድርገናል። በጋራ ሆነን ስለ ዓለማችን ስለ ሀገራችን ሕዝቦች ስለ እናንተ ካቶሊካውያን ልጆቻችን እንዲሁም ስለሰላም፣ ስለምሕረት ጸሎት ስናደርግ ቆይተናል። ይህንን ጉባኤያችንን ያከናውንነው ሁላችንንም ስጋት ውስጥ በጣሉን ሁለት ሀሳቦች አጣብቂኝ ውስጥ ሆነን ነው። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄድ እና የሃገራችን የጸጥታ እና የሰላም ችግር ልባችንን ከብደው ሀሳባችንን አስጨንቀው ይዘውናል።
የውይይታችን አጀንዳዎችም የቤተክርስቲያናችንን ሕይወት እና ሐዋርያዊ አገልግሎቶቻቸንን ከእነዚህ ሁለት አበይት ጉዳዮች ጋር በማያያዝ መመርመር ላይ ያተኮሩ ነበሩ። ምንም እንኳን እነዚህ ከባድ የሆኑ ፈተናዎች ከፊታችን ቢደቀኑም በእግዚአብሔር ያለን እምነት እና ተስፋ ጥልቅ ሰለሆነ “አይዞአችሁ አትፍሩ!” እንላችኋለን። ንስሀችንን እና ጸሎታችንን እግዚአብሄር ሰምቶ ክፉውን ሁሉ ከእኛ ያርቅልን። ራሳችንን እና ወገኖቻችንን ከዚህ ከክፉ ወረርሽኝ እንድንጠብቅ የተሰጡንን መመሪያዎች እንድናከብር እና ያለማሰለስ በተግባር እንድናውል አበክረን እናሳስባችኋለን። ሁኔታዎች ተስተካክለው ሁላችንም በነጻነት እና በደስታ ተሰብስበን በጋራ፣ በዕልልታ ማምለክ እስክንጀምር ድረስ በተስፋ ጸንተን በጋራ እንቁም።
ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እናንተ ልጆቿ በእምነት እንድትጸኑ ለማድረግ የተለያዩ ምቹ የሆኑ መንገዶችን በመጠቀም አገልግሎቷን ወደ እናንተ ለማድረስ ጥረቷን ትቀጥላለች። ካህናት እና ገዳማውያንና ገዳማውያት፣ ካቴኪስቶች በያላችሁበት ሁኔታው በፈቀደላችሁ መንገድ ሁሉ ሕዝባችንን እንድታጽናኑ ምስክርነትም እንድትሰጡ አደራ እንላችኋለን።
እኛ ጳጳሳት ሀገራችን ያለችበት የኢኮኖሚ፣ ማሕበራዊ እና ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ያሳስቡናል። የምናያቸው፣ የምንሰማቸው እና ያንዣበቡብን አደጋዎች የሰው ልጅ ሕይወት በከንቱ መጥፋት፣ የንብረት መውደም፣ የሰዎች መፈናቀል፣ የስደተኞች በተለይ ከውጭ ሀገር ከስደት የሚመለሱ ልጆቻቸን ሕይወት እንዲሁም ጾታዊ ጥቃት የሚደርስባቸው ህጻናት እና ሴቶች ጉዳይ በጥልቅ ያሳስቡናል። ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ዓለም አቀፍ ጉዳዮችም ሌሎቹ የሚያሳስቡን ወቅታዊ ሁኔታዎች ናቸው። አባይ እግዚአብሔር ለኢትዮጵያ የሰጣት ጸጋ ነው፡፡ የፈጣሪ ስጦታ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለጎረቤቶቿ ሁሉ፣ ግብፅን ጨምሮ፣ መልካሙን ትመኛለች፡፡ ወሮታዋን ከሰው ባትጠብቅም ከእግዚአብሔር እንደምታገኝ ታምናለች፡፡
እነዚህ ሁላችንንም ስጋት ውስጥ የጨመሩን ፈተናዎች በቀላል የማይታዩ እና ልዩ ጸሎት የሚሹ በመሆናቸው ካቶሊካውያን በሙሉ ሌት ተቀን በእግዚአብሔር ፊት ተደፍታችሁ እንድትጸልዩ በአባትነት ፍቅር እንለምናችኋለን። በተለይ በነሐሴ ወር በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ፍልሰታ ጾም፣ ጸሎትና ምህላ ወቅት ለኮሮና ወረርሽኝ፣ ለሀገራችን ሰላም እና ለሕዝቦች አንድነት ተግተን እንድንጸልይ እኛ አባቶች እናሳስባችኋለን።
በሀገራችን ጉዳይ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ በማስተዋል፣ በጥበብ፣ ቅንነት በተሞላበት፣ የሕዝብን ጥቅም፣ አንድነት እና አብሮነት ባማከለ መንገድ ውይይት እንዲያደርጉ በእግዚአብሔር እና በሕዝብ ስም ሆነን እንማጸናለን።
እኛ ካቶሊካውያን በእግዚአብሔር ባለን እምነት ተመስርተን እንዲሁም የቤተክትርስቲያናቸንን ማሕበራዊ አስተምህሮ ይዘን በማሕበረሰቡ ውስጥ እንደ ጨው ጣፍጠን እንደ ሻማ በርተን ለሌሎች መልካም ምሳሌ የሚሆን ሕይወት መኖር ይጠበቅብናል።
ከማንኛውም የሰውን ልጅ መለኮታዊ ክብር ከሚነኩ ሃይማኖታዊም ሆኑ የብሔር አጀንዳዎችን ከማራመድ ሁላችንም መቆጠብ ይጠበቅብናል። የሰው ልጅ ሁሉ እኩል ክብር ያለው በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ ስለሆነ እንደራሳችን አድርገን እንድንወድደው መለኮታዊ ትዕዛዝ ተቀብለናል። በተለይ የተጎዱትን፣ የተቸገሩትን እና በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ለችግር የተጋለጡትን ወይንም በሰላም እጦት ምክንያት ቤተሰቦቻቸውን በሞት የተነጠቁትን፣ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉትን እንዲሁም ስደተኞችን እና ከስደት ተመላሽ ወገኖቻችንን በፍቅር ልንደግፋቸው ይገባል።
በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 10 የተጻፈውን የደጉ ሳምራዊ ታሪክ ሁል ጊዜ ልናስታውስ ይገባናል። ባልንጀራችን፣ ወንድማችን፣ እህታችን የእኛን ሃይማኖት የሚከተል፣ የወንዛችን ልጅ የሆነ እና ቋንቋችንን የሚናገረው ብቻ አይደለም። የሰው ዘር የሆነ ሁሉ ባልንጀራችን በመሆኑ ልክ እንደ ደጉ ሳምራዊ ችግር በደረሰበት ጊዜ ሃይማኖት፣ ዘር፣ ቋንቋ ሳንቆጥር ሰው በመሆኑ ብቻ ልንደግፈው፣ ልንረዳው፣ እምባውን ልናብስለት፣ ስብራቱንም ልንጠግን ይገባናል።
ሰለዚህ እኛ ካቶሊካውያን መልካም በሆነው ሁሉ በተለይ የሰው ልጆችን ሊያቀራርቡ በሚችሉ፣ የተጣሉትን በማስታረቅ፣ የተጎዱትን በመርዳት፣ የሰላም መሣሪያዎች በመሆን ለሀገራችን ሕዝቦች አንድነት እና ሰላም መልካም ምሳሌ በመሆን የበኩላችንን አስተዋጽዖ የማድረግ ትልቅ ኃላፊነት አለብን።
”የሕያው ወንጌል እናት፣ ለእግዚአብሔር ታናናሾች የደስታ ምንጭ የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለኛ ለልጆቿ ትለምንልን ፡፡ አሜን"፡፡ (የወንጌል ደስታ 288)
+ ካርዲናል ብርሃነየሱስ
ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን
የካቶሊካውያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት
ሐምሌ 2012 ዓ/ም አዲስ አበባ