የሐምሌ 12/2012 ዓ.ም ሰንበት ዘክረምት 3ኛ የቅ. ወንጌል አስተንትኖ የሐምሌ 12/2012 ዓ.ም ሰንበት ዘክረምት 3ኛ የቅ. ወንጌል አስተንትኖ 

የሐምሌ 12/2012 ዓ.ም ሰንበት ዘክረምት 3ኛ የቅ. ወንጌል አስተንትኖ

የእለቱ ምንባባት

1.      2ቆሮ 10፡1-18

2.    ያዕቆብ 3፡1-8

3.    ሐዋ. 28፡17-31

4.    ማቴ. 8፡1-34

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

የለምጻሙ መንጻት

ከተራራው በወረደ ጊዜም ብዙ ሕዝብ ተከተለው። እነሆ፤ አንድ ለምጻም ሰው ወደ ኢየሱስ ቀረበና ከፊቱ ተንበርክኮ እየሰገደለት፣ “ጌታ ሆይ፤ ብትፈቅድስ ልታነጻኝ ትችላለህ?” አለው። ኢየሱስም እጁን ዘርግቶ ዳሰሰውና፣ “ፈቃዴ ነው፤ ንጻ!” አለው። ሰውየውም ወዲያውኑ ከለምጹ ነጻ። ከዚያም ኢየሱስ፣ “መፈወስህን ለማንም አታውራ፤ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፤ ሙሴ ያዘዘውንም መባ አቅርብ፤ ይህም ምስክር ይሆንላቸዋል” አለው።

የመቶ አለቃው እምነት

ኢየሱስ ቅፍርናሆም እንደ ደረሰ አንድ የመቶ አለቃ ቀርቦ፣ እንዲህ ሲል ለመነው፤ “ጌታ ሆይ፤ አገልጋዬ ሽባ ሆኖ እጅግ በመሠቃየት ከቤት ተኝቶአል” አለው። ኢየሱስም፣ “እኔ መጥቼ እፈውሰዋለሁ” አለው።

የመቶ አለቃው ግን መልሶ እንዲህ አለ፤ “ጌታ ሆይ፤ ወደ ቤቴ እንድትገባ የሚገባኝ አይደለሁም፤ ነገር ግን ከዚሁ ሆነህ አንዲት ቃል ብቻ ተናገር፤ አገልጋዬም ይፈወሳል፤ እኔ ራሴ የምታዘዛቸው አለቆች፣ ለእኔም የሚታዘዙ የበታቾች አሉኝ፤ ከእነርሱ አንዱን፣ ‘ሂድ!’ ስለው ይሄዳል፤ ሌላውን፣ ‘ና!’ ስለው ይመጣል፤ አገልጋዬንም፣ ‘ይህን አድርግ’ ስለው ያደርጋል።”

ኢየሱስም በመልሱ ተደንቆ ይከተሉት ለነበሩት እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፣ ከእስራኤል መካከል እንኳ እንዲህ ያለ እምነት ያለው አንድ ሰው አላገኘሁም፤ እላችኋለሁ፣ ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ፤ በመንግሥተ ሰማይ ማእድ ዙሪያ ከአብርሃም፣ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር ይቀመጣሉ፤ መንግሥተ ሰማይ ተዘጋጅቶላቸው የነበሩት ግን ወደ ውጭ ወደ ጨለማው ይጣላሉ። በዚያም ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።”

ኢየሱስም መቶ አለቃውን፣ “ሂድ እንደ እምነትህ ይሁንልህ” አለው። አገልጋዩም በዚያች ቅጽበት ተፈወሰ።

ኢየሱስ ብዙዎችን መፈወሱ

ኢየሱስ ወደ ጴጥሮስ ቤት ጎራ ሲል የጴጥሮስ ዐማት በትኵሳት ታማ ተኝታ አገኛት። እጇን ዳሰሳት፤ ትኵሳቱም ለቀቃት፤ ተነሥታም አገለገለችው። በዚያ ምሽት በአጋንንት የተያዙ ብዙ ሰዎችን ወደ ኢየሱስ አመጡ፤ እርሱም መናፍስትን በቃሉ አስወጣ፤ በሽተኞችንም ሁሉ ፈወሰ። በዚህም ኢሳይያስ እንዲህ ብሎ የተናገረው ትንቢት ተፈጸመ፤

“እርሱ ደዌያችንን ተቀበለ፤

ሕመማችንንም ተሸከመ።”

የኢየሱስ ተከታይ ለመሆን ውሳኔ ይጠይቃል

ኢየሱስ ብዙ ሰዎች በዙሪያው ተሰብስበው ባየ ጊዜ ወደ ባሕሩ ማዶ እንዲሻገሩ አዘዛቸው። በዚህ ጊዜ አንድ የአይሁድ ሃይማኖት መምህር ወደ እርሱ ቀርቦ፣ “መምህር ሆይ፤ ወደምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ” አለው።

ኢየሱስም፣ “ቀበሮዎች ጕድጓድ፣ የሰማይ ወፎችም ጎጆ አላቸው፤ የሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት ቦታ የለውም” ሲል መለሰለት።

ደቀ መዝሙር የሆነ አንድ ሌላ ሰው ደግሞ፣ “ጌታ ሆይ፤ መጀመሪያ ሄጄ አባቴን እንድቀብር ፍቀድልኝ” አለው። ኢየሱስ ግን፣ “ሙታን ሙታናቸውን ይቅበሩ፤ አንተ ተከተለኝ” አለው።

ኢየሱስ ማዕበሉን ጸጥ አደረገ

ከዚያም ኢየሱስ ወደ ጀልባ ገባ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከትለውት ገብተው ሄዱ። ድንገት ኀይለኛ ማዕበል በባሕሩ ላይ ተነሥቶ ጀልባዪቱን እስኪሸፍን ድረስ አወካቸው፤ በዚህ ጊዜ ግን ኢየሱስ ተኝቶ ነበር። ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው ቀሰቀሱትና፣ “ጌታ ሆይ! ጠፋን፤ አድነን” አሉት።

ኢየሱስም፣ “እናንተ እምነት የጐደላችሁ፤ ለምን ይህን ያህል ፈራችሁ?” አላቸው፤ ከዚያም ተነሥቶ ነፋሱንና ማዕበሉን ገሠጸ፤ ወዲያውም ጸጥታ ሰፈነ። ሰዎቹም፣ “ነፋስና ባሕር እንኳ የሚታዘዙለት፣ ይህ እንዴት ያለ ሰው ነው?” እያሉ ተደነቁ።

ከርኩሳን መናፍስት ስለ ተፈወሱ ሁለት ሰዎች

ባሕሩን ተሻግሮ ጌርጌሴኖን ወደሚባል አገር እንደ ደረሰ፣ አጋንንት ያደሩባቸው ሁለት ሰዎች ከሚኖሩበት የመቃብር ቦታ ወጥተው ተገናኙት። በዚያ መንገድ ሰው ማለፍ እስከማይችል ድረስ እጅግ አደገኞች ነበሩ። እነርሱም “የእግዚአብሔር ልጅ ሆይ፤ ከእኛ ምን ጕዳይ አለህ? ጊዜው ሳይደርስ ልታሠቃየን መጣህን?” እያሉ ጮኹ።

ከእነርሱ ትንሽ ራቅ ብሎ፣ የብዙ ዐሣማ መንጋ ተሰማርቶ ነበር። አጋንንቱም ኢየሱስን፣ “የምታስወጣን ከሆነ ዐሣማዎቹ መንጋ ውስጥ እንድንገባ ፍቀድልን” ብለው ለመኑት። ኢየሱስም፣ “ሂዱ!” አላቸው። አጋንንቱም ከሰዎቹ ወጥተው ዐሣማዎቹ ውስጥ ገቡ፤ ዐሣማዎቹም በሙሉ ከነበሩበት አፋፍ እየተጣደፉ ባሕሩ ውስጥ በመግባት ውሃው ውስጥ ሰጥመው ሞቱ። የዐሣማዎቹ ጠባቂዎችም ሸሽተው ወደ ከተማ በመሄድ፣ የሆነውን ሁሉና በአጋንንት ተይዘው በነበሩት ሰዎች ላይ የተደረገውን ነገር አወሩ። እነሆም፤ መላው የከተማ ነዋሪ ኢየሱስን ለመገናኘት ወጣ፤ ባዩትም ጊዜ አገራቸውን ለቅቆ እንዲሄድ ለመኑት።

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

“እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ቸርነትህ መጠን፣ ምሕረት አድርግልኝ፤ እንደ ርኅራኄህም ብዛት፣መተላለፌን ደምስስ” (መዝ. 51:1)።

የተወደዳችሁ የእግዚኣብሔር ቤተሰቦችና በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ።

ባሳለፍነው ሳምንት ውስጥ ለእለታዊ ኑሮዋችን አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን በመሥራት፣ ለራሳችንና እና ለቤተሰቦቻችን አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ስናከናውን ቆይተናል። በዚህም ውጣ ውረድ ውስጥ በአጋጣሚ ይሁን ሆን ብለን እህት ወንድሞቻችንን ያስቀየምንባቸው፣ የበደልናቸው ወቅቶች እንደ ሚኖሩ እሙን ነው። ለእዚህ ነው ታዲያ የዛሬው እለት ሰንበት አስተንትኖዋችን “እግዚኣብሔር ሆይ ምህረትህን አድርግልኝ” በሚለው በዳዊት የመማጸኛ ጸሎት የጀመርነው። ዳዊት በእዚሁ በመዝሙር 51 ላይ በቅንነት እንዲያገለግል የሰጠውን የእግዚኣብሔር ሕዝብ በመበደሉ የተነሳ እግዚኣብሔር ምሕረት እንዲያደርግለት ሲማጸን እንሰማለን። በእዚሁ ምዕራፍ ውስጥ ዳዊት ምሕረት፣ የማይናወጥ ፍቅር፣ ታላቅ ርኅራኄ፣ ደምስስ፣ እጠብ፣ አንጻ፣ መተላለፍ፣ በደል፣ ኅጢአት የሚሉትን ቃላት በተደጋጋሚ ሲጠቀም እናያለን።

ከበደሉ ሁሉ እግዚኣብሔር ያነጻው ዘንድ ዳዊት ከፍተኛ የሆነ ሮሮ ወደ እግዚኣብሔር እንዳቀረበ ሁሉ እኛም በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ከሠራነው ኅጢአት ያነጻን እና ያጥበን ዘንድ ወደ እግዚኣብሔር መጮኽ ይገባናል። “ሰማይ ከመሬት ከፍ እንደ ሚል” ሐሳቡ ከሐሳባችን መንገዱ ከመንገዳችን ልዩ የሆነው እግዚኣብሔር በምሕረቱ ይጎበኘን ዘንድ በርትተን ልንጸልይ ይገባናል ማለት ነው።

በዛሬው እለተ ሰንበት እኛ እንድናስተነትንበት ቤተክርስቲያናችን የሰጠችን የእለቱ ምንባባት በቀዳሚነት የተወሰደው (2ኛ ቆርጦንስ 10:1-18) ላይ የተወሰደው ጳውሎስ ሰለአገልግሎቱ ያቀረበው መከላከያ የሚያመልክት ሲሆን ጳውሎስ በዚሁ መልእክቱ “ጌታ በሰጠኝ ሥልጣን እጅግ ብመካም በዚህ አላፍርም፤ ሥልጣኑን የተቀበልነው እናንተን ለማነጽ እንጂ ለማፍረስ አይደለምና” በማለት እኛ ክርስቲያኖች ይነስም፣ ይባዛም/ በቤተሰብ ውስጥ ይሁን በሥራ ቦታ የተሰጠንን ኃላፊነት ሰዎችን ለማነጽ እንጂ ለማፍረስ ማዋል እንደ ሌለብን ሐዋርያው ጳውሎስ ዛሬ ያሳስበናል።

በዛሬው እለተ ሰንበት በሁለተኛነት ለአስተንትኖ ይሆነን ዘንድ የተሰጠን የእግዚብሔር ቃል የተወሰደው (ያዕቆብ 3:1-8) ላይ የተጠቀሰው አንደበትን መግራት በሚል አርእስት የተቀመጠው ሲሆን “ፈረሶች እንዲታዘዙልን ልጓም በአፋቸው ውስጥ ስናስገባ፣ መላ ሰውነታቸውን መምራት እንችላለን። ወይም መርከቦችን ተመልከቱ፤ ምንም እንኳ እጅግ ትልቅና በኃይለኛ ነፋስ የሚነዱ ቢሆኑም የመርከቡ ነጂ በትንሽ መሪ ወደ ሚፈልገው አቅጣጫ ይመራቸዋል። እንዲሁም ምላስ ትንሽ የሰውነት ክፍል ሆና ሳለ በታላላቅ ነገሮች ትኵራራለች፤ ትልቅ ጫካ በትንሽ እሳት እንዴት ተቃጥሎ እንደሚጠፋ አስተውሉ፤ ምላስም እንደ እሳት ናት፤ በሰውነት ክፍሎቻችን መካከል የምትገኝ የክፋት ዓለም ናት፤ ሰውነትን ሁሉ ታረክሳለች፤ ደግሞም የፍጥረትን ሩጫ ታቃጥላለች፤ ራሷም በገሃነም ትቃጠላለች” የሚለው ነው። ይህም መልእክት ምንም እንኳን ሁል ጊዜ ምላሳችንን መቆጣጠር አስቸጋሪ የሆነ ነገር ቢሆንም ቅሉ፣ ምላሱን የሚቆጣጠር ፍጹም የሆነ ሰው ካለ ግን ያሰው ሕይወቱን መቆጣጠር ይችላል ማለት ነው። ከምላስ የሚመነጭ ክፉ ነገር፣ ሁልጊዜም ቢሆን ምንጩ ዲያቢሎስ ነው። በምላሳችን እግዚኣብሔርን እናመሰግናለን፣ በምላሳችን ለእግዚኣብሔር እንዘምራለን፣ በምላሳችን ሰዎችን እናወድሳለን፣ በተቃራኒው ግን በምላሳችን ብዙ ክፉ የሚባሉ ነገሮችን እንናገራለን።

ለዚህም ነው እንግዲህ ነብዩ ኢሳያስ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ይህ ሕዝብ በአፉ ወደ እኔ ይቀርባል፤ በከንፈሩም ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው፤ የሚያመልከኝም፣ ሰው ባስተማረው ሰው ሠራሽ ሥርዐት ብቻ ነው” (ኢሳያስ 29:13) በማለት እግዚኣብሔር በሰው ልጆች የይስሙላ ተግባር እንዳልተደሰት ይናጋራል። በዛሬው ሰንበትም አንደበታችንን መግራት የሚያስችለን ጥበብ እግዚኣብሔር ይሰጠን ዘንድ ልንማጸን ያስፈልጋል፣ ምክንያቱ አንደበታችን ሁል ጊዜም ከሰው ጋር ያጋጨናል፣ ከእግዚኣብሔርም እንድንርቅ ያደርገናልና።

በዛሬው ወንጌል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታላቅ ተአምራትን ሲያከናውን እንመለከታለን፡፡ ተአምር ማለት አስደናቂ፣ ያልተለመደ፣ ከእዚህ በፊት አይተነው የማናውቀው ነገር ወይም ሥራ ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ በብሉይ ኪዳን ለሕዝቡ ማንነቱን ለማሳየትና ለማስተማር የተለያዩ ተአምራትን አድርጓል፡፡ ለምሳሌም በሙሴ በእያሱ በኤልያስ በመሳሰሉት ነብይት ተአምራትን አሳይቷል፡፡ በአዲስ ኪዳንም ጌታችንን መድኃኒታችን ብዙ ተአምራትን እንዳደረገ አይተናል፡፡ ለምሳሌ በእናታችን ምልጃ ውሃን ወደ ወይን ጠጅ ለወጠ ፣ በውሃ ላይ ተራመደ ፣ ንፋስን ፀጥ በማድረግ ስልጣኑን አሳየ፡፡ አጋንትን አወጣ ፣ ሰዎችን ከብዙ ደዌዎችና በሽታዎች ፈወሰ፡፡ ሦስት ሰዎችን ከሞት አስነሳ፡፡ ተአምራዊ ስራዎቹ እጅግ ብዙ ናቸው፡፡

የሰው ልጅ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ የማይገጥመው የኑሮ ውጣውረድ ፣ የኑሮ ማዕበል ውሽፍርና ሞገድ የለምና የዚህ ዓይነት መከራ በራሱም በቤተሰቡም ይመጣበታል ፤ በሽታ ፣ ችግር ፣ የኑሮ ውድነት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የሰው ልጅ በእነዚህ ችግሮች ሲወድቅ ሊመካበት ችግሩን ሊቋቋምበት የሚችልበትን ሀብት ፣ወገን ሊሻ የግድ ይለዋል፡፡በዚህ ወቅትም የራሱ ወገንም ሆነ ሀብት ይሸሹታል በዚህ ችግር ወቅት አይዞህ ባይ፣ በርታ ባይ ያስፈልገዋል፡፡ በዚህ ችግር ወቅት አይዞህ ባይ በርታ ባይ ሲያጣ ተስፋ ይቆርጥል ፤ ራሱንም ይጠላና ራሱን ለማጥፋት ያስባል፣ ምክንያቱም በዚህ ችግርና መከራ ውስጥ አይዙህ ባይ ከማጣቱም ባሻገር የራሱ የሆነ ጉልበት ሁሉ ይክደወል፡፡

ታዲያ ለዚህ መድኃኒቱ ምን ሊሆን ይችላል? ምንም ቢባል መልሱ አንድና አንድ ብቻ ነው፡፡ የሰናፍጭ ቅንጣት የምታክል እምነት ካለን በቂ እንደሆነ፣ ንፋስ እና ባሕርም የሚታዘዙለት ፤ ባሕሩንም ሞገዳችንንም ፣ ችግሮቻችንንም ፣ በሽታዎቻችንንም ሁሉ ፀጥ ለጥ ብለው የሚገዙለት አምላክ ከእኛ ጋር  ነውና ለእርሱ ችግሮቻችንን መናገር እና ማስረከብ ይኖርብናል።

ዛሬ ቀደም ሲል ሲነበብ የሰማችሁት ቅዱስ ወንጌል (ማቴ. 8:1-34) ላይ “በመጀመሪያ ከለምጽ ስለ ነጻ ሰው፣ በሁለተኛ ደረጃ የመቶ አለቃው የነበረውን ከፍተኛ እምነት እየሱስ ማድነቁ፣ በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ኢየሱስ ብዙ ሰዎችን መፈወሱን የሚገልጽ ምልእክት ያለው የወንጌል ክፍል ነው።

በዛሬው ቅዱስ ወንጌል ውስጥ በቅድሚያ ከለምጽ የነጻውን ሰው ታሪክ እናገኛለን፣ ለምጽ የሚለው ቃል በግሪክ ቋንቋ የሚያመለክተው የለምጽ በሽታን ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም ዓይነት የቆዳ በሽታን ያመለክታል። ይህ ለምጻም የነበረ ሰው ኢየሱስን በትህትና ቀርቦትና በፊቱ ተንበርክኮ “ጌታ ሆይ! ብትፈቅድስ ልታነጻኝ ትችላልህ?” በማለት ሲጠይቀው እንሰማለን።

በለምጻሙ ሰው እና በኢየሱስ መካከል በተደረገው ውይይት ውስጥ ሁሉት አስገራሚ እውነታዎችን እናገኛለን። በቅድሚያ ፈውስ የሚገኘው ሁሉን ቻይ በሆነው በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መልካም ፈቃድ ብቻ መሆኑን ያሳያል። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የዚህን ለምጻም ሰው እርግጠኛ፣ ጠንካራና ጽናት ያለው እምነት እናገኛለን።  የእኛ የሰው ልጆች ሕይወት በብዙ ነገሮች ውስጥ በእየለቱ ያልፋል። በበሽታ፣ በመከራ፣ በጭንቀት፣ የአእምሮ ረፍት በማጣት፣ የመሳሰሉት ነገሮች ሕይወታችንን እያመሱት ይገኛሉ። ስለዚህም የእግዚኣብሔር ፈውስ ያሻናል ማለት ነው።

በዛሬው ቅዱስ ወንጌል ውስጥ የተጠቀሱት ተአምራት ከለምጽ በሽታ ከተፈወሰው ሰው አንስቶ፣ የመቶ አለቃው አገልጋይ፣ የጴጥሮስ አማትና በተለያዩ እርኩስ መናፍስት ተይዘው የነበሩ ሰዎች የተፈውሱት የእግዚኣብሔር በጎ ፈቃድ እና እነዚህ ሰዎች በነበራቸው ጠንካራ እምነት የተነሳ መሆኑን ከዛሬው ቅዱስ ወንጌል ለመረዳት እንችላለን።

ታዲያ ይህንን የእግዚኣብሔር ፈውስ በምንሻበት ወቅቶች ሁሉ ይህ መሻታችን እውን ይሆን ዘንድ ቀደም ሲል የተጠቀሱትን ሁለት መስፈርቶች ሟሟላት ይገባናል፣ ሁሉን ቻይ የሆነውን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መልካም ፈቃድ መጠየቅና በእኛ በኩል ደግሞ ጠንካራና ጽናት ያለው እምነት ሊኖረን ያስፈልጋል ማለት ነው። በተለይም ደግሞ በጊዜው ትልቅ የሚባል ወታደራዊ ስልጣን የነበረው የመቶ አለቃ የነበረው ሰው በስልጣኑ ሳይመካ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝ እንደ ሆነ በማመኑና እርሱና ቤቱ ለጌታ የተገቡ አለመሆናቸውን በትህትና በመግለጹ የተነሳ ያሰበውና የጠየቀውን ፈውስ መግኘቱን ሰምተናል።

ሁል ጊዜም ቢሆን ራሳችንን ዝቅ አድርገን በእምነት  በጌታ ፊት በምንቀርብበት ጊዜ ሁሉ እርሱ የልባችንን መሻት የሰጠናል ማለት ነው።

ሁላችንም ኃጢአት በመሥራታችን የተነሳ የእግዚኣብሔር ክብር ጎሎናል። ለጌታ ክብር የተገባን አይደለንም። ብዙን ጊዜ እመነት ይጎለናል። በእመነታችን ጠንክረን፣ ከኃጢኣት ነጽተን፣ በምላሳችን ሳይሆን በሕይወታችን የእግዚኣብሔርን ክብር በመግለጽ የእርሱን ፈቃድ ፈጻሚዎች እንሆን ዘንድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በአማላጅነቷ ትርዳን። አሜን!

ምንጭ፡ የቫቲካን ሬዲዮ የአማርኛ አገልግሎት ክፍል

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

17 July 2020, 11:02