ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የደቡብ ሱዳን አብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች ተቀብለው ሲያነጋግሩ፤  ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የደቡብ ሱዳን አብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች ተቀብለው ሲያነጋግሩ፤  

የደቡብ ሱዳን አብያተ ክርስቲያናት የሰላም ጥሪያቸውን አቀረቡ፣

የደቡብ ሱዳን አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት በአገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች እየተቀሰቀሰ ያለውን አመጽ፣ ግድያን እና ንብረት መውደምን በመኮነን የሰላም ጥሪያቸውን ማስተላለፋቸው ታውቋል። ለዓመታት በተካሄደው የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት በርካታ የሰው ሕይወት የጠፋባት፣ ንብረት የወደመባት እና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎቿ የተፈናቀሉባት ደቡብ ሱዳን፣ ከአመጽ እና ከጦርነት በመውጣት ወደ ሰላም ጎዳና ለመግባት የምታደርገውን የአንድነት እና የሽግግር መንግሥት እያንዳንዱ ተቃዋሚ የፓለቲካ ፓርቲ እንዲደግፍ እና አመጾችን አቁመው ለሰላም እንዲቆሙ በማለት የደቡብ ሱዳን አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ጥሪውን አስተላልፏል።

የቫቲካን ዜና፤

“በአገሪቱ እየተፈጸመ ያለው ግፍ በእግዚአብሔር ፊት ተጠያቂዎች ያደርገናል” በማለት ድምጹን ያሰማው የደቡብ ሱዳን አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት፣ ባለፉት ቀናት በኬንያ መዲና ናይሮቢ በሚገኘው የምስራቅ አፍሪቃ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ዋና ጽሕፈት ተገኝቶ ባደረገው ስብሰባ ማጠቃለያ መሆኑ ታውቋል። የደቡብ ሱዳን አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት በመግለጫው እንዳስታወቀው፣ በአገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች እየተፈጸመ ያለው ጭካኔ የተሞላበት የግድያ እና የንብረት ማውደም ተግባር እንዲቆም አሳስቧል።

“ለዚህ የጭካኔ ተግባር ሃላፊነትን እንድንወስድ እግዚአብሔር ይጠይቀናል”፣

“በአገሪቱ የመፈጸሙ የጭካኔ ተግባራት በከፍተኛ ሐዘን ውስጥ እንድንገባ አድርጎናል” ያሉት የደቡብ ሱዳን አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት አባላት፣ ይህን የጭካኔ ተግባር እግዚአብሔር ተመልክቶት ሃላፊነትን እንድንወስድ ይጠይቀናል ብለዋል። የምክር ቤቱ አባላት አክለውም የጭካኔ ተግባሩ የሰው ሕይወት ቅድስናን ካለማወቅ የተነሳ ነው ብለዋል። የደቡብ ሱዳን አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ይህን ካስገነዘበ በኋላ፣ መንግሥት በየቦታው እየተካሄዱ ያሉ አመጾችን አስቁሞ በሕዝቡ መካከል እርቅ እና ሰላም የሚወርድበትን መንገድ እንዲያመቻች ጥሪውን አቅርቧል።

ፖለቲከኞች ለተፈረሙ ስምምነቶች ታማኝ ይሁኑ፣

መንግሥት በደቡብ ሱዳን ውስጥ ተግባራዊ የሚሆን የተሻለ የሽግግር መንግሥት እና አንድነትን እንዲፈጥር እንጠይቃለን ያለው የደቡብ ሱዳን አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት በመግለጫው ሁሉም ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አስቸኳይ እርምጃን በመውሰድ በንጹሐን ዜጎች ላይ የሚደርስ ስቃይ እንዲያበቃ በማለት ጥሪውን አቅርቧል። በማከልም ለአገሩ ሕዝቦችም ባቀረበው ጥሪው፣ ሁላችንም በጋራ አገራችን አብረን በፍቅር ለመኖር የተጠራን የአንድ አገር ሕዝቦች በመሆናችን በሰላም ልንኖር ይገባል ብሏል። የአብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤቱ የፖለቲካ መሪዎች ከዚህ በፊት ለተፈረሙ የሰላም እና የእርቅ ስምምነቶች ታማኝ እንዲሆኑ አሳስቦ፣ የፖለቲካ መሪዎች ከግል ጥቅም እና ከፖለቲካ ስልጣን ይልቅ ለሕዝባቸው ሰላማዊ ሕይወት ቅድሚያን እንዲስጡ አሳስቦ፣ ባሁኑ ጊዜ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች የሚነሱ አመጾች ቆመው፣ የሰውን ሕይወት ማጥፋት እና ንብረት ማውደም ተግባር ቆሞ የክልል መንግሥታት ቢመሰረቱ በማለት ጥያቄውን አቅርቧል።

ንስሐ መግባት፣ ይቅርታን ማድረግ እና ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ ያስፈልጋል፣

የደቡብ ሱዳን አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ባስተላለፈው ጠንካራ መልዕክቱ፣ ንስሐ መግባት፣ ይቅርታን ማድረግ እና ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ ያስፈልጋል ብሎ በአገሪቱ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ለሕዝቡ ታማኝ በመሆን፣ የእርቅ አገልግሎታቸውን ዘወትር እንደሚያበረክቱ፣ ለአገራቸው ሰላም እና አንድነት በርትተው እንደሚሠሩ፣ የሰላም ተስፋ እንዳለ የሚያምኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።

እ. አ. አ. በ2005 ዓ. ም. የተቀሰቀሰው የእርስ በእርስ ጦርነት፣

በደቡብ ሱዳን ውስጥ ብሔራዊ አንድነትን ለማምጣት ያለመ የሽግግር መንግሥት የተቋቋመው ዘንድሮ የካቲት 14/2012 ዓ. ም. መሆኑ ይታወሳል። በአገሪቱ ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር እና በምክትላቸው ሪክ ማቻር ስምምነት የተጀመረው የሽግግር መንግሥት እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በ2011 ዓ. ም. የሰላም ጥረት ቢያደርግም ዘላቂነት ሳያገኝ መክሸፉ ይታወሳል። በደቡብ ሱዳን እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በ2005 ዓ. ም. የተቀሰቀሰው የእርስ በእርስ ጦርነት በጎሳዎች መካከል ከፍተኛ የሕይወት መጥፋትን፣ የንብረት መውደምን እና መፈናቀልን ያስከተለ መሆኑ ይታወሳል።

25 June 2020, 18:58