የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማሕበራዊ አስተምህሮ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማሕበራዊ አስተምህሮ 

ማሕበራዊ አስተምህሮ፣ ስብከተ ወንጌል እና ሰብዓዊ እድገት

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማሕበራዊ አስተምህሮ

ክፍል አስራ ሦስት

ማሕበራዊ አስተምህሮ፣ ስብከተ ወንጌል እና ስብዓዊነትን በማሕበርሰቡ ውስጥ ማስተዋወቅን በተመለከተ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት ጳውሎስ 6ኛ በጻፉት ሐዋርያዊ መልእክት የሚከተለውን ብለው ነበር።

“የቤተክርስቲያኗ ማህበራዊ አስተምህሮ ከስብከተ ወንጌል ጋር በተዋሃደ መልኩ የሚሰጥ የቤተክርስቲያኗ ዋና ተልእኮ ነው። የሰው ልጆችን ዕለታዊ ጉዳይ የማይመለከት ነገር የለም፣ - ፍትህ ፣ ነፃነት ፣ ልማት ፣ በሰዎች መካከል ስምምነት፣ ሰላም - ለስብከተ ወንጌል እንግዳ የሆኑ ነገሮች አይደሉም። እናም ስብከተ ወንጌል የሰው ልጆችን የግል እና ማሕበራዊ ሕይወት ከግምት ካላስገባ እና ቅዱስ ወንጌል የሚጠይቀውን የማሕበርሰቡን የጋራ ግዴታዎች ከግምት ውስጥ ካላስገባ በስተቀር የተሟላ የስብከት ወንጌል አግልግሎት ለመስጠት አዳግች ይሆናል፣ ስብከተ ወንጌል የሰው ልጆችን የግል እና ማሕበራዊ ሕይወት ከግምት ባስገባ መልኩ ሊሰጥ ይገባል” (Paul VI, Encyclical Letter Evangelii Nuntiandi, 29: AAS 68 (1976), 25)።

በዚህ መሰረት ማንኛውም ሐዋርያዊ የሆነ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት የተሟላ ሊሆን የሚችለው ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ የማሕበርሰቡን ነባራዊ ሁኔታ እና አውድ ከግምት ባስገባ መልኩ መሆን እንደ ሚገባው መናገራቸው ይታወሳል። 

በስብከተ ወንጌል እና በሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት መካከል ጥልቅ የሆነ ትስስር ወይም መሰተጋብር ያለ ሲሆን የዚህ ትስስር እና መስተጋብር መሰረት የሆነው ደግሞ “እግዚአብሔር ሰውን በራሱ መልክ ፈጠረው፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው” (ዘፍጥረት 1፡27) በማለት የሰው ልጅ ሲፈጠር በእግዚአብሔር መልክ እና አምሳል መሆኑን መጽሐፍ ቅዱሳችን ስለሚያስተምረን፣ እንዲሁም የሰው ልጅ በነፍስ እና በሥጋ ተዋቅሮ የተፈጠረ በመሆኑ የተነሳ ሁለንተናዊ የሆነ ሰብዓዊ እድገት ያስፈልገዋል። በወንጌል አስተምህሮ እና በሰው ሁለንተናዊ እድገት መካከል ጥልቅ የሆነ ትስስር አለ። በስብከተ ወንጌል እና በሰብዓዊ እድገት መካከል ያለው ጥልቅ ግንኙነት በተመለከተ እ.አ.አ. ከ1963-1978 ዓ.ም ድረስ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን 262ኛው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት ጳውሎስ 6ኛ እ.አ.አ 1976 ዓ.ም በላቲን ቋንቋ “Evangelii Nuntiandiበአማርኛው “ወንጌልን ማወጅ”  በተሰኘው ሐዋርያዊ መልእክታቸው በሰው ልጅ ሰብዓዊ አፈጣጠር እና በፈጣርዊ መካከል ጉልህ እና ጥብቅ የሆነ ትስስር እንዳለ በሚከተለው መልኩ ገልጸዋል።

“የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት የሥነ-ሰብ (anthropological) ቅደም ተከተል ግንኙነቶችን ያካትታል፣ ምክንያቱም ስብከተ ወንጌል የሚሰበክለት የሰው ልጅ ረቂቅ ፍጡር አይደለም ፣ ነገር ግን ለማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች የተጋለጠ ፍጡር ነው። እንዲሁም አንድ ሰው ፍጥረታት የተፈጠሩበትን እቅድ ከመዋጀት ወይም ከመበዤት እቅድ ለያይቶ መመልከት ስለማይቻል በዚህ የተነሳ እነሱ በሥነ-መለኮታዊ ቅደም ተከተል የተቆራኙ እና የተሰላሰሉ መሆናቸውን ያካትታል። የኋለኛው ዕቅድ የፍትሕ መዛባት ተጨባጭ ሁኔታዎችን መዋጋት እና ፍትህ እንደገና እንዲሰፍን ማድረግን ያካትታል። የቅዱስ ወንጌል ስርዓት ዋነኛ አካል የሆነውን ፍቅር ያጠቃልላል፣ አንድ ሰው ፍትህ እና ሰላም እውነተኛ በሆነ መንገድ እንዲሰፍን የማያደርግ ከሆነ፣ እውነተኛ የሆነ ሰብዓዊ እድገት እንዲመጣ የማያደርግ ከሆነ አዲሱን ትእዛዝ (ፍቅር) እንዴት ማወጅ ይችላል? ” (Paul VI, Encyclical Letter Evangelii Nuntiandi (ወንጌልን ማወጅ), 31: AAS 68 (1976), 26)።

ቤተክርስቲያን በክርስቶስ ከተመሰረተችበት ጊዜ አንስቶ እስከ ዛሬ ቀን ድረስ በተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ በመሳተፍ በተለይም ድምጽ ለሌላቸው ሰዎች ድምጽ በመሆን፣ በተለያዩ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ምክንያቶች የተነሳ  በሕዝቦች ላይ የሚደረሰውን ማኅበራዊ ጫና እና በደል በመቃወም ለዓለም ድምጽዋን ስታሰማ በመቆየቷ የተነሳ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በማኅበራዊ ጉዳዮች ውስጥ በቀጥታ ሰላማዊ በሆነ መልኩ የመሳተፍ ሕጋዊ እና ስነ-ምግባራዊ መብት እንዳለት በጥልቀት ተገነዘባለች። ይህ መብት የሚመነጨው ደግሞ የቤተክርስቲያኗ ማህበራዊ አስተምህሮ “እራሱ ትክክለኛ የቅዱስ ወንጌል ማብሰሪያ መሳሪያ በመሆኑ የተነሳ” (John Paul II, Encyclical Letter Centesimus Annus, 54: AAS 83 (1991), 860)፣ ሲሆን ሁል ጊዜም ከቅዱስ ወንጌል መልእክት እና ከማህበራዊ ሕይወት ግንኙነት የተወለደ ነው።

የካቶሊክ ቤተክርስትያን በማኅበራዊ ጉዳዮች ውስጥ ትስተፋለች ሲባል በአንድ ሀገር ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ ትገባለች ማለት እንዳልሆነ ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ ሲሆን፣ ነገር ግን በተለያዩ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ጫናዎች ምክንያት በሰው ልጆች ላይ የሚደርሱትን በደሎች፣ ኢፍታዊ ተግባሮች፣ በተለይም ደግሞ ዝቅተኛ እና ድኸ በሚባሉ የማኅበረሰብ ክፍሎ ላይ የሚደርሰውን በደል በመቃወም ለዓለም ድምጿን ታሰማለች ማለት እንደ ሆነ ልብ ሊባል ይገባል። በእዚህ ረገድ የቤተክርስቲያናችን ተልዕኮ አንድ እና አንድ ብቻ ነው፣ ቤተክርስቲያን በክርስቶስ የተመሰረተችው የመላእክት ጠባቂ ለመሆን ሳይሆን የሰው ልጆችን አቅፋ ደግፋ፣ በስነ-ምግባር ታንጸው እንዲኖሩ በማድረግ፣ የሕዝቡ ደስታ ደስታዬ፣ የሕዝቡ ለቅሶ ደግሞ ለቅሶዬ ወይም ሐዘኔ ነው በማለት ሕዝቡ በሰላም እና በደስታ እግዚኣብሔር የሰጥቸውን በረከት እየታቁዳሱ እንዲኖሩ ለማድረግ፣ በመጨረሻም የሰው ልጆችን ለእግዚኣብሔር መንግሥት የማብቃት መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ የሆነ ተልዕኮ እንደ ተሰጣት ይታወቃል። 264ኛው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በላቲን ቋንቋ “Sollicitudo Rei Socialis” በአማርኛው በግርድፉ ሲተረጎም “ማህበራዊ እንክብካቤ” በሚል አርእስት እ.አ.አ 1988 ዓ.ም ይፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ መልእክት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማሕበራዊ አስተምህሮ የምትሰጥበትን ምክንያት ሲያብራሩ “የቤተክርስቲያን ማህበራዊ አስተምህሮ ቤተክርስቲያኗ የቃል አገልግሎቷን እና የነቢይነት ሚናዋን የምታከናውንበት ልዩ መንገድ ነው” (John Paul II, Encyclical Letter Sollicitudo Rei Socialis, 41: AAS 80 (1988), 570-572) ማለታቸው ይታወሳል።

አዘጋጅ እና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

02 June 2020, 16:04