ሐሜት ተፈታታኝ እና መጥፎ የሆነ ተግባር ነው ሐሜት ተፈታታኝ እና መጥፎ የሆነ ተግባር ነው 

ሐሜት ተፈታታኝ እና መጥፎ የሆነ ተግባር ነው!

ሐሜት አብዛኛውን ጊዜአችንን በኃጢአት ላይ እንድንወድቅ ከሚያደርጉን ተፈታታኝና መጥፎ ተግባት መካከል አንዱ ነው፡፡ አፋችን ከተከፈተ አስቸጋሪ ነው፣ ባልንጀራችንን ሳናማ አናልፍም። “እገሌኮ የሌብነት፣ የምንዝርና ልማድ አለው። ደህና ሰው ይመስላል እንጂ ፈጽሞ ክፉ ሰው ነው። እንደዚህ ይላል፣ እንደዚህ ያደርጋል፣ ጠባዩ እያድርስ ነው። ዋጋ የሌለው ርካሽ ሰው ነው፣ ወዘተ …” እያልን ሥጋውን እንቦጭቀዋለን። በዚህ ዓይነት የባልንጀራችንን አመልና ገመና በማውጣት ስሙን እናጠፋለን፣ ያደረገውንም ያላደረገውንም እየጨማመርን እናማዋለን።

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ሐሜት ሰይጣን በሰዎች ልብ ውስጥ የሚዘራው እንክርዳድና መጥፎ ዘር ነው፡፡ የሐሜት ተቃራኒ ደግሞ “ባልንጀራህን እንደራስህ አድርገህ ውደድ” (ማርቆስ 12፡31) የሚለው የእግዚአብሔር ፍቅር ትዕዛዝ ነው። ይህ ኃጢአት አውቀነውና ፈቅደነው በሐቅም ፈልገነው የምናደርግው ቀላል ነገር ይመስለናለ። ባለንጀራችንን ግን እጅግ አድርገን እንጐዳበታለን፡፡ ለሰዎችም መሰናክልና እንቅፋት እንፈጥራለን፡፡ ሐሜት ስንናገር በሰዎች ፊት መጥፎ አብነትና እንቅፋት እየሆንን እግዚአብሔርን እናሳዝናለን፡፡ እርሱ ፊት የኃጢአት ዕዳ በራሳችን ላይ እንጨምራለን፡፡ ሐሜት እኛንም አጥብቆ ይጐዳናል ወደ ኋላም ይጐትተናል፡፡

ሐሜት ስንናገር የሚሰማን ሰው ምንም እንኳ ለጊዜው ዝም ብሎ ቢያዳምጠንም ቆይቶ ግን እኛን መጥላቱ የማይቀር ነገር ነው፡፡ “በማንም ሰው ላይ አትፍረዱ በእናንተም ላይ ይፈረድባችኋልና፡፡ እንዲሁም በምትሠፍሩበት መስፈሪያ ይሰፈርባችኋል” (ማቴ. 7፣1) እያለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስጠነቅቀናል፡፡ በባልንጀራችን ላይ ሥልጣን ያለው በበደሉም ሊፈርድ የሚችል አምላክ ብቻ ነው፡፡ እኛ በባልንጀራችን ላይ ሥልጣን የለንም፡ በክፋቱ ልንፈርድበት አንችልም፣ ብንፈርድበት ግን እግዚአብሔር በባልንጀራችን ላይ በፈረድነው ፍርድ ልክ በእኛ ላይ ይፈርድብናል፡፡

ይህም ብቻ አይደለም ሰውም በእኛ ላይ ይፈርድብናል፡፡ ምክንያቱም በራስህ ዓይን ውስጥ ያለውን ጉድፍ ሳታይ እንዴት በሌላው ሰው ዓይን ውስጥ ያለውን ጉድፍ ትመለከታለህ; ደግሞም “በአንተ ዓይን ውስጥ ያለውን ጉድፍ ሳታወጣ በሌላው ሰው ዓይን ላይ ያለውን ጉድፍ ላውጣልህ እንዴት ትለዋለህ” የሚል ወቀሳም ያስከትላል፡፡ ቀጥሎም “አንተ ግብዝ አስቀድመህ በአንተ ዓይን ውስጥ የለውን ምሰሶ ንቀል ከዚያ በኋላ በለላ ዓይን ውስጥ ያለውን ጉድፍ ለማውጣት አጥርተህ ታያለህ” (ማቴ. 7፣3-5) ይላል ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ፡፡

ሁላችን በእየራሳችን ያለብንን ክፋት ደብቀን የባልንጀራችንን እንናገራለን፡፡ እኛ በደል የሌለብን ንጹሐን መስለን ባልንጀራችን ግን ክፋት የተሞላ መስሎ ይታየናል፡፡ ምንም እንኳ ክፋታችን የላቀና የበዛ ቢሆን ተሰውሮ እንዲቀር እየጣርን የባልንጀራችን ክፋት ግን ምንም እንኳ አነስተኛ ቢሆን እንዲገለጥበት እንፈልጋለን፡፡ እንዴት ክፉዎችና ጨካኞች ነን ሐሜት እንግዲህ አምላክንና ሰውን የሚያጣላ ቆሻሻ ተግባር ነው፡፡

“ወንድሞቼ ሆይ! እርስ በርሳችሁ አትተማሙ፡፡ ሰውን የሚያማ በሰው ላይም የሚፈርድ ሕግን ያማል፡፡ በሕግም ላይ ይፈርዳል በሕግ ላይ ብትፈርድ ፈራጅ መሆንህ ነው እንጂ ሕግን ፈፃሚ አይደለህም” (ያዕ 4፣11) ይላል ቅዱስ ያዕቆብ፡፡ መጽሐፈ ምሳሌም “ሰዎች ፌዘኛውን ይጸየፉታል” (ምሳ. 24፣9) ይላል፡፡ ጥበበ ሰሎሞንም “ከሐሜትም አንደበታችሁን ተከላከሉ ቀስ ብለው የተናገሩት ነገር በከንቱ አይነገርምና እንደፍላጻም የሚወጋ ሐሰት የሚናገር አፍ ሰውነት ይጐዳልና፡፡ አንደበታችሁን ከሐሜት በመከልከል፤ በሕይወታችሁ እግዚአብሔርን በመሻት ለሞት አትቅኑ” (ጥበ.ሰሎ. 1፣11) እያለ ያስጠነቅቀናል፡፡ በዚህ ምክንያት ሐሜት ክፉና ወደ ኃጢያት አዘቅት የሚጥለን መጥፎ ክፉ አመል በመሆኑ ማሻሻልና መተው ይገባናል፡፡

እግዚአብሔር ምላሳችንን ለክብሩና ለእኛ ጥቅም ብሎ ነው የሰጠን እንጂ ለመጥፎ ነገር ብሎ አልፈጠራትም። ለጽድቅ እንጂ ለክፋትና ለኃጢአት መሥሪያ ብሎ አልሰጠንም። እንግዲህ ምላሳችንን ወደ ጥሩ አላማ እንመልሳት፣ በሐሜት አናበላሻት። ፈጣሪዋን እንድታመሰግንና እንድታከብር ባልንጀራችንን እንድታንጽ እኛንም ደግሞ እንድትጠቅመን እናድርግ። ቅዱስ ቶማስ ዘቫሊኖቨ አንድ ቀን አንዳንድ ትልልቅ ሰዎች በአፋቸው ሰውን ሊያሙ በጀመሩ ጊዜ “ሐሜትን ተው ወይም ደግሞ እኔ እናንተን ትቼ ሄዳለው” ብሎኋቸው እንደ ነበረ የገራል። እኛም እንደዚሁ ቅዱስ ሰው ከሐሜት እንራቅ ሌሎችም ሰዎች ሰውን እንዲያሙ አንፍቀድ።

17 June 2020, 18:51