አባታችን ሆይ ክፍል ሦስት አባታችን ሆይ ክፍል ሦስት 

ስትጸልዩም እንደ ግብዞች አትሁኑ

አባታችን ሆይ ክፍል ሦስት

“ስትጸልዩም እንደ ግብዞች አትሁኑ፤ ለሰው ይታዩ ዘንድ በምኩራብና በመንገድ ማዕዘን ቆመው መጸለይን ወዳሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል።  አንተ ግን ስትጸልይ፥ ወደ እልፍኝህ ግባ መዝጊያህንም ዘግተህ በስውር ላለው አባትህ ጸልይ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል” (ማቴ. 6፡5-6)።

ከዚህ ቀደም አባታችን ሆይ” በሚለው ጸሎት ዙርያ የጀመርነውን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በመቀጠል ዛሬ ደግሞ ምስጢር ብርሃን ታግዘን  ቀደም ሲል የጀመርነውን አስተምህሮ እንቀጥላለን።

በማቴዎስ ወንጌል ውስጥ የተጠቀሰው "አባታችን ሆይ" የሚለው ጸሎት በተራራው ላይ በተደርገው ስብከት ማዕከል ውስጥ ቁልፍ የሆነ ቦታ አለው (ማቴ. 6፡9-13)። እስከዚያ ድረስ ሁኔታውን እንመልከት፦ ኢየሱስ በውሃ አጠገብ ወዳለው ኮረብታማ ቦታ ወጣ፣ በዚያም ተቀመጠ። በዙሪያው ለእርሱ እጅግ ቅርብ የነበሩ የእርሱ ደቀ-መዛሙርት ከበውት ነበር፣ ከዚያም በመቀጠል ደግሞ ከተለያዩ ቦታዎች የመጡ የማይታወቁ እጅግ በጣም ብዙ ሰዎች ፊት ለፊቱ ቆመው ነበር። ይህን የመጀመሪያውን "አባታችን ሆይ!" የሚለውን ጸሎት የተቀበሉት/የተማሩት ከተለያዩ አከባቢዎች የተውጣጡ፣ የተለያየ ባሕሪ እና አቋም የነበራቸው የተቀላቀሉ የማኅበርሰብ ክፍል ሰዎች ነበሩ።

ቀደም ሲል እንደ ተጠቀሰው ቦታው (ኢየሱስ “አባታችን ሆይ” የሚለውን ጸሎት ያስተማረበት ኮረብታማ ቦታ ማለት ነው) በጣም ጠቃሚ የሆነ ጥልቅ ትርጉም አለው፣ ምክንያቱም ኢየሱስ “የተራራው ስብከት” (ማቴ. 5፡1-7,27) ተብሎ የሚጠራውን አስተምህሮ ያደረገው በዚህ ስፍራ በመሆኑ የተነሳ ነው። ኢየሱስ በዚያ (በተራራ ላይ ያደርገውን ስብከት) አጠቃላይ የመልእክቱን ይዘት መሠረታዊ ገጽታ ጭብጥ ያቀረባል። በቅድሚያ “በተራራ ላይ” ያደርገውን ስብከት በተዋበ መልኩ እንደ አንድ ተዋኒያን በመሆን በደስታ ያቀርበዋል። ኢየሱስ በእርሱ ዘመን የእርሱ ተከታይ በነበሩ ሰዎች እና በኛም ጭምር ደስተኛ እንድንሆን ይፈልጋል! እኛ ግን ለእነዚህ ነገሮች ከፍተኛ የሆነ ግምት ባንሰጥም በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዕን ናቸው፥ የዋሆች ብፁዕን ናቸው፣ የሚያስተራርቁ ብፁዓን ናቸው፥ ልበ ንጹሖች ብፁዓን ናቸው. . .ወዘተ የሚሉት መልእክቶች በቅዱስ ወንጌል ውስጥ ከፍተኛ ልውጥ እንዲከሰት ያደርጉ ቃላት ናቸው። ሁሌም ማፍቀር የምያስችል አቅም ያላቸው ሰዎች፣ ከዛሬ ጀመሮ እስከ መጨረሻው የታሪክ ሂደት ድረስ ሰላም እንዲፈጠር የሚተጉ ሰዎች ሁሉ የእግዚአብሔር መንግሥት ገንቢዎች ናቸው። ልክ ኢየሱስ እንደተናገረው ሁሉን ቻይ በፍቅር እና በይቅርታ ተሞልቶ የገለጠውን የእግዚአብሔር ምሥጢር ወደ ልብ ያመጡታል!

ይህ የመንደርደሪያ ሐሳብ ታሪክዊ የሆኑ እሴቶች በመሻር ቅዱስ ወንጌል በአዲስ መልክ ይገልጻል። አንድ ሕግ መሻር የለበትም፣ ነገር ግን ወደ መጀመርያው ቀድሞ ወደ ነበረው ትርጉሙ የሚመልሰው አዲስ ትርጓሜ ያስፈልገዋል። አንድ ሰው መልካም የሆነ ልብ ካለው፣ ለማፍቀር ዝግጁ ከሆነ እያንዳንዱ የእግዚአብሔር ቃል በመላበስ እስከ መጨረሻው ድረስ መጽናት ይኖርበታል። ፍቅር ምንም ዓይነት ወሰን የለውም ፦አንድ ሰው የትዳር ጓደኛውን፣ የጓደኛውን እና እንዲያውም አንድ ጠላት የሆነውን ሰው እንኳን ሙሉ በሙሉ በአዲስ አመለካከት ሊወድ ይችላል፡ እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በሰማያት ላይ ላለው አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፥ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ፤ እርሱ በክፎዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፥ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና” (ማቴ 5፡ 44-4)።

“ሁላችሁም በሰማያት ላይ ላለው አባታችሁ ልጆች ናችሁ!” የሚለው ሐረግ በዚህ በተራራው ላይ በተደርገው ስብከት ውስጥ የሚያንፀባርቅ ታላቁ ምስጢር ነው።

እነዚህ በማቴዎስ ወንጌል ውስጥ የተጠቀሱት ምዕራፎች (5 እና 6) የስነ-ምግባር ሁኔታዎችን የሚተነትኑ ንግግሮች ይመስላሉ፣ እነዚህን የመሰሉ አስገራሚ የሆኑ የስነ-ምግባር ባሕርያትን የምያነሳሳ ቢመስሉም፣ ነገር ግን ከዚህ ይልቅ እነዚህ ሁሉ ነገረ-መለኮታዊ ይዘት ያላቸው ንግግሮች ናቸው። ክርስቲያን መሆን ማለት ከሌላው የተሻለ ሆኖ ለመገኘት መትጋት ማለት አይደለም፣ ነገር ግን እንደ ሌሎች ሰዎች እርሱም ኃጢአተኛ እንደ ሆነ ማወቅ ማለት ነው። በቀላሉ ክርስቲያን መሆን ማለት በአዲስ መልክ በሚቃጠለው ቁጥቋጦ ፊት ለፊት ራሱን በሚገልጸው አምላክ ፊት በመቆም፣ በማይታወቅ ስሙ አማካይነት የሚታወቀውን  ማንነቱን በመግለጽ ልጆቹ ሁሉ “አባት” በሚለው መጠሪያ ስም እንዲጠሩት የሚጠይቃቸውን አምላክ የሚመለከት፣ በእርሱ ኃይል አማካይነት እንዲታደሱ ራሳቸውን የሚያዘጋጁ፣ በእዚህ መልካም ነገሮችን በተጠማው ዓለም ውስጥ የእርሱን መልካምነት የሚያንፀባርቅ የእርሱን መልካም ዜናን በመጠባበቅ ላይ ለሚገኙ ሰዎች መልካም ዜናውን ማብሰር የሚችል ሰው መሆን ማለት ነው።

ኢየሱስ "የአባታችን ሆይ" የሚለውን ጸሎት ያስተማረው በዚህ መንገድ ነው። እርሱ ይህንን ትምህርት ያስተማረው ከሁለት ቡድኖች ራሱን ባራቀ መልኩ ነው። በመጀመርያ ደረጃ ራሱን አስቀድሞ ከግብዞች ስያርቅ እንመለከታለ፣ ይህንን በተመለከተ ደግሞ እንዲህ ይላል፦ “ስትጸልዩም እንደ ግብዞች አትሁኑ፤ ለሰው ይታዩ ዘንድ በምኩራብና በመንገድ ማዕዘን ቆመው መጸለይን ይወዳሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል” (ማቴ. 6፡5) በማለት ስለ እነርሱ ይገልጻል። አንዳንድ በእግዚኣብሔር የማያምኑ ሰዎች ያለእግዚአብሄር ፀሎት ማድረግ የሚቻል የሚመስላቸው ሰዎች አሉ፣ ይህንንም የሚያደርጉት ከሰዎች ዘንድ አድናቆትን ለማግኘት ፈልገው ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የአንድ ክርስቲያን ጸሎት ከአባቱ ጋር በጣም በቅርበት ከሚገናኝበት ከራሱ ሕሊና የተሻለ ሌላ ተጨባጭ እና ታማኝ የሆነ ምስክር የለውም፣ ለዚህም ነው በቅዱስ ወንጌል ውስጥ ኢየሱስ አንተ ግን ስትጸልይ፥ ወደ እልፍኝህ ግባ መዝጊያህንም ዘግተህ በስውር ላለው አባትህ ጸልይ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል” (ማቴ. 6፡6) በማለት የተናገረው።

በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ኢየሱስ አረማዊያን ከሚጸልዩት የጸሎት ዓይነት ራሱን ስያርቅ እንመለከታለን፣ ይህንን በተመለከተ ደግሞ እንዲህ ይላል፦ እናንተ ስትጸልዩ  አንደ አረማዊያን ከንቱ ቃላትን በመደጋገም አትለፍልፉ [. . .] እነርሱ በመለፍለፋቸው ብዛት እግዚኣብሔር የሚሰማቸው ይመስላቸዋል” (ማቴ 6[7) በማለት የተናግረው በዚሁ ምክንያት ነው። እዚህ ላይ ኢየሱስ "አንጀት ለመብላት በማሰብ የሚደረጉ ጸሎቶችን” በተመለከተ በርካታ ጥንታዊ ጸሎቶች በተመስጦ ይደረጉ እንደ ነበር ለመግለጽ አስቦ የተናገረው ንግግር ነበር -እርግጥ ነው በእዚያን ወቅት የአንድ ጸሎት መለኮታዊ ይዘቱ የሚለካው “ለረዥም ጊዜ በተከታታይ የምስጋና ውዳሴዎችን በማቅረብ ነው” ተብሎ ይታሰብ ነበር። አንተ ግን በምትኩ በምትጸልይበት ጊዜ አንድ ልጅ አባቱን በሚቀርብበት አኳኋን ወደ እግዚኣብሔር በመቅረብ፣ ሳትለምነው በፊት ምን እንደ ምያስፈልግህ በምያውቀው አባትህ ፊት ሆነ ጸልይ” (ማቴ 6፡8) በማለት ይናገራል። በተጨማሪም "አባታችን ሆይ" የሚለውን ጸሎት በልባችን ውስጥ በዝምታ መጸለይ እንችላለን፣ ራሳችንን በእግዚአብሔር እይታ ውስጥ ማስገባት፣ የአባታችንን ፍቅር ማስታወስ እነዚህን ነገሮች በመፈጸም ይህንን ጸሎት በዝምታ መጸለይ በራሱ በቂ ነው።

የአምላካችንን የርሱን ሞገስ ለማግኘት ለእርሱ መስዋዕት ማቅረብ አስፈላጊ እንዳልሆነ ማሰብ በራሱ ምንኛ ጥሩ ነው! የእኛ አምላክ የሆነው እግዚኣብሔር እርሱ ከእኛ ምንም አይፈልግም፣ ነገር ግን እርሱ ከእኛ የሚፈልገው አንድ ነገር ቢኖር የእርሱ በጣም ተወዳጅ ልጆቹ የሆንን እኛ በጸሎት ሁልጊዜ ከእርሱ ጋር ለመገናኘት የምያስችለንን የመገናኛ መስመር ሁልጊዜ ክፍት እንድናደርግ ብቻ ነው የሚጠይቀን።

ምንጭ፡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራቸስኮስ በታኅሳስ 24/2011 ዓ.ም “አባታችን ሆይ” በሚለው ጸሎት ዙሪያ ላይ ካደረጉት ጸሎት የተወሰደ።

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ይህን ዝግጅት ለማዳመጥ ከእዚህ ቀጥሎ ያለውን "ተጫወት" የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
07 May 2020, 19:22