የመቁጠሪያ ጸሎት የመቁጠሪያ ጸሎት 

የመቁጠሪያ ጸሎት

በ1208 ዓ.ም. በአንዲት የፈረንሳይ አገር ከተማ ብርቱ መናፍቅነት ተነሳ። የቤተክርስቲያን ጠላቶች በጭካኔ ተነሳስተው ስትህተተኛ ትመህርታቸውን እየሰበኩ ገዳማትንና አብያተ ክርስቲያናትን አቃጠሉ፣ ካህናትን ገደሉ፣ መስቀሎችን ሰበሩ፣ መንፈሳዊ ቦታዎተችን እና መንበረ ታቦትን አረከሱ፡፡ ሕዝበ ክርስቲያን በዚህ አጸያፊ ድርጊት ተንቀጥቅጦ ወደ እግዚአብሔር ብርቱ ምህለላ አደረገ። ዶመኒኮስ የሚባል አንድ ቅዱስ እነዚያን የሃይማኖት ጠላቶች በስብከቱና በጸሎቱ ለመቋቋም ተነሳ። ነገር ግን ፍሬ አላገኘም። በዚህ ምክንያት አዝኖ ሳለ እመቤታችን ድንግል ማርያም በእጅዋ መቁጠሪያ ይዞ ታየችው። በዚያን ጊዜ እነዚያ መናፍቃን የሚሸንፉበት የጦር መሣሪያ “የመቁጠሪያ ጸሎት” መሆኑን ገለጠችለት። ቅዱስ ዶመኒኮስም ምክርዋን ተቀብሎ ብዙ የመቁጠሪያ ጸሎት ደገመ፤ ሌሎችም እንዲጸለዩ አስተማረ። በዚህ ከፍተኛ የመቁጸሪያ ጸሎት አስደናቂ የሆነ ተአምር በመታየቱ መናፍቃን ተሸንፈው ድል ተመቱ፡፡ በሺህ የሚቆጠሩ መናፍቃን ወደ ቅድስት ቤተክርስቲያን ተመለሱ፤ በሕዝበ ክርስቲያኑም መካከል ሰላም ሰፈነ።

የቫቲካን ዜና

እመቤታችን ድንግል ማርያም የመቁጠሪያ ጸሎት እንድናደርግ በመማጸን የመቁጠሪያ ጸሎት ትልቅ መሆኑን ለእኛም ከፍ ያለ ጸጋ የሚያስገኝ እግዚአብሔርንም የሚስደስትና ክብር የሚሰጠው ጸሎት መሆኑን አስረድታናለች። ስለዚህ ዘወትር እንድንደግመው ትመክረናለች።

መቁጠሪያ የሕዝበ ክርስቲያን ትልቅ ጸሎት ነው፡፡ ምክንያቱም ይህን  በገዛ ራሷ ፈቃድ የገለጠችው ታላቋ ቅድስት ድንግል ማርያም ናትና። እርሷ ከሥነ ፍጥረት ሁሉ በላይ ናት። እርሷ ራሷ የገለጠችልን ነው እንጂ ሌላ ሰው ወይ አንድ መልአክ፣ አንድ ቅዱስ የገለጠልን ጸሎት አይደለም። መቁጠሪያ ክቡር ጸሎት ነው፤ ምክንያቱም ይህ ጸሎት ከፍ ያለ የቤተክርስቲያን ጸጋ ያለበት ከመሆኑም በላይ ራሷ የአምላክ እናት የገለጠችልን ነው።

“ጸሎተ ሃይማኖት” ቤተክርስቲያን ያስተማረችን የጸሎት ዓይነት ሲሆን “ጸጋ የሞላሽ ማርያም” … የሚለውን ጸሎት ደግሞ ቅዱስ መልአከ ገብርኤልና ቅድስት ኤልሳቤጥ እንዲሁም ሊቃውንት ያስተማሩን ጸሎት ነው። “ስብሐት ለአብ …” “ሰላም ለኪ …”፣ “ሊጣንያ” … ፣ ቅድስት ቤተክርስቲያን ያስተማረችን ጸሎቶች ናቸው። በቅዱስ ገብርኤል ሰላምታ እመቤታችን ድንግል ማርያምን የምናከብርበትና የምንለምንበት ጸሎት ሲሆን “በሰማይ የምትኖር አባታችን …” በሚለው ጸሎት ደግሞ እግዚአሔርን እናመሰግንበታን እንለምንበታለን።

የመቁጠሪያ ጸሎት ቁም ነገር ብዙ በመሆኑ ታላቅ የሆነ ጸሎት ነው። የካቶሊካዊት ቤተክርስቱያን የበላይ አባት የነበሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ኡርባኖስ 4ኛ “በመቁጠሪያ ጸሎት አማካይነት በሕዝበ ክርስቲያን ላይ የቡራኬ ዝናም ይወርዳል” ማለታቸው ያታወሳል። እንዲሁም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮን 13ኛ በበኩላቸው “በዚያች የሰማይ ንግሥት የመቁጠሪያ ጸሎት አማካይነት ከፍ ያለ መንፈሳዊ ኃይል እንደሚገኝ ማመን አለብን” ብለዋል፡፡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 5ኛም “የመቁጠሪያ ጸሎት በዓለም ላይ መስፋፋት በጀመረበት ጊዜ ክርስቲያኖች በእርሱና በምስጢራት ጸሎትም በመጠቀም ኑሮአቸውን ሊውጠው የነበረውን የመናፍቃን ጨለማ ገፎላቸው የሃይማኖት ብርሃንም ፈነጠቀላቸው” ብለዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሲክስቶስ 4ኛ የተባሉ ደግሞ “እግዚአብሔርን እመቤታችን ድንግል ማርያምን የሚያስከብር የመቁጠሪያ ጸሎት ነው፤ ከዓለም መዓት፣ ቅጣትና መቅሰፍትንም የሚያስወግድው የመቁጠሪያ ጸሎት ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ስለ መቁጠሪያ ጸሎት ፍሬና ጥቅም ብዙ መናገር ይቻላል። የመቁጠሪያ ጸሎት ከእግዚአብሔር ጸጋንና ምሕረትን ያወርዳል የደኀንነት መሰላልም በመሆኑ በችግራችን ጊዜ ይረዳናል ብርታትንም ይሰጠናል። እነዚህን የመሳሰሉ ጥቅሞች ስላሉት እመቤታችን ድንግል ማርያም እነዚህን መንፈሳዊያን ጥቅሞች እንድናገኝና እንድንጠቀምባቸው አደራ ትለናለች። እ.አ.አ በ1916 ዓ.ም. በፖርቱጋል አገር ፋጢማ በሚባልበት ስፍራ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለሶስት እረኛ ለነበሩ ልጆች ስትታያቸው “ጦርነት አብቅቶአል። በዓለም ሰላም እንዲነግሥ በየቀኑ የመቁጠሪያ ጸሎት ድገሙ” እያለች ተማጥናለች። በመቀጠልም “መቁጠሪያ በመድገም የአምላክ ድጋፍና ዕርዳታ ከሰማይ ወደ ምድር ይወርዳል” ብላቸው ነበር።

የሮም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮን 13ኛ ስለ መቁጠሪያ ጸሎት ጥቅም ከተናገሩ በኋላ “እኛ ይህ መንፈሳዊ ጸሎት ዘወትር እየተስፋፋ እንዲሄድ ሕዝበ ክርስቲያንም ሁሉ በየቀኑ በሁሉም ስፍራ የሚደግመው ጸሎት እንዲሆን ፈቃዳችን ነው” በማለት በአደራ ጭምር መናገራቸው ይታወሳል። ስለዚህ የእመቤታችን የድንግል ማርያምንና የቤተክርስቲያንን አደራ በጥልቅ ስሜት ተቀብለን በተግባር እንድናውለውና የመቁጠሪያ ጸሎት ወዳጆች እንድንሆን ቁርጥ ፈቃድ እናድርግ። የመቁጠሪያ ጸሎት ሳንደግም አንዲት ቀንም እንኳ እንዳናሳልፍ እንወስን።

29 May 2020, 20:10