ግንቦት 6/2012 ዓ. ም. የዓለም ሕዝብ በጸሎት የሚተባበር ቀን መሆኑ ተገለጸ።

በመላው ዓለም የሚገኙ የልዩ ልዩ እምነት ተከታዮች በአንድ መንፈስ ሆነው ግንቦት 6/2012 ዓ. ም. በሚደርግ ዓለም አቀፍ የጸሎት ሥነ ሥርዓት የሚተባበሩ መሆኑ ታውቋል። ሁሉም የሐይማኖት ተቋማት በመተባበር፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያስከተለውን መከራ ማለፍ የሚቻልበትን ኃይል ከእግዚአብሔር የሚለምኑ መሆኑን ታውቋል። በዚሁ የጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከአምስቱም አህጉራት ከተወጣጡ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች እና ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር በጸሎት የሚተባበሩ መሆናቸው ታውቋል።

የቫቲካን ዜና፤

ግንቦት 6/2012 ዓ. ም. ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ቫይረስ የተጠቃው የዓለማችን ሕዝብ ወደ እግዚአብሔር ፈጣሪው ጸሎቱን የሚያቀርብበት ዕለት መሆኑ ታውቋል። የጋራ ጸሎቱ መላው ዓለም የስቃይ ድምጹን የሚያሰማበት እና ተስፋን የሚለምንበት መሆኑ ታውቋል። ግንቦት 6/2012 ዓ. ም. በመላው ዓለም የሚገኙ የልዩ ልዩ እምነቶች ተከታዮች እጅ ለእጅ ተያይዘው፣ በመንፈስ ተቀራረበው የሚያቀርቡት የጋራ ጸሎት አንድ እና ብቸኛ ጸሎት ይሆናል ተብሏል።

“የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያስከተለውን አደጋ የምንዋጋበት እና የምንቋቋምበት ዋና መሣሪያ ጸሎት ነው” በማለት ሃሳባቸውን በቪዲዮ ምስል የገለጹት የዓለም ሕዝቦች፣ ይህን አስጨናቂ ጊዜን ማስታወስ የምንችለው፣ አንድነታችንንም መግለጽ የምንችለው በሕብረት ስንሆን ነው ብለዋል። ቤተክርስቲያን መሆናችንን ለማወቅ፣ እርስ በእርስ ለመዋደድ በጋራ መጸለይ ያስፈልጋል፣ ተስፋ መቁረጥ የለብንም፣ በጋራ ስንቆም ማንኛውንም ሕመም እና ስቃይ ማሸነፍ ይቻላል በማለት ከዓለም ዙሪያ የተወጣጡ የልዩ ልዩ እምነት ተከታዮች በቪዲዮ ባሰራጩት መልዕክታቸው አስታውቀዋል።

ከጸሎት እና ከጾም በተጨማሪ ለጋስነትም ያስፈልጋል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ከተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት የተወጣጣ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ከፍተኛ ጽሕፈት ቤት አባላት ባቀረቡላቸው ጥያቄ መሠረት ግንቦት 6/2012 ዓ. ም. የዓለማችን ሕዝቦች በጸሎት የሚተባበሩበት ዕለት እንዲሆን መደረጉ ታውቋል። በሕብረት የሚደረግ የጋራ ጸሎት ዋና ዓላማ ዓለማችንን እያጠቃ የሚገኘውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እግዚአብሔር በኃይሉ እንዲያስወግደው በጸሎት የምንጠይቅበት፣ በቀጣዩ ዘመናችንም የወንድማማችነትን እና አብሮ የመኖር መልካም እሴቶቻችንን ለማሳደግ መሆኑ ታውቋል።

ይህን ዜና በድምጽ ማድመጥ ከፈለጉ የተጫወት ምልክትን ይጫኑ፣
13 May 2020, 14:10