እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ጸጥታን አስተማሪ፤ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ጸጥታን አስተማሪ፤  

አባ ኤሚሊያኖ “የምንገኝበት የጸጥታ ጊዜ የእግዚአብሔርን ድምጽ የምንሰማበት ጊዜ ነው”።

በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የበርካታ ሰዎች ሕይወት በመጥፋቱ በሐዘን እና በጸጥታ ውስጥ እንገኛለን ያሉት ፍራንችስካዊ ካህን አባ ኤሚሊያኖ አንተኑቺ፣ ይህ የጸጥታ ጊዜ ልባችን የእግዚአብሔርን ድምጽ የሚሰማበት ጊዜ መሆኑን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሚያዝያ 13/2012 ዓ. ም. ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያመጣውን የጸጥታ ጊዜ በመቀበል አንዱ ሌላውን የማድመጥ አቅማችንን ልናሳድግ ይገባል ብለው፣ በቀድሞ ክርስቲያኖች መካከል የነገሠውን የጸጥታ ጊዜን በማስታውስ ለመንፈስ ቅዱስ ዕድል ከሰጠነው አስደናቂ ነገሮችን ማድረግ ይችላል ብለዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም መንፈስ ቅዱስ ለክርስቲያኖች አንድት እንቅፋት የሆኑ ሦስት ነገሮችን፥ የገንዘብ ፈተናን፣ ኩራትን እና አሉባልታ ወሬን ማሸነፍ ይቻላል ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመስዋዕተ የቅዳሴ ጸሎት መጀመሪያ ላይ እንደገለጹት ባሁኑ ወቅት በዓለማችን ውስጥ ጸጥታ መንገሡ ይስተዋላል ብለው፣ በዚህ የጸጥታ ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር እና እርስ በእርስ መደማመጥ እንድንችል በርትተን መጸለይ ይገባል ብለዋል።  

“የጸጥታ ጎዞ” የሚል መጽሐፍ ደራሲ የሆኑት ክብር አባ ኤሚሊያኖ አንተኑቺ፣ የእራሳቸውን ሃሳብ ማሠረት በማድረግ የእግዚአብሔርን ድምጽ ለማድመጥ የሚያግዝ የትምህርት ዘርፍ መጀመሩ ታውቋል። ባለፈው ዓመት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር በቫቲካን ውስጥ የተገናኙት ክቡር አባ ኤሚሊያኖ አንተኑቺ፣ እርሳቸው የሳሉትን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዝምታ ገላጭ የመጀመሪያ ቅጂ ምስል ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በስጦታ ማቅረባቸው ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጣሊያን፣ አቬዛኖ ሀገረ ስብከት ውስጥ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መንፈሳዊ የንግደት ሥፍራ እንዲታነጽ በማለት ለክቡር አባ ኤሚሊያኖ አንተኑቺ ሐዋርያዊ ቡራኬአቸውን ሰጥተው ማሰናበታቸው ይታወሳል። የፍራንችስካዊያን ታናናሽ ወንድሞች ማኅበር አባል የሆኑት ክቡር አባ ኤሚሊያኖ አንተኑቺ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንደገለጹት፣ ጸጥታ ከእግዚአብሔር ጋር መነጋግር እንድንችል ዕድል የሚሰጥ የመግባቢያ ቋንቋ ነው ብለው፣ አሁን የምንገኝበት ወቅትም ከእግዚአብ|ሔር ጋር በመነጋገር ለውጥን የምናመጣበት ጊዜ ነው ብለዋል።

ይህ የምሕረት እና የጸጥታ ጊዜው በሕይወታችን ውስጥ ለውጥን ለማምጣት ምቹ አጋጣሚ መሆኑን አባ ኤሚሊያኖ አንተኑቺ አስረድተዋል። በሐዘን የተዋጠ ጸጥታን ያስታወሱት አባ ኤሚሊያኖ፣ ከዚህም አልፎ ተርፎ የልብ ጸጥታም አለ ብለዋል። “የእግዚአብሔርን ድምጽ ማድመጥ ይኖርብናል” ያሉትን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስብከት ያስታወሱት አባ ኤሚሊያኖ፣ የእግዚአብሔርን ድምጽ በማድመጥ አስጨናቂውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጊዜ ተሻግረን ወደ ትንሳኤ የምንደርስበትን መንገድ ማግኘት እንችላለን ብለዋል። “ዛሬ የምንገኝበት ጸጥታ በእውነት አስደንጋጭ ነው” ያሉት አባ ኤሚሊያኖ በዚህ የጸጥታ ጊዜ እግዚአብሔርን እና ራሳችንም ማድመጥ ያስፈልጋል ብለዋል። ጸጥታ እውነት መሆኑንና በጸጥታ መቀመጥ ከባድ እንደሆነ ያስረዱት አባ ኤሚሊያኖ ቢሆንም ጸጥታ የእግዚአብሔር የመግባቢያ ቋንቋ ነው ብለው፣ ወደ ውስጣዊ መንፈሳዊነት የሚወስደን ፈጣን መንገድ መሆኑንም አስረድተዋል።

በእውነት ላይ ያልተደገፈ አሉ ባልታ ወሬ የሌላን ሰው መልካም ስም ሊያጎድፍ እንደሚችል ያስረዱት አባ ኤሚሊያኖ እኛም እውነት የሌለበት ወሬ ስናወራ የሌሎችን መልካም ስብዕና እናጎድፋለን ብለዋል። የውሸት እና የአሉባልታ ወሬ ጠንሳሽ፣ በቤተክርስቲያን፣ በቤተስብ እንዲሁም በማኅበረሰብ መካከል ልዩነትን የሚዘራ እርሱም ሰይጣን እንደሆነ እናውቃለን ብለዋል። በዚህ ወንጀል የምንሸነፍ ከሆነ የሰይጣንን ተልዕኮ እንፈጽማለን ብለዋል። ንግግራችን “አዎ ከሆነ አዎ፣ አይደለም ከሆነ አይደለም” መሆን አለበት ብለው፣ ለሰዎች የተስፋ እና የመጽናናት ቃል መናገር እና መባረክ እንጂ መርገም የለብንም ብለዋል።

ጸጥታ ከእግዚአብሔር ጋር በጸሎት ለመገናኘት ያዘጋጀናል ያሉት ክቡር አባ ኤሚሊያኖ፣ ጸጥታ የእግዚአብሔር ቃል የሚፈልቅበት ምንጭ ነው ብለዋል። እናታችን ቅድስት ማርያም በልቧ ውስጥ እግዚአብሔር የሚወለድበትን ሥፍራ በማዘጋጀቷ የጸጥታ ምንጭ ናት ብለው ጸጥታ ለሌሎች መልካም ቃላትን እንድንናገር ያግዘናል ብለው የመልካም የቃላት ሁሉ ምንጭ መሆኑንም ክቡር አባ ኤሚሊያኖ አንተኑቺ አስረድተዋል።

ነቢዩ ኤልያስን ያስታወሱት አባ ኤሚሊያኖ፣ እግዚአብሔር ጸጥታ በሚገኝበት ስፍራ እንደሚገኝ መናገሩን አስታውሰው፣ ኢየስሱ ክርስቶስም የእግዚአብሔርን ቃል ሊያደምጥ ጸጥታ ወደ ነገሠበት ተራራ ላይ መውጣቱን አስረድተዋል። ይህም የጸሎት እና የጸጥታ አባት የሆኑት ፣ በቸርነታቸው እና በመልካም ንግግራቸው የሚታወቁ በርካታ ቅዱሳን የሕይወት ተሞክሮ መሆኑን ክቡር አባ ኤሚሊያኖ አስረድተዋል።

ጸጥታ በመንፈሳዊ ጉዟቸው ትልቅ ብርታት እንደሰጧቸው የገለጹት አባ ኤሚሊያኖ፣ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስም የሚጠራ ቤተክርስቲያን ለማሳነጽ አግዞኛል ብለዋል። አባ ኤሚሊያኖ፣ ዛሬ ላይ በቤተክርስቲያን ሆነ በማኅበረሰብ መካከል የጸጥታን ጥቅም ማወቅ አስፈላጊ ነው ብለው የጸጥታን ጥቅም ከተገነዘብን የቃላት ጥቅምንም ማወቅ እንችላለን ብለዋል። ትክክለኛ ጊዜ በውል ባያውቁትም፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሲያበቃ መንፈሳዊ ጸጥታን የሚማሩበት የስልጠና ማዕከል እንደሚከፍቱ ክቡር አባ ኤሚሊያኖ አንተኑቺ ገልጸዋል።       

26 April 2020, 13:27