ቶማስ ኢየሱስ ከሙታን መነሳቱን አመነ። ቶማስ ኢየሱስ ከሙታን መነሳቱን አመነ። 

የሚያዝያ 18/2012 ዓ.ም. ዘዳግም ትንሣኤ ቃለ እግዚኣብሔር አስተንትኖ

"ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፣ ሰላሜን እተውላችኋለሁ። እኔ የምሰጣው ሰላም አለም እንደሚሰጠው ዓይነት ሰላም አይደለም"!

የእለቱ ምንባባት 

1.     1ኛ ቆሮ· 15፡ 1-19

2.     1ኛዮሐ· 1፡1-10

3.     ሐዋ·ሥራ 23፡ 1-9

4.     ዮሐንስ  20፡19-31

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ታየ

በዚያኑ ዕለት፣ በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን በምሽት፣ ደቀ መዛሙርቱ አይሁድን በመፍራት በሮቹን ቈልፈው ተሰብስበው ሳለ፣ ኢየሱስ መጣና በመካከላቸው ቆሞ፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው። ይህንም ብሎ እጆቹንና ጐኑን አሳያቸው፤ ደቀ መዛሙርትም ጌታን ባዩት ጊዜ እጅግ ደስ አላቸው። ኢየሱስም እንደ ገና፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ አብ እኔን እንደ ላከኝ፣ እኔም እናንተን እልካችኋለሁ” አላቸው። ይህን ካለ በኋላም፣ እፍ አለባቸውና እንዲህ አላቸው፤ “መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ፤ የሰዎችን ኀጢአት ይቅር ብትሉ፣ ኀጢአታቸው ይቅር ይባልላቸዋል፤ ኀጢአታቸውን ይቅር ባትሉ ግን፣ ይቅር አይባልላቸውም።”

ኢየሱስ ለቶማስ ታየ

በዚህ ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው፣ ዲዲሞስ የተባለው ቶማስ፣ ኢየሱስ በመጣ ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር አልነበረም። ሌሎች ደቀ መዛሙርትም፣ “ጌታን አየነው እኮ!” አሉት። እርሱ ግን፣ “በምስማር የተቸነከሩትን የእጆቹን ምልክቶች ካላየሁ፣ ምስማሮቹ በነበሩበት ቦታ ጣቴን ካላደረግሁ፣ በጐኑም እጄን ካላስገባሁ አላምንም” አለ። ከስምንት ቀን በኋላም፣ ደቀ መዛሙርቱ በቤት ውስጥ ነበሩ፤ ቶማስም ከእነርሱ ጋር ነበር፤ በሮቹ ተቈልፈው ነበር፤ ኢየሱስ ግን መጥቶ በመካከላቸው ቆመና፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው። ከዚያም ቶማስን፣ “ጣትህን ወደዚህ አምጣ፤ እጆቼንም ተመልከት፤ እጅህን ዘርጋና በጐኔ አስገባ፤ አትጠራጠር፤ እመን” አለው። ቶማስም፣ “ጌታዬ፤ አምላኬም!” አለው። ኢየሱስም፣ “አንተ ስላየኸኝ አምነሃል፤ ሳያዩ የሚያምኑ ግን ብፁዓን ናቸው” አለው። ኢየሱስ በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፉ ሌሎች አያሌ ታምራዊ ምልክቶችን በደቀ መዛሙርቱ ፊት አድርጓል፤ ነገር ግን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ፣ የእግዚአብሔርም ልጅ እንደሆነ ታምኑ ዘንድ፣ አምናችሁም በስሙ ሕይወት እንዲኖራችሁ ይህ ተጽፎአል።

 

የእለቱ የእግዚኣብሔር ቃል አስተንትኖ

በክርሰቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

ዛሬ (ሚያዝያ 18/2012 ዓ.ም) እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓተ አምልኮ አቆጣጠር ደንብ መሰረት ዳግማዊ ትንሳኤ ወይም ደግሞ ዘቶማስ የተሰኘውን ሰንበት እናከብራለን።

በዚህም ዕለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በበዓለ ትንሳኤው ያገኘነውን ጸጋና በረከት እንዴት አድርገን በሕይወታችን ለመተርጎም የምንችልበትን መንገድ ሊያሳየንና ሊያበረታታን ቀደም ባሉት ንባባት አማካኝነት ወደ እያንዳዳችን ልብ በመምጣት ያንኳኳል።

በዚህም መሠረት በመጀመሪያው ንባብ 1ኛ ቆሮ· 15፡ 1-19 ላይ እንደምናገኘው ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ የእምነታችን መሠረት ስለሆነው ስለ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ከሞት መነሳትና በትንሣኤውም አማካኝነት ባገኘነው ጸጋ እንዴት አድርገን መጓዝ እንዳለብን ያስተምረናል።

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን የተበሰረውን  የክርስቶስ ትንሳኤ በማመን ከእርሱም በሚፈልቀው የማያልቅ መንፈሳዊ ጸጋ በመጋትና ሕይወታችንን በትክክለኛ አቅጣጫ በመምራት የዘለዓለማዊ ደኅንነት ተካፋዮች እንደምንሆን ይነግረናል።

ክርስቶስን ማመን ማለት ከእርሱ ጋር አብሮ መጓዝ ማለት ነው፣ ከክርስቶስ ጋር አብሮ መኖር ማለት ነው። እምነታችን ከእርሱ ጋር አብረን በመጓዝና በመኖር ላይ ያልተመሠረተ ከሆነ በውስጣችን አለን የምንለው እምነት ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል። ምክንያቱም ከእርሱ ጋር ካልሆንን በስተቀር ምንም ዓይነት መንፈሳዊ ፍሬ ማፍራት አንችልም። እኛ በእርሱ ውስጥ እርሱ ደግሞ በእኛ ውስጥ ከሌለ በምንም መልኩ መንፈሳዊ ፍሬ ለማፍራት አንችልም። ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ “በእኔ ኑሩ፤ እኔም በእናንተ እኖራለሁ። ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ካልሆነ በቀር ብቻውን ፍሬ ሊያፈራ አይችልም፤ እናንተም በእኔ ካልኖራችሁ ፍሬ ልታፈሩ አትችሉም። “እኔ የወይን ተክል ነኝ፤ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ማንም በእኔ ቢኖር እኔም በእርሱ ብኖር፣ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል፤ ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና” (ዮሐ. 15፡ 4-5) ይለናል።

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንጦስ ሰዎች የሰበከውን ቃል ዛሬም ለእኛ ለእያንዳዳችን በድጋሚ ይናገራል፣ እንዲህም ይላል “ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የሞተው ኃጢአት ሳይኖርበት የእኛን  ኃጢአት ለማጠብ፣ የእኛን ቅጣት እርሱ ለመሸከም፣ የእኛን ክፋት፣ የእኛን ውርደት፣ የእኛን ስቃይ፣ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ ነው። ይህንንም አድርጎ ከሞት በመነሳት እርሱ ዘለዓለማዊ አምላክ መሆኑን አሳይቶናል ሞት በእርሱም ላይ ሆነ በእኛ ላይ ምንም ዓይነት ስልጣን እንደሌለው አረጋግጦልናል” ይለናል።

ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አብረን በመኖራችን ከእርሱ ጋር አብረን ወደ መቃብር እንወርዳለን፣ ኃጢያታችንን በሙሉ በተከፈነበት በተልባ እግሩ ልብስ ጠቅልለን እዛ በመተው ከእርሱ ጋር አብረን አንነሳለን እኛም እንደሱ ዘለዓለማዊ ሞትን አሸንፈን  ዘለዓለማዊ ሕይወትን እንቀዳጃለን። ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ  ይህንን በተመለከተ ሲናገር “ነገር ግን ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው የእርሱ መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር፣ ክርስቶስ ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው እርሱ በእናንተ በሚኖረው በመንፈሱ ለሚሞተው ሰውነታችሁ ደግሞ ሕይወትን የሰጠዋል” (ሮሜ 8፡11)  ይለናል።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ በመነሳቱ በፍርሃትና በጭንቀት ተውጠው ተስፋ ቆርጠው በቤት ውስጥ በር ቆልፈው ተቀምጠው ለነበሩት ወንድሞቹ አዲስ ተስፋን ሰጣቸው፣ ጥልቅ የሆነ መረጋጋትን ውስጣዊና ውጫዊ ሰላምን አላበሳቸው። እነርሱም ይህን ነገር ከሰው የሰሙት ሳይሆን በራሳቸው ዓይን የተመለከቱት በእጃቸው ዳስሰው ያረጋገጡት ታሪክም ሆነ የሰው ልጅ ሊሽሩት የማይችሉት ሃቅ ነው። በዛሬ በሁለተኛው ምንባብ ላይ እንደ ተጠቀሰው ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንጦስ ሰዎች የሰበከውን ቃል በሙላት ያጠናክረዋል አንዲህም ይላል “ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያ የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውንና የተመለከትነውን እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን። ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል፣ እንመሰክራለንም ከአብ ዘነድ የነበረውን ለእኛም የተገለጸውን የዘለዓለምን ሕይወት እናወራላቹሃለን” (1ዮሐ· 1፡1-10)  ይለናል።  ስለዚህ ይህ ሞትን ድል አድርጎ የተነሳ አምላክ ዛሬም ለእኛ ለልጆቹ በመገለጥ የእርሱን ሰላም ያላብሰናል፣ አዲስ ሰማያዊ ተስፋን ይሰጠናል፣ ጥልቅ የሆነ ውስጣዊና ውጫዊ ሐሴትን ይሞላናል፣ እንዲሁም ዘወትር የእርሱ እውነተኛ ምስክሮች ሆነን መቆም የምንችልበትን ጸጋና በረከት ያጎናጽፈናል።

ይህ ሞትን ድል አድርጎ የተነሳ አምላክ የብርሃን አምላክ፣ የቅድስናና የጽድቅ አምላክ፣ የፍቅርና የአንድነት አምላክ ነው ይላል ቅዱስ ዮሐንስ በዛሬው መልእክቱ። ከእግዚአብሔር የሚመጣ ብርሃን ጨለማን እንደሚያጠፋ እንዲህም ደግሞ ከእግዚኣብሔር የሚመጣ ፍቅርና ሕብረት ክፉውን ሁሉ እንደሚያርቅ ዛሬ እኛም ከእግዚኣብሔር ጋር ያለንን አንድነት በማጥበቅ በብርሃን እንድንመላለስ በሕይወታችን ያለውን ውስጣዊና ውጫዊ ጨለማን እንድናስወግድ ተጋብዘናል። ይህ በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ አማካኝነት ያገኘነውን ብርሃን የተቀበልነውን እውነተኛ መንፈስ በተግባር አንድንኖርበት፣ ብሎም ይህ ብርሃን ከእኛ አልፎ ለሌሎችም አንዲያበራ ምክንያት እንድንሆን ግንባር ቀደም መስካሪዎች እንድንሆን ተጠርተናል።

እግዚኣብሔር ፍጹም ብርሃን ነው፣ ስለዚህ እኛም ከዚህ ከብርሃን አምላክ ጋር ሕብረት ካለን ይህ ፍጹም ብርሃን በውስጣችን ያበራል፣ ከብርሃኑ የሚወጣው ነጸብራቅ ልክ እንደ ጨረቃ በዙሪያችን ለሚኖሩት ሁሉ ያበራል፣ በዚህ መልኩ እያንዳዳችን በእርሱ ብርሃን ብንመላለስ የአንዳችን ብርሃን ለሌላው የሌላው ብርሃን ደግሞ ለሌሎች ስለሚያንጸባርቅ ዓለማችን በክርስቶስ ብርሃን ትሞላለች፣ ጨለማንና የጨለማን ሥራ የዲያቢሎስንም ሴራ ሁሉ በቀላሉ ማስወገድ ትችላለች። ሐዋርያው ዮሐንስ በመልዕክቱ ሲናገር “ስለዚህ የዲያቢሎስን ሥራ እንዲያፈርስ የእግዚኣብሔር ልጅ ተገለጠ ከእግዚኣብሔር የተወለደ ሁሉ ኃጢያትን አያደርግም ዘሩ በእርሱ ይኖራልና፣ ከእግዚኣብሔርም ተወልዷልና ኃጢያትን ሊያደርግ አይችልም” (1 ዮሐ 3፡9) ይለናል። ይህም ማለት ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ከመሠረተው ዘወትር ከኃጢያት ርቀን እንድንኖር ከሚያደርገው ከምስጢረ ንስሃ ጋር የጠበቀ ግንኙነት አለው ማለት ነው። በዚህ መልኩ የክርስቶስን ብርሃን ይዘን ከዓለም ጫፍ እስከ ዓለም ጫፍ እንጓዛለን።

 የዛሬው የዮሐስ ወንጌል ምዕራፍ 20 ላይ ያለው ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛምርቱ እንደተገለጸ ይናገራል። ደቀ መዛምርቱ ፈርተው በአንድነት ተሰብስበው ወደነበሩበት ገባ፣ ምን አልባት እነሱ ከድተውት በመሄዳቸው ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወቀሳና ትችት ይመጣብናል ብለው ሰግተው ይሆናል። እርሱ ግን ፍርሃታቸውን ተረድቶ ጭንቀታቸውንም ተገንዝቦ የማበረታቻና የመጽናኛ ቃል ሰጣቸው፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው። በዚህም ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቃል ብውስጣቸው የነበረ ስጋትና ጭንቀት ተወገደ።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያቱ የስጣቸው ሰላም ለእነርሱ ብቻ ሳይሆን ይህንኑ ሰላም ወደ ዓለም ሁሉ ይዘው አንዲሄዱ ነግሮኣቸዋል። አብ እኔን እንደላከኝ እኔም ደግሞ እናንተን እልካችኋለው አላቸው። ኃጢያትን ሁሉ ይቅር የማለትን ሥልጣን በመስጠት የእርሱን ሰላም የእርሱን ብርሃን፣ የእርሱን ፍቅር፣ የእርሱን ቃል የእርሱን ሕብረት በዓለም ሁሉ እንዲያዳርሱ ላካቸው። ይህንን ሁሉ ሲያደርጉ ግን የእርሱ መንፈስ የእርሱ ኃይል ዘወትር ከእነርሱ ጋር እንደሚሆን ቃል ገብቶላቸዋል። ዛሬ ደግሞ እኛ በእነርሱ ቦታ ተተክተን እንደየስጦታችን እውነተኛ የክርስትና ሕይወትን በመኖር ይህንን የክርስቶስን ብርሃንና ሕብረት ፍቅርና ሰላም ወደ ዓለም ሁሉ ለማድረስ ጽዋውን ተቀብለናል።

ከሐዋርያቱ አንዱ ቶማስ የተባለው በመጀመሪያው የክርስቶስ መገለጽ ጊዜ አልነበረም፣ በሁለተኛው ጊዜ ግን ነበረ፣ የክርስቶስን ቁስሎች ተመልክቶ አመነ፣ ጌታዬ አምላኬ በማለትም ሙሉ በሙሉ ማመኑን ገለጸ።

ይህ የቶማስ መጠራጠር የሚያመለክተው በእያንዳዳችን ውስጥ ያለዉን የኃጢያት ዝንባሌ ነው። በእያንዳዳችን ውስጥ ያለው በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ብርሃን ያልተጎበኘውን የእኛን ማንነት ነው። ነገር ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምንም እንኳን የዚህ ዓይነት የድካም ዝንባሌ ብናንፀባርቅም እርሱ ግን አይዟችሁ አትፍሩ፣ እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ፣ በማለት ያጽናናናል ያበረታንማል። እኛም ይህንን የእርሱን ማጽናኛ ቃል ስንሰማ ልክ አንደ ቶማስ ከልባችን አምላኬና ጌታዬ ብለን ለቀጣይ ተልዕኳችን ዝግጁ መሆናችንንንና እስከ መጨረሻ ከእርሱ ጋር አብረን እንደምንጓዝ ቃል ልንገባ ይገባል። እውነተኛ የትንሣኤው ብርሃን መስካሪዎች መሆናችንን በሕይወታችን ልናስመሰክር ይገባል።  ይህንንም ለማድረግ እንድንችል የዘውትር ረዳታችን እና ጠበቃችን የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትርዳን፣  ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የተቀበልነውን የትንሣኤ ብርሃን ይዘን እስከ መጨረሻ መጓዝ እንችል ዘንድ ብርታትን ከአንድያ ልጇ ታሰጠን ዘንድ አማላጅነቷን ልንማጸን ያስፈልጋል።

ምንጭ፡ የቫቲካን ሬዲዮ የአማርኛው አገልግሎት

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ይህን ዝግጅት ለማዳመጥ ከእዚህ ቀጥሎ ያለውን "ተጫወት" የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
24 April 2020, 19:45