የጣሊያን መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሰፔ ኮንተ፤ የጣሊያን መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሰፔ ኮንተ፤ 

የጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ መንግሥት ባወጣው አዲስ ደንብ ላይ ቅሬታውን ገለጸ።

የጣሊያን መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሰፔ ኮንተ ትናንት ሚያዝያ 18/2012 ዓ. ም. ለመላው የሃገራቸው ሕዝብ የኮሮና ቫይረስ አስቸኳይ ጊዜ ሁለተኛ ዙር እቅድ በማስመልከት መንግሥታቸው ያስተላለፈውን ውሳኔ በማስመልከት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሰፔ ኮንተ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ለዜጎች ክፍት ሆነው የተሟላ ባይሆንም በመጠኑ አገልግሎታቸውን የሚያቀርቡ ተቋማትን እና መሥሪያ ቤቶችን ይፋ አድርገዋል። ይሁን እንጂ ቤተክርስቲያናት ለምዕመናን የሚሰጡት መንፈሳዊ አገልግሎቶች ዝግ ሆነው የሚቆዩ መሆናቸውን አስታውቀዋል። በዚሁ የጠቅላይ ሚኒስትር መግለጫ ላይ ቅሬታ እንዳለው ያስታወቀው የጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በበኩሉ የመንግሥት ውሳኔ የዜጎችን የእምነት ነጻነት የሚጥስ ነው ብሏል። የጳጳሳት ጉባኤ ቅሬታን ያዳመጠው የመንግሥት ምክር ቤት፣ በጉዳዩ ላይ አስቸኳይ ውይይት በማድረግ በቅርብ ጊዜ ውስጥ መንግሥታዊ ውሳኔን የሚያሳውቅ መሆኑን ገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን 

የጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በእምነት ነጻነት ላይ የሚደረገውን ጥሰት አሜን ብለው የማይቀበሉ መሆኑን ገልጸው ለሕዝብ አገልግሎት ተብሎ የሚደረግ ከሆነ ቤተክርስቲያንም በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ለድሆች የምታቀርበው ከፍተኛ አገልግሎት ግንዛቤ ሊኖረው ይገባል ብለዋል። አገልግሎቱ የቅዱሳት ምስጢራት አቅርቦትን የሚያካትት መሆኑን ከሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋዜጣዊ መግለጫ ከሰጡ በኋላ አስታውቀዋል።

የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ከመንግሥት ምክር ቤት ጋር ሳምንታትን የፈጀ ውይይት ካደረገ በኋላ፣ ቤተክርስቲያን የመንግሥትን መመሪያ እና ደንብ በማክበር ተግባራዊ ስታደርግ የቆየች መሆኑ ገልጸው መንግሥት ለምዕመናን የሚቀርብ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት አገልግሎት እንዳይጀመር መከልከሉ ተገቢ አይደለም ብሏል። የብጹዓን ጳጳሳቱ ጉባኤ መንግሥት የተጣለበትን ሃላፊነት ለይቶ በማወቅ፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አስቸኳይ ጊዜ የጤና እንክብካቤን ቤተክርስቲያን ከምታቀርበው መንፈሳዊ አገልግሎት ጋር አመዛዝኖ መመልከት ተገቢ ነበር ብሏል።  

የጣሊያን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ሉቺያኖ ላሞርጌሰ በበኩላቸው እንዳስታስወቁት መንግሥታቸው የዜጎችን የአምልኮ ነጻነት የሚያከብር እና በስፋት የተመለከተው መሆኑን ገልጸው፣ እስካሁን በጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ፣ በሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በመንግሥት ምክር ቤት መካከል ሰፊ ውይይቶች ሲደረጉ መቆየቱን አስረድተዋል። የብጹዓን ጳጳሳቱ ጉባኤ የመንግሥትን ውሳኔ ከቅሬታ ጋር የተቀበለው መሆኑን ገልጾ፣ መንግሥት የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ የሚወስዳቸውን ውሳኔዎን መቃወም እንደማይችል ገልጾ፣ ወረርሽኙን ለመከላከል በቂ አቅም በማይታይበት ባሁኑ ወቅት ቤተክርስቲያን የምታቀርባቸውን ሐዋርያዊ አገልግሎቶች አሳንሶ መመልከት ተገቢ አለመሆኑን ገልጿል።

የጣሊያን መንግሥት ምክር ቤት በበኩሉ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ያሰማውን ቅሬታን እንደሚቀበል አስታውቆ፣ በሚቀጥሉት አጭር ቀናት ውስጥ በጉዳዩ ላይ መክሮበት ውሳኔውን የሚያሳውቅ መሆኑን ገልጿል።

ይህን ዜና በድምጽ ማድመጥ ከፈለጉ የተጫወት ምልክትን ይጫኑ፣
27 April 2020, 17:43