ካርዲናል ብርሃነየሱስ የ2012 ዓ.ም የትንሳኤ በዓል አስመልክተው ያስተላለፉት መልእክት ካርዲናል ብርሃነየሱስ የ2012 ዓ.ም የትንሳኤ በዓል አስመልክተው ያስተላለፉት መልእክት 

ካርዲናል ብርሃነየሱስ የ2012 ዓ.ም የትንሳኤ በዓል አስመልክተው ያስተላለፉት መልእክት

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳሳት የ2012 ዓ.ም. የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የትንሣኤ በዓል በማስመልከት ያስተላለፉት መልዕክት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

“በአንተ የሚያምኑ ሁሉ በችግራቸው ጊዜ ወደአንተ ይጸልያሉ፤ ብርቱ የመከራ ጎርፍ በሚመጣበት ጊዜ አይነካቸውም።” (መዝ. 33፡8)

በፁዐን ጳጳሳት

ክቡራን ካህናትና ገዳማውያን/ውያት

ክቡራትና ክቡራን ምዕመናን

መላው ሕዝበ እግዚአብሔር

በጎ ፍቃድ ላላቸው ሰዎች በሙሉ

ከሁሉ አስቀድሜ እንኳን ለ2012 ዓ.ም. የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞቴን አቀርብላችኋለሁ።  የአርባ ጾማችንን በሰላም አስጀምሮና አስፈጽሞ ለዚህች ለተባረከች የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ክብረ በዓል ላደረሰን ለፈጣሪ አምላካችን ከፍ ያለ ምስጋና እናቀርብለታለን።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ክርስቶስ ሁሉ ነው፡ በሁሉም ነው” ይላል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  ዛሬ በአዲስ ሁኔታ በበዓለ ትንሣኤ በእኛ ይኖራል። እኛም ከእርሱ ጋር የእግዚአብሔር ልጆች ነን ሰለሆነም ዛሬ ወደ እርሱ የምንመለስበት ቀን ነው።

የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ  ትንሣኤ ከማክበር የበለጠ ቀን የለም። ሆኖም የዘንድሮው በዓላችን በሃዘንና በጨለማ የተከበበ ቢመስለንም በተስፋ የተሞላ ሆነን እናከብረዋለን። ምክንያቱም ጌታችን የሥጋውን ድካም ሞትን ድል በማድረግ በመንፈሳዊነት እንዳሸነፈ እኛም የሥጋን ድካም በመንፈሳዊነት እንደምናሸንፍ አውቀን በዚህ ወቅት የዓለም ደዌ ሆኖ የመጣውን የኮሮና ቫይረስ እርሱ በትንሣኤው እንዲሽርልንና እንዲያጠፋልን የጀመርነውን የጸሎትና የንስሐ ልመና አምላካችን ሆይ እንደቸርነትህ ብዛት ማረን፣ ይቅር በለን በማለት አጠናክረን ልንቀጥል ያስፈልጋል። ከዚህ ጋር ልባችንን ሙሉ በሙሉ ልናስገዛለት ይገባናል። ምክንያቱም ክርስቶስ በልባችን ውስጥ ሲኖር እነሆ በክብር ተስፋው እንኖራለን። አሁን ከፀሃይ በታች ያለው መልካም ነገር ሁሉ ከንቱ መሆኑን አይተናል። ከዚህ በኋላ የሚቀረን እግዚአብሔርን ፈርቶ ማክበር እና ለእርሱ መታዘዝ ነው።

ብዙዎቻችን ዓመቱን ስንጀምር ብዙ ነገሮችን አቅደን ይሆናል። በትምህርት፣ በሥራ፣ በንግድ፣ በጉዞ፣ ሌሎችም፤ ሆኖም ግን በዚህ ደዌ እንቅፋት ገጥሞናል ቢሆንም ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ወደኋላ ሊጎትቱ የሚችሉ እንቅፋቶች በገጠሙት ጊዜ ምንም ነገሮች ቢከሰቱ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለይኝ የሚችል ምንም ነገር የለም (ሮሜ 8 ፡35)በማለት ፀንቶ እንደቆመ እኛም እስከመጨረሻው በጋራ ፀንትን በመቆም ደህንነቱንና ፈውሱን በልመናና በንስሐ ተግተን ምህረቱን ልንጠብቅ ያስፈልጋል።

ማንኛውም ሰው ቢሆን ሕይወቱን እንደማይረባ ነገር ቆጥሮ በማይሆን አቅጣጫ መምራት የለበትም። ትርጉም የሚሰጠውን ሕይወት ለመኖርና የሙሉ ደስታ ሕይወትነ መልስን ለማግኘት በየዕለቱ የሚነገረንን እና የምንባለውን መስማትንና የሚያዋጣውን መፈፀም ያስፈልገናል።

የፈጠረን አምላክ የማይለወጥና ቅዱስ ነው፡፡ በሕይወት ያለው ፍጥረት በሙሉ ያለ እርሱ መኖር እንደማይችል ሁሉ ለተጨነቀው አዕምሮአችን ሰላምና እርጋታን የሚስጠን እርሱ ነው። የምናደርገው እንቅስቃሴያችን ለጊዜው ከመንቀሳቀስ ቢታገድም በማንኛውም መንገድ ለነፍሳችን የሚተላለፈውን የእግዚአብሔር መልዕክት ማዳመጥ መቻል አለብን፤ ብቻችንን አይደለም ያለነው፡፡

 የከበበንን አስፈሪ ነገር ስናየው ያለእርሱ ምንም መሆናችንን ያስረዳናል፡፡ ሰው አሁን ከምንጊዜውም በበለጠ አምላኩን የሚፈለግበት ጊዜ ነው። ሁሉም ወደርሱ ተንበርክኮ በድለንሃልና ይቅርበልን የሚልበት እንጂ በራሱ ብቻ የሚሮጥበት ምንም ነገር የለውም፡፡ ማንም ከዚህ መቅሰፍት ካለጌታ መሻገር አይችልምና።

አሁን የመጣብን መከራ ከእግዚአብሔር አቅምና ችሎታ በላይ ስላልሆነ በእርሱ ጥላ ሥር መሆን ያስፈልገናል። እርሱ በዙሪያችን እንደሚገኝ ስናውቅ ፍስሐና ደስታ ይሞላናል፡፡ በትንቢተ ዕንባቆም 3፡ 17-18 ላይ አንዲህ ተብሎ ተጽፏል፤ “እኔ በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል እርሱ መድኃኒቴም ስለሆነ ሐሴት አደርጋለው” ይላል።

ጌታችን የደረሰበትን መከራና ስቃይ ስናስብና የክርስቶስን ትንሳኤ ስናከብር እኛም ባሳለፍነው አርባ ጾም ዓለም ከክርስቶስ ጋር ያሳለፈውን መከራና ስቃይ ስናስተውል በእርሱ ደግሞ ድልና መድኃኒት መኖሩን በማመን ነው። በጎልጎታ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር እንደሌለ ያሳየን ራሱን በሞት እስከመስጠት የወደደን ዛሬም ልጆቼ አይዟችሁ ይለናል።

የተወደዳችሁ ወገኖች፣

 ይህን ክፉ ቀን ማለፍ የምንችለው በእምነትና በፀሎት ነውና እንበርታ። እንቆቅልሽ የሆነብን ነገር ተፈቶ አዕምሮአችን ሰላምና ደስታ እንዲያገኝ በተለያየ መንገድ ይህን በሽታ ለመከላከል ለሚሰሩና ለሚተጉ እንዲሁም በጎ ለሚያደርጉ ሁሉ እግዚአብሔር ጥበቃውንና ፀጋውን እንዲያበዛላቸው ምኞታችንና ጸሎታችን ነው።

ክርስቲያኖችም በዚህ የትንሳኤ ክብረ በዓል ጥንቃቄ በተሞላው መንገድ ለወንድሞቻችሁና ለእህቶቻችሁ ብሎም ለአገራችሁ ህዝቦች እንደአቅማችሁ አስፈላጊውን እገዛ እና እርዳታ እንድታደርጉ በእግዚአብሔር ስም እንጠይቃችኋለን።       

በመጨረሻም በውጭ አገር ለምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ በስደት ላይ ያላችሁ ወንዶች እና ሴቶች ወገኖቻችንና ልጆቻችን፣ የአገርን ድንበር ለማስከበር በየጠረፉና በውጭ አገራት ለምትገኙ የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ በየማረሚያ ቤቶች ለምትገኙ የሕግ ታራሚዎች፣ በየቤቱና በየ ሆስፒታሉ ለምትገኙ ህሙማን፣ በውጭ አገራት ለምትገኙ ኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያውያት በሙሉ እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ በዓሉንም የሰላም የደስታ የፍቅር ያድርግላችሁ።

አምላካችን ወረሽኙንና በሽታውን ከአገራችንና ከምድራችን ያርቅልን!

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በትንሣኤው አገራችንን ኢትዮጵያን ይባርክልን፤ ይጠብቅልን።

19 April 2020, 10:06