የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማሕበራዊ አስተምህሮ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማሕበራዊ አስተምህሮ  

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ ያለፈባቸው አራት ዋና ዋና የታሪክ ሂደቶች።

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማሕበራዊ አስተምህሮ

ክፍል ስምንት

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ባለፈው ሳምንት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ አራት ዋና ዋና የሚባሉ የታሪክ ሂደቶችን አልፎ ዛሬ የደረስበት ደረጃ ላይ መድረሱን መግለጻችን የሚታወስ ሲሆን ከእነዚህ ደረጃዎች ውስጥ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕዮተ ዓለም (እ.አ.አ 1891-1931) የተሰኘውን የመጀመሪያውን የታሪክ ሂደት በአጭሩ ከእዚህ ቀደም ማቅረባችን ይታወሳል። በዛሬው እለት የክፍል ስምንት ዝግጅታችን ደግሞ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማሕበራዊ አስተምህሮ ያለፈበትን ሁለተኛ የታሪክ ሂደት እናቀርብላችኋለን እንድተከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።

አዘጋጅ እና አቅራቢ መብራቱ ሀ/ጊዮርጊስ ቫቲካን  

2.  ደረጃ ሁለት፡- አዲስ የክርስቲያን አስተሳሰብ (እ.አ.አ. 1931-1958)!

በሁለተኛ ደረጃ የሚጠቀሰው እና የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማሕበራዊ አስተምህሮ ያለፈበት ታሪካዊ ሂደት “አዲስ የክርስቲያን አስተሳሰብ” የተሰኘው ሲሆን ይህ በተለይም ደግሞ  እ.አ.አ. 1931-1958 ዓ.ም ድረስ በሰፊው ይስተዋል የነበረው የኢኮኖሚ እድገት ባመጣው አዳዲስ የኢኮኖሚ ስርዓት እና  ርዕዮተ ዓለም የተነሳ በወቅቱ የተፈጠረውን ማኅበራዊ ቀውስ መፍታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ትኩረቱን ለማድረግ፣  አዲሱ የኢኮኖሚ ስርዓት ርዕዮተ ዓለም በወቅቱ የነበረውን የክርስቲያን ማኅበርሰብ በማይጎዳ መልኩ፣ ለሁሉም ሕዝቦች እኩልነት እና የጋራ ማኅበራዊ ጥቅም መዋል በሚችልበት ሁኔታ ተጣጥሞ እንዲሄድ የሚያሳስብ እና የሚያስተምር፣ በወቅቱ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን 259ኛ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነበሩት ፒዮ 11ኛ በላቲን ቋንቋ “Quadragesimo anno”በአማርኛው በግርድፉ ሲተረጎም (የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የመጀመርያው ማኅበራዊ አስተምህሮ የነበረው “Rerum Novarum” ከተጻፈ ከአርባ አመታት በኋላ የተጻፈ ማለት ነው) ሐዋርያዊ መልእክት ለንባብ መቀረቡ ይታወሳል።

በላቲን ቋንቋ “Quadragesimo anno” በሚል አርእስት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን 259ኛ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት ፒዮ 11ኛ ይፋ ያደረጉት ሐዋርያዊ መልእክት ሥራን፣ ደሞዝን፣ የግል እና የማሕበርሰብ ሐብት እና በአጠቃላይ ኢኮኖሚን የተመከተ ሐዋርያዊ መልእክት ሲሆን በአጭሩ የሚከተሉትን ዋና ዋና ጭብጦች የዳሰሰ ሐዋርያዊ መልእክት ነው . . .

Ø ሥራ፡- ድርብ ልኬት/ገጽታ አለው፣ ግለሰባዊ እና ማህበራዊ ገጽታ አለው።

Ø ደሞዝ:- የአንድ ሠራተኛ ደሞዝ መወሰን የሚገባው የሠራተኛውን እና የቤተሰቡን ኑሮ፣ የህብረተሰብን ሁኔታ፣ የጋራ ጥቅም ከግምት ያስገባ፣ ሥራ አጥ የሆኑ ሰዎችን ለኑሮአቸው በቂ የሆነ ድጎማ እንዲደረግ ምክረ ሐሳብ ያቀርባል።

Ø ኢኮኖሚ ወይም ካፒታል- በወቅቱ በሁለት ጫፎች ማለትም በካፒታሊዝም እና በሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም የተነሳ ውጥረት ውስጥ ገብቶ የነበረው ኢኮኖሚ ሚዛኑን በጠበቀ መልኩ ለዜጎች በሙሉ በተቻለ መጠን እኩል በሆነ መልኩ የአንድ አገር ሀብት ስርጭት እንዲኖር የሚያስችል መሰረታዊ የሆነ መርህ እንዲኖር ጥሪ የሚያቀርብ ሐዋርያዊ መልእክት ነው።

Ø የንብረት ክፍፍልን በተመለከተ፣ በግለሰባዊ (የግል) እና በማህበራዊ (የጋራ) ንብረት መካከል ያለው ልዩነት በተጣጣመ መልኩ አንዱ ሌላውን በማይጎዳ ሁኔታ ተመጋጋቢ ሆኖ ይኖር ዘንድ መንግሥት ይህ ሁኔታ እንዲፈጠር የማስማማት ግዴታ አለበት የሚሉ ሐሳቦች ተጠቅሰውበታል።

አዲስ የክርስቲያን አስተሳሰብ (እ.አ.አ. 1931-1958) በሚለው በእዚህ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማሕበራዊ አስተምህሮ ያለፈበት ሁለተኛው ሂደት ውስጥ በተለይም ደግሞ በወቅቱ በከፍተኛ ሁኔታ ይነጸባረቅ በነበረው አዲስ የኢኮኖሚ ርዕዮተ ዓለም የተነሳ “Capitalism” በማበብ ላይ በነበረበት ወቅት የተጻፈ ሐዋርያዊ መልእክት ሲሆን በወቅቱ በማኅበርሰቡ ውስጥ በነበረው የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ፍትሃዊ ያልነበረ በመሆኑ የተነሳ ተፍጥሮአዊ የስነ ምግባር ሂደቱን ጠብቆ መሄድ የሚችለው የሰው ልጅን በቅዱስ ወንጌል ላይ መስረቱን ባደረገ የስነ-ምግባር አስተምህሮ ብቻ ላይ የተመሰረተ መሆን እንደ ሚገባው በሰፊው የሚተነትን ሐዋርያዊ መልእክት ነው።  በተለይም ደግሞ በማኅበርሰቡ ውስጥ የኢኮኖሚ ትብብር እንዲፈጠር፣ የመተባበር እና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ሰዎች የኢኮኖሚ ድጎማ እንዲደረግ የሚያሳስብ ሐዋርያዊ መልእክት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ ካለፈባቸው ታሪካዊ ሂደቶች ውስጥ በሁለተኛነት የሚጠቀስ ነው።

ቀደም ባሉት ጊዜያት ማለትም እ.አ.አ. 1917 ዓ.ም ማርክሲዚም በጽነሰ ሐሳብ ደረጃ የነበረ አስተሳሰብ ሲሆን እንደ አውሮፓዊያኑ የቀን አቆጣጠር ከ1931-1958 ዓ.ም ባሉ ጊዜያት ውስጥ ደግሞ ወደ እውነተኛ ሶሻሊዝም እና ኮምኒዝም የተሸጋገረ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ስርዓት ውስጥ ተጨባጭ በሆነ መልኩ መታየት የጀመረበት ወቅት ነበር። እነዚህ በቀድሞ ሶቬት ሕብረት ሶሻሊዝም እና ኮምኒዝም ጽነሰ ሐሳቦች መጀመራቸው የሚታወቅ ሲሆን ቤተክርስቲያን እነዚህን ጽንሰ ሐሳቦች በከፍተኛ ደረጃ የምታቃወም እንደ ሆነ የሚታወቅ ሲሆን ምክንያቱም እነዚህ የሶሻሊዝም እና የኮምኒዝም ርዕዮተ ዓለም አስተሳሰቦች በከፍተኛ ደረጃ ሐይማኖትን የሚቃወሙ በመሆናቸው የተነሳ ነው። በእዚህም መሰረት በወቅቱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት ፒዮ 11ኛ ኮሚንዚምን በከፍተኛ ሁኔታ የሐይማኖት ጠላት አድርገው በመፈረጅ እና ኮሚንዝምን በማውገዝ በላቲን ቋንቋ “Divini Redemptoris”  በአማርኛው በግርድፉ ሲተረጎም (መለኮታዊ አዳኝ) በሚል አርእስት ለንባብ ባበቁት ሐዋርያዊ መልእክታቸው ኮሚንዚምን እና ርዕዮተ ዓለሙን የሚከቱሉ ክርስቲያኖችን በይፋ ማውገዛቸው ይታውሳል፣ ምክንያቱ ደግሞ ኮሚንዝም የሐይማኖት ጸር ነው  ከሚል እሳቤ የመነጨ ነው።

16 March 2020, 18:09