ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል፣ ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል፣ 

የኤርትራ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ለብሔራዊ የሐይማኖት ጉዳዮች ጽ/ቤት ጥያቄ ማቅረቧ ተገለጸ።

ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ እንዳይገቡ ስለታገዱት የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ጉዳይ ማብራሪያ እንዲሰጥ በማለት የኤርትራ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ለብሔራዊ የሐይማኖት ጉዳዮች ቢሮ ጥያቄ ማቅረቧ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት እና የኢትዮጵያ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ሊቀመንበር፣ በኢትዮጵያ የእምድብር ሀገረ ስብከት ጳጳስ ከሆኑት ከብጹዕ አቡነ ሙሴ ገብረ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ጸሐፊ ከሆኑት ከክቡር አባ ተሾመ ፍቅሬ ጋር ሆነው ወደ ኤርትራ የተጓዙት በኤርትራ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የኪዳነ ምሕረት ካቴድራል 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ ክብረ በዓል ላይ እንዲገኙ በማለት ከሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ መንግሥተ ዓብ ተስፋ ማርያም በተደረገላቸው ግብዣ መሠረት መሆኑ ታውቋል።

የኤርትራ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ጽሕፈት እንዳብራራው በክብረ በዓሉ ላይ እንዲገኙ በማለት ግብዣ የተላከላቸው በርካታ የቤተክርስቲያኒቱ ወዳጆች መኖራቸው ሲታወቅ፣ የኢትዮጵያ ልኡካንም ቢሆን በዚሁ ግብዣ መሠረት መሆኑን አስታውቋል። በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ልኡካን የሚፈለግባቸውን የጉዞ መስፈርት አሟልቶ አዲስ አበባ ወደሚገኝ የኤርትራ ኤምባሲ ማቅረቡን እና ወደ ኤርትራ መግባት የሚያስችል ፈቃድ ማግኘቱንም የጠቅላይ ጽሕፈት ቤቱ ማብራሪያ አስታውቋል። ጠቅላይ ጽሕፈት ቤቱ በማከልም ከኤርትራ ካቶሊካዊ ቤተክርስቲያን በኩል ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የእምነት አባቶች የተላከው ግብዣ በሁለቱ አገሮች ሕዝቦች መካከል ለረጅም ዓመታት የዘለቀውን ታሪካዊ ወዳጅነት እና የአክብሮት ባሕልን ያገናዘበ በመሆኑ ልዩ የጉዞ ፈቃድ እንዲሰጣቸው መጠየቁን ገልጾ፣ ይህ ሁሉ ከተደረገ በኋላ ልኡካኑ ወደ ኤርትራ እንዳይገቡ የተከለከሉበት ምክንያት የገለጽ በማለት የኤርትራ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ለአገሩ ብሔራዊ የሐይማኖት ጉዳዮች ቢሮ ጥያቄ  ማቅረቧን አስታውቋል።

ወደ ኤርትራ የሚጓዙ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ የመግቢያ ፈቃድ የሚያረጋግጡት አሥመራ አውሮፕላን ጣቢያ ሲደርሱ መሆኑን ያስታወቀው የኤርትራ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ጽሕፈት ቤቱ አሁንም ቢሆን ወደ ኤርትራ እንደሚመጡ ተስፋ የሚያደርገው በተመሳሳይ መንገድ መሆኑን አስታውቋል። የካቲት 14/2012 ዓ. ም. በአሥመራ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በተፈጸመው ተግባር ማዘኑንም በኤርትራ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ በሆኑት በክቡር አባ ተስፋ ጊዮርጊስ ክፍሎም ተፈርሞ ለብሔራዊ የሐይማኖት ጉዳዮች ጽ/ቤት በቀረበው የማብራሪያ ጥያቄ ገልጿል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
05 March 2020, 17:37