በእግዚአብሔር ምሕረት አንቀልድ በእግዚአብሔር ምሕረት አንቀልድ 

በእግዚአብሔር ምሕረት አንቀልድ

እየበደልነው ሳለን እግዚአብሔር ዝም ብሎ ይመለከታል፣ በመቅጣት ፈንታ ይታገሰናል፣ በኃጢአት ላይ ኃጢአት ብንጨምርም ምንም አያደርገንም፣ ቁጥር በሌለው ክፋታችን እንዳላየንና እንዳልሰማ ይሆናል፣ ንስሐ ገብተን ወደ እርሱ እንደንመለስ በትዕግሥት ይጠብቀናል፣ ምሕረቱ በእኛ ላይ እጅግ በጣም ብዙ ነው። ግን እንደ እርሱ ቸርነትና ታላቅ ምሕረቱ ንስሐ መግባትና መመለስ ሲገባን በክፋታችን እንደገና እንኰንናለን። በበደላችን በክፉ ሥራችን ተጸጽተን ንስሐ ገብተን በመመለስ ፈንታ እንደገና በሌላ ኃጢአት እንወድቃለን። «ከአሁን በኋላ አልበድለውም፣ ምሕረቱን መፈታተን አንፈልግም´ ብለን ከመጠንቀቅ ኃጢአት መሥራት ከመተው እንደገና «እግዚአብሔር መሐሪ ነው፣ ምንም አያደርገኝም ዝም ብሎ ያየኛል፣ በፊት ምሕረት እንዳደረገልኝ አሁንም ደግሞ ይምረኛል´ በሚል ሐሳብ ጸንተን እንቀራለን። በምሕረቱ ተማምነን ደጋግመን በኃጢአት ላይ አንወድቅ። ምንም ሳናስብለት እናሳዝነዋለን፣ በምሕረቱ እንቀልዳለን፣ እናላግጣለን።በእግዚብሔር ምሕረት አንቀልድ፣ “ምንም አያደርገኝም የፈለኩትን ባደርግ ዝም ብሎ ይመለከተኛል፣ መልካም ነገር ማድረግን እምቢ ብል እንኳ ክፉ ባደርግ አንድ ነገር አይናገረኝም´ በማለት እንሞኛለን፡፡ በክፉ ነገር ጸንተን እንኖራለን፡፡ «ቤተክርስቲያን አልሄድም፣ ምን እንዳይመጣብኝ; ጸሎት አላደርግም ምስጢራትን አልሳተፍም፣ አኗኗሬን አልቀይርም፣ የቤተክርስቲያን ትዕዛዞችን አልጠብቅም፣ ምን እንዳልሆን; እግዚአብሔርን ማክበር ማመስገን ብተወው ምንም አያደርገኝም በኃጢአት ውስጥ ብጨመላለቅ እንኳ ዝም ብሎ ያየኛል´ እያልን ክፋት እናበዛለን፣ በምሕረቱ እንሳለቅበታለን፡፡

በእግዚብሔር ምሕረት መቀለድ ጥበበ ሲራክ የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ይሰጠናል፣ «በድዬ ግን አልተቀጣሁም አትበል እግዚአብሔር ቀስ ብሎ ነው የሚቀጣው … በኃጢአት ላይ ምን ኃጢአት አትደራርብ፣ ሁሉንም ኃጢአት ይቅር ይለኛል አትበል፡፡ ምክንያቱም ምሕረትና ቅጣት ከእርሱ በፍጥነት ይመጣብሃልና´ (ጥበ. ሲራ. 5፣4)።

እግዚአብሔር ሁልጊዜ አይታገስም ዝም የማይበልበትና የማይታገስበት ጊዜም አለው፡፡ መሐሪ ብቻ አይደለም ቅን ፈራጅም ነው። ጊዜው ሲያልፍ ምሕረት ማድረጉን ትቶ በፍርድ ተገቢውን ቅጣት ሳይሰጥ አያልፍም፡፡ ለረጅም ጊዜ ከጠበቀ በኋላ በመጨረሻ መዓቱን ያወርዳል፡፡ እስከወሰነው የምሕረት ጊዜ ድረስ የምንፈልገውን እንድናደርግ ይተወናል፡፡ በኋላ ግን ጊዜው ሲያልቅ ይቀጣናል፣ በወዲያኛው ዓለም ስንሻገር ይፈርድብናል፡፡ አሁን በምሕረቱ አንቀልዳለን፣ በኋላ ግን በኃያልነቱ እንቀጠቀጣለን፡፡ ሞተን ለፍርድ ስንቀርብ የሚገባንን ቅጣት እንቀባላለን እርሱ ማን እንደሆነ እናስበው፣ እንደነበረው ዝም ብሎ የሚያይ፣ መሐሪ፣ ታጋሽ ብቻ እንዳልሆነ ይገባናል፡፡ የዚያን ጊዜ በሞኝነታችን ልናዝንና ልንቆጭ ነው፡፡ በምሕረቱ የተጫወትን ልናለቅስ ነው፡፡ የዚያን መጸጸት ምን ሊጠቅም ነው; ጊዜው አልፏል ከንቱ ነው። ጊዜ ካለፈ በኋላ ሊደረግ የሚችል የለም። በወዲያኛው ዓለም ተቆጭተህ፣ አልቅሰህ ወይ ለምነህ የሚቀየር ነገር የለም። ይህንን አስበን ከአሁኑ እንጠንቀቅ፣ በኋላ እግዚአብሔር እንዳይቀጣን ከፈለግን አሁን በምሕረቱ አንቀለድ፣ በትዕግሥቱ አናሹፍበት፣ በኃጢአት ጸንተን አንቅር። መሐሪ ነው ምንም አያደርገኝም እያልን አናስከፋው፣ በኋላ እንዳይብስብን። ምሕረቱ ለእኛ ማስተዋያችን ንስሐ መግቢያችን እንጂ ለኩነኔ አናድርገው።

06 February 2020, 12:34