የየካቲት 22/2012 ዓ.ም ሰባተኛው ሳምንት እለተ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የየካቲት 22/2012 ዓ.ም ሰባተኛው ሳምንት እለተ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ 

የየካቲት 22/2012 ዓ.ም ሰባተኛው ሳምንት እለተ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

በእግዚአብሔር የተወደድን እኛ በአንጻሩ እኛም እንድንወድ ተጠርተናል፣ ይቅርታን ያገኛን እኛ ይቅር እንድል ተጠርተናል፣ በእርሱ ፍቅር የተዋጀን እኛ ሌሎችን በፍቅር እንድንዋጅ ተጠርተናል፣

የእለቱ ምንባባት

1.     ዘሌዋዊያን 19፡1-2,27-18

2.    መዝሙር 102

3.    1 ቆሮ 3፡16-23

4.    ማቴዎስ 5፡38-48

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ዓይን ስለ ዓይን፣ ጥርስ ስለ ጥርስ’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ‘ክፉ አድራጊውን ሰው አትቃወሙት’፤ ነገር ግን ቀኝ ጒንጭህን ለሚመታህ ሌላውን ጒንጭህን ደግሞ አዙርለት። አንድ ሰው እጀ ጠባብህን ሊወስድ ቢከስህ ካባህን ጨምረህ ስጠው። አንድ ሰው አንድ ኪሎ ሜትር ተኩል የሚያህል ርቀት እንድትሄድ ቢያስገድድህ ዕጥፉን መንገድ አብረኸው ሂድ። ለሚለምንህ ስጥ፤ ከአንተም ሊበደር የሚሻውን ፊት አትንሣው።

 “ ‘ወዳጅህን ውደድ፤ ጠላትህን ጥላ’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ ፤ ለሚያሳድዷችሁም ጸልዩ እላችኋለሁ። እንደዚህም በማድረጋችሁ በሰማይ ላለው አባታችሁ ልጆች ትሆናላችሁ፤ እርሱ ፀሓዩን ለክፉዎችና ለደጎች ያወጣል፤ ዝናቡንም ለኀጢአተኞችና ለጻድቃን ያዘንባል። የሚወዷችሁን ብቻ የምትወዱ ከሆነ ምን ዋጋ ታገኛላችሁ? ቀራጮችስ ይህንኑ ያደርጉ የለምን? ወንድሞቻችሁን ብቻ እጅ የምትነሡ ከሆነ ከሌሎች በምን ትሻላላችሁ? አሕዛብስ ይህንኑ ያደርጉ የለምን? ስለዚህ የሰማይ አባታችሁ ፍጹም እንደሆነ እናንተም ፍጹማን ሁኑ።”

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ!

በዛሬው ቅዱስ ወንጌል ውስጥ ኢየሱስ በጥንት ጊዜ የነበረውን ሕግ በመጥቀስ “ ‘ዓይን ስለ ዓይን፣ ጥርስ ስለ ጥርስ’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል” (ማቴ 5፡ 38 ፣ ዘፀ 21፡ 24) በማለት ይናገራል።  ሕጉ ምን ለማለት እንደ ፈለገ እንረዳለን፣ “አንዳች ነገር ቢወሰድብህ፣ አንተም ተመሳሳይ የሆነ ነገር ውሰድ” ማለት እንደ ሆነ እንረዳለን። በእውነቱ ታላቅ መሻሻል የተደርገበት ሕግ ሲሆን  ምክንያቱም የከፋ አጸፋ እንዳንመልስ ይከላከላል፣- አንድ ሰው ቢጎዳህ በተመሳሳይ ሚዛን እንዲከፍለው የሚያደርግ ሕግ ነው፣ በእዚህ ህግ መሰረት ተመጣጣኝ ቅጣት ማደረግ ተፈቅዱዋል፣ ያልተመጣጠነ ቅጣት ማደርግ ግን የተከለከለ ነበር። ይህም በሕጉ ላይ የተደረገ አንድ የማሻሻያ እርምጃ ነው። ሆኖም ኢየሱስ ከእዚያ ባሻገር በመሄድ “እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ‘ክፉ አድራጊውን ሰው አትቃወሙት’፤ ነገር ግን ቀኝ ጒንጭህን ለሚመታህ ሌላውን ጒንጭህን ደግሞ አዙርለት” (ማቴ 5፡39) በማለት ይናገራል። ነገር ግን ጌታ ሆይ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? አንድ ሰው ስለ እኔ መጥፎ ነገር ቢያስብ ፣ አንድ ሰው ቢጎዳኝ በተመሳሳይ መልኩ እና መጠን ብድሩን ብከፍለው ምን አለበት? ኢየሱስ ግን “በፍጹም!” እንዲህ ማደረግ አይገባም፣ ክፉን በክፉ፣ አመጽን በአምጽ መመለስ ተገቢ አይደለም ይለናል።

ኢየሱስ የሚከተለውን የማስተማሪያ ዘዴ ማሰብ እንችላለን፣- በመጨረሻ ክፉ መንፈስ እንደ ማያሸንፍ ያሳያል። ነገር ግን ኢየሱስ የሚጎዱንንንም ሰዎች እንኳን ሳይቀር እንድንወድ የሚጠይቀው ለዚህ ዓላማ ብቻ አይደለም። ምክንያቱስ ምንድን ነው? ምንም እንኳን እኛ ለእርሱ ተገቢ የሆነ ምላሽ ባንሰጥም እግዚኣብሔር አባታችን ሁል ጊዜ ሁሉንም ሰው ይወዳል። እኛ የበደሉንን ሰዎች ይቅር ማለት ከቻልን፣ ክፉን በክፉ የማንመልስ ከሆንን “እንደዚህም በማድረጋችሁ በሰማይ ላለው አባታችሁ ልጆች ትሆናላችሁ፤ እርሱ ፀሓዩን ለክፉዎችና ለደጎች ያወጣል፤ ዝናቡንም ለኀጢአተኞችና ለጻድቃን ያዘንባል” (ማቴ 5፡45) በማለት ይናገራል። ለእዚህም ነው ታዲያ ዛሬ በመጀመሪያው ምንባብ ውስጥ “‘እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” (ዘሌዋዊያን 19፡2) በማለት የሚናገረው። ያ ማለት “እንደ እኔ ሁኑ፣ እኔ የምፈልገውን ነገር ፈልጉ” ማለት ነው። ኢየሱስም ራሱ እንዲህ ነበር ያደርገው። ባልተገባ ሁኔታ እርሱን አወግዘው አሰቃይተው እና በጭካኔ በገደሉት ሰዎች ላይ ጣቱን አልቀሰረባቸውም ነበር፣ ነገር ግን እጆቹን በመስቀል ላይ ለእነሱ ክፈተላቸው። እናም ሚስማሮቹን በእጆቹ ውስጥ እየሰኩ በመዶሻ እየመቱ ከመስቀሉ ጋር እርሱን በቸነከሩበት ወቅት እነሩስን ከማውገዝ ይልቅ “አባት ሆይ የሚያደርጉን አያውቁም እና ይቅር በላቸው” ( ሉቃ 23፡ 33-34) በማለት አባቱን ተማጸነ።

ስለዚህ የክርስቶስ ደቀመዝሙር መሆን ከፈለግን፣ ራሳችንን ክርስቲያን ብለን ለመጥራት ከፈለግን፣ መንገዱ ይህ ነው ፣ ሌላ መንገድ የለም። በእግዚአብሔር የተወደድን እኛ በአንጻሩ እኛም እንድንወድ ተጠርተናል፣ ይቅርታን ያገኛን እኛ ይቅር እንድል ተጠርተናል፣ በእርሱ ፍቅር የተዋጀን እኛ ሌሎችን በፍቅር እንድንዋጅ ተጠርተናል፣ ገደብ የሌልው ፍቅር እንድንሰጥ ተጠርተናል፣ ፍቅር ከሌላ ወግን እስኪመጣ ድረስ ሳንጠብቅ ቀድመን ልንወድ ይገባናል፣ በምናደርገው መልካም ነገር ምንም ትርፍ ሳንጠብቅ መልካም ነገርን እንዲሁ በነጻ ማደርግ ይኖርብናል። ምን አልባትም “ኢየሱስ ነገሮችን አጋኖ ያቀርባል” ብለን እናስብ ይሆናል፣ ሌላው ቢቀር “እኔ ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ ፤ ለሚያሳድዷችሁም ጸልዩ እላችኋለሁ” (ማቴ 5፡44) በማለት ይናገራል፣ እርሱ ትኩረታችንን ለመሳብ በማሰብ በእዚህ መልኩ የተናገረ ቢመስለንም፣ ምናልባት ግን እንዲህ ማለት ሊሆን ይችላል። ይልቁንስ አዎ  በእውነቱ ያ ማለት ነው። እዚህ ላይ ኢየሱስ ተቃራኒ የሆኑ ሐሳቦችን አይናገርም፣ ግራ የተጋቡ ቃላትን አይጠቀምም። እሱ ቀጥተኛ እና ግልጽ ነው። የጥንቱን ሕግ ከጠቀሰ በኋላ በጥብቅ “እኔ ግን እላችኋለሁ፣ ጠላቶቻችሁን ውደዱ” ይለናል፣ እነዚህ ጠቃሚ የሆኑ ተፋላጊ የሆኑ ትክክለኛ ቃላት ናቸው።

ጠላቶቻችሁን ውደዱ፣ ለሚያሳድዱአችሁ ጸልዩ። ይህ አዲሱ የክርስቲያን አሰተሳሰብ ነው። ይህ ክርስቲያኖች የሚለዩበት ምልክት ነው።  መጸለይ እና መውደድ: - ማድረግ ያለብን ይህን ነው ፣ የሚወዱንን  ብቻ ሳይሆን ወዳጆቻችንን ብቻ ሳይሆን፣ ጓደኞቻችንን ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ሕዝብ እንዲህ እንድናደርግ ኢየሱስ ይጋብዘናል። ምክንያቱም የኢየሱስ የፍቅር ድንበሮችንና መሰናክሎችን አያውቅም። ጌታ ያለ ምንም ስሌት ሁሉንም በድፍረት በፍቅር እንድንወድ ይጋብዘናል። ምክንያቱም የኢየሱስ ፈቃድ እርሱ ያለምንም ልኬት እና ቅድመ ሁኔታ እንደወደደን እኛም በእዚያው መጠን ያለ ቅድመ ሁኔታ እና ልኬት እንድንወድ ይፈልጋል።  እንደማንኛውም ሰው በመሆን እርሱ ላቀረበልን ጥያቄዎች ምን ያህል ጊዜ ችላ ብለን አልፈናል! ሆኖም የፍቅር ትእዛዝ እንዲያው ቀለል ባለ መልኩ የተገለጸ ነገር ሳይሆን የቅዱስ ወንጌል ማዕከላዊ ነጥብ ነው። ብቸኛው እና  ህጋዊ የክርስቲያን አክራሪነት ሊገለጽ እና ሊሆን የሚገባው የፍቅር ጽንፈኝነት ነው።

ጠላቶቻችሁን ውደዱ። ዛሬ እነዚህን የኢየሱስ ቃላት ከሰማን በኋላ እነዚህን ቃላት መልሰን መላልሰን በመደጋገም እኛን የሚያሳድዱንን፣ የሚቆጡንን፣ የሚጠሉንን፣ ምቾት የሚነሱንን፣ ክፉ ነገር የፈጸሙብንን ሰዎች እናስብ። “ጠላቶቻችሁን ውደዱ” ይለናል ኢየሱስ። አንዳንድ ጊዜ ለራሳችን ራሳችን ጥያቄ ማቅረብ በጣም መልካም የሆነ ነገር ነው። “በሕይወቴ ውስጥ እንድጨነቅ የሚያደርገኝ ነገር ምንድነው? የሚያስጨንቁኝ ጠላቶቼ ናቸው፣ መጥፎ ነገር የሚሹልኝ ሰዎች ናቸው? ወይስ አለመወደዴ ነው? ”፡፡ ስለ ሌሎች መጥፎ ነገር ፣ ስለ አንተ መጥፎ ነገር ስለሚያስቡ ሰዎች አትጨነቅ። ይልቁንም ልብን ከኢየሱስ ፍቅር ጋር ማስተሳሰር ጀምር፣ ምክንያቱም እግዚአብሔርን የሚወድ በልቡ ውስጥ ጠላት የለውም። አምላክን ማምለክ የጥላቻ ባህልን ማጣፋት ማለት ነው። የጥላቻ ባህል ደግሞ ከእግዚኣብሔር ባህል እጅግ የተለየ ነው። ነገሮች ሳይሳኩ ሲቀሩ፣ ነገሮች እኛ እንደፈለግነው ሳይሄዱ ሲቀሩ ቅሬታ የተሰማን ጊዜያት ስንት ናቸው! ይህ  ስህተት ነው! ኢየሱስ ብዙ ነገሮች የተሳሳቱ መሆናቸውን ፣ ሁል ጊዜም ክፉ ነገር የሚመኙልን ሰዎች እንዳሉ፣ የሚያሳድዱን ሰዎች እንዳሉም በሚገባ ያውቃል።  እርሱ እንድንጸልይ እና እንድንወድ ብቻ ነው የሚጠይቀን። በታሪክ ውስጥ ትልቁ የሆነው አብዮት የኢየሱስ አብዮት ነው! የምትጠላውን ጠላትህን ውደደው የሚለው ነው፣ ከማጉረምረም ባሕል ወደ አመስጋኝነት ባሕል መሻገር ነው። እኛ የኢየሱስ ከሆንን መንገዱ ይህ ነው! ሌላ ከእዚህ የተሻለ መንገድ የለም።

እውነት ነው ይህንን መቃወም ትችላላችሁ-“የአስተያየቱን ታላቅነት ተረድቻለሁ ፣ ግን ሕይወት ሌላ ነገር ነው! ልትሉ ትችሉ ይሆናል። እኔ ኢየሱስ ባለኝ መሰረት ብወድ እና ይቅር የምል ከሆነ፣ በኃይል እና በጥንካሬ አመክኒዮ በሚያምነው በዚህ ዓለም ውስጥ ያለኝ ሕልውና አደጋ ላይ ይወድቃል፣ ምክንያቱም ሁሉም ሰው ስለራሱ ብቻ ያስባልና ብለን ድምዳሜ ላይ ልንደርስ እንችል ይሆናል። ነገር ግን የኢየሱስ አመክንዮ ተሸናፊ የመሆን አመክኒዮ ነውን? ምን አልባት በዓለም ፊት ተሸናፊ የሆናችሁ ሊመስላችሁ ይችል ይሆናል፣ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት አሸናፊ ናችሁ፣  ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በሁለተኛው ንባብ እንዲህ ሲል ነግሮናል “ማንም ራሱን አያታልል፤ ከእናንተ ማንም በዚህ ዓለም ጥበበኛ የሆነ ቢመስለው፣ ጥበበኛ ይሆን ዘንድ ራሱን እንደ ሞኝ ይቍጠር። የዚህ ዓለም ጥበብ በእግዚአብሔር ፊት ሞኝነት ነውና፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፎአልና፤ “እርሱ ጥበበኞችን በራሳቸው ተንኰል ይይዛቸዋል” (1ቆሮ. 3፡18-19 በማለት ይናገራል። እግዚአብሄር አሻግሮ ይመለከታል። እንዴት ማሸነፍ እንደሚቻል ያውቃሉ። ክፉን በመልካም ማሸነፍ እንደሚቻል ያውቃል። እርሱ ያዳነን በሰይፍ ሳይሆን በመስቀል ነው። መውደድ እና ይቅር ማለት እንደ አሸናፊዎች ሰው ሆኖ መኖር ማለት ነው። እምነታችንን በኃይል የምንከላከል ከሆነ እንሸነፋለን። ጌታም በጌቴሴማኒ ለጴጥሮስ የተናገራቸውን ቃላት ይደግምልናል-“ሰይፉን ወደ ሰገባው አስጋባ” (ዮሐ 18፡ 11) ይለናል። በዛሬው እኛ በምንኖርበት ጌትሰመኔ  ግድየለሽ እና ኢፍትሃዊ በሆነ ዓለም ውስጥ፣ የተስፋ ጭላንጭ የጠፋ በሚመስለው ዓለማችን ውስጥ ክርስቲያኖች በመጀመሪያ ሰይፉቸውን እንደመዘዙ ከእዚያም በኋላ እንደ ሸሹት እንደ ደቀመዛሙርቱ ማድረግ አይጠበቅብንም። አይሆንም! መፍትሄው የአንድን ሰው ጎራዴ በአንድ ሰው ላይ ስቦ ማውጣት እና ከእዚያም በኋላ ያሻንን አድርገን ከምንኖርበት ስፍራ መሸሽ አይደለም። መፍትሄው የኢየሱስ መንገድ ነው -ንቁ የሆነ ፍቅር ፣ ትሁት ፍቅር ፣ እስከ መጨረሻው ማፍቀር (ዮሐ. 13፡1)።

ውድ ወንድሞች እና እህቶች ፣ ዛሬ ኢየሱስ ፣ ወሰን በሌለው ፍቅሩ ፣ ሰብዓዊነታችንን ከፍ ከፍ አደረገ። በመጨረሻ እራሳችንን መጠየቅ እንችላለን-“እኛስ ፣ እናደርገዋለን?”። ግቡ የማይቻል ከሆነ ፣ ጌታ እዚህ ግብ ላይ እንድንደርስ አይጠይቀንም ነበር። ነገር ግን ይህንን ብቻችንን ተግባራዊ ማድረግ አስቸጋሪ ነው። ይህንን መተግበር እንችል ዘንድ ጸጋውን እንዲሰጠን ልንጠይቀው ይገባል። ለመውደድ የሚያስችል ጥንካሬን ለማግኘት እግዚአብሔርን ጠይቁ፣ “ጌታ ሆይ ፣ እንድወድ እርዳኝ ፣ ይቅር ማለት አስተምረኝ ፡፡ እኔ ብቻዬን ማድረግ አልችልም፣ የአንተን እርዳታ እሻለሁ፣ እፈልጋለሁም በማለት እንጠይቀው። ሌሎችን የማየት ጸጋ፣ እንዲሁ መሰናክሎች እና ውስብስብ ነገሮች ብቻ ለመፍታት የሚያስችል ጸጋ ብቻ ሳይሆን መጠየቅ ያለብን፣ ነገር ግን ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን መውደድ እንችል ዘንድ እንዲረዳን እንማጸነው። ብዙ ጊዜ እርዳታ እንጠይቃለን፣ ምስጋና እናቀርብለታለን። ነገር ግን እንዴት መውደድ እንዳለብን ለማወቅ ጸጋውን እንዲሰጠን ልንጠይቀው የገባል። ትክክለኛ ክርስቲያን ለመሆን እንችል ዘንድ እውነተኛውን የቅዱስ ወንጌል ልብ በሚገባ መኖር እንችል ዘንድ እንዲረዳን እንማጸነው። በሕይወታችን መጨረሻ ላይ የምንዳኘው “በፍቅር ሕግ ላይ መሰረቱን ባደርገ መልኩ ነው”።  ምንም እንኳን ብዙ ዋጋ የሚያስከፍለን ቢሆንም ቅሉ ዛሬ ፍቅርን እንመርጣለን። ፍቅርን በመለኪያ ስፍረን መስጠት አይገባንም። ኢየሱስን የሰጠንን ተግዳሮት እና የማፍቀር ፈተና ተቀብለን ከእርሱ ጋር ሆነን ያለ ገደብ እንድንወድ እንዲረዳን እንጠይቀው። በእዚህ መልኩ እውነተኛ ክርስቲያኖች እንሆናለን፣ ዓለምም የበለጠ ሰብዓዊ ስፍራ ይሆናል።

ምንጭ፡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በየካቲት 15/2012 ዓ.ም ካደረጉት ስብከት የተወሰደ።

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

29 February 2020, 19:05