ዐብይ ጾም ከመጀመሩ በፊት ባለው ረቡዕ ቀን የሚደረገው በዐመድ የመቀባት ስርዓት ትርጉሙ ዐብይ ጾም ከመጀመሩ በፊት ባለው ረቡዕ ቀን የሚደረገው በዐመድ የመቀባት ስርዓት ትርጉሙ  

ዐብይ ጾም ከመጀመሩ በፊት ባለው ረቡዕ ቀን የሚደረገው በዐመድ የመቀባት ስርዓት ትርጉሙ

በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሥርዐተ አምልኮ ደንብ መሰረት የዐብይ ጾም የሚጀመረው ቄሳውስት የምዕመናንን ግንባር በአመድ የመቀባት ሥርዐት ካከናወኑ በኋላ ነው። በጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር መሰረት የላቲን ሥርዐተ አምልኮ በምትከተለው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የሥርዐተ አምልኮ ደንብ መሰረት የዐብይ ጾም የተጀመረው ረቡዕ እለት የካቲት 18/2012 ዓ.ም ግንባርን በዐመድ የመቀባት ስርዓት ከተደረገ በኋላ ሲሆን ይህም ለመጪዎቹ አርባ ቀናት በጸሎት፣ በጾም እና ምጽዋዕት በመስጠት የሚፈጸመው ጾም እግዚኣብሔርን የሚያስደስት ጾም ይሆን ዘንድ፣ ለጿሚው ሰው ደግሞ መንፈሳዊ ጸጋ የሚያስገኝለት ጾም ይሆን ዘንድ፣ እንዲሁም የፋሲካን በዓል ዋና ትርጉሙን በጠበቀ መልኩ ለማክበር ይቻል ዘንድ መንፈሳዊ ዝግጅት የሚደረግበት ወቅት ነው።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

“ዮሐንስም ተላልፎ ከተሰጠ በኋላ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል እየሰበከና፡ ‘የእግዚአብሔርም መንግሥት ቀርባለች ንስሐ ግቡ በወንጌልም እመኑ’ እያለ ወደ ገሊላ መጣ” (ማር 1፡14-15)። ከዚህ የማርቆስ ወንጌል የምንረዳው ነገር ቢኖር በዐብይ ጾም ወቅት የእግዚኣብሔር መንግሥት መምጣት በጉጉት በመጠባበቅ ይህንን የሚመጣውን የእግዚኣብሔር መንግሥት ተገቢ በሆነ ሁኔታ መንፈሳዊ ዝግጅቶችን በማድረግ መቀበል እንችል ዘንድ መንፈሳዊ ዝግጅት የምናደርግበት ወቅት ሊሆን ይገባዋል። ለዚህም ነው ታዲያ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን የዐብይ ጾምን በሚጀምሩበት ወቅት ግንባራቸውን በአመድ የመቀባት መንፈሳዊ ሥርዓት በመፈጸም በሰሩት ኃጢአት በመጸጸት ወደ ንሰሐ በመመለስ፣ መንፈሳዊ ለውጥ በማምጣት ሕይወታቸውን ለእግዚኣብሔር የተገባ እንዲሆን በማድረግ የዐብይ ጾምን የሚጀምሩት በዚሁ ምክንያት ነው።

ዐብይ ጾም በሚጀመርበት ረቡዕ ቀን ግንባርን በአመድ የመቀባት መንፈሳዊ ስነ-ሥረዐት እንዲያው ለይስሙላ የሚደረግ ቀልል ያለ መንፈሳዊ ሥነ-ሥረዓት ሳይሆን ከዚያ በመለጠቅ ለአርባ ቀናት በሚደረገው ጾም ጸሎት ላይ የራሱን አዎናትዊ የሆነ አሻራ ማሳረፍ የሚችል መንፈሳዊ ይዘት ያለው መገለጫ ሲሆን በሰራነው ኃጢአት አዝነን፣ ማቅ ለብሰን፣ በአመድ ላይ ተቀምጠን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በመፈጸምናቸው ኃጢአቶች መጸጸታችንን በእውነተኛ መንፈስ በመግለጽ በእነዚህ አርባ ቀናት ውስጥ ራሳችንን ከኃጢአት በማንጻት መንፈሳዊ ለውጥ በማምጣት በፋሲካ በዓል የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ተካፋዮች ለመሆን ያስችለናል.

የዐመድ መቀባት መንፈሳዊ ሥርዓት ታሪካዊ አመጣጥ

በጥንት ጊዜ በነበረው የሥርዓተ አምልኮ ልማድ መሰረት ምዕመኑ ምስጢረ ንስሐን ያደርግ የነበረው በሕዝብ ፊት በይፋ ኃጢአቱን በመናዘዝ እንደ ነበረ ከታሪክ ለመረዳት የሚቻል ሲሆን ከእዚያም በኃላ በኃጢአቱ መጸጸቱን የሚያመልክቱ መንፈሣዊ ተግባራትን በመፈጸም የሚከናወን ሲሆን ለአርባ ቀናት ያህል በኃጢአቱ መጸጸቱን የሚያመለክቱ ተግባራትን በማከናወን በሕማማት ሳምንት ውስጥ ከሚገኘው ከስቅለተ ዐርብ በፊት ባለው የጸሎተ ሐሙስ ቀን በካህን አማካይነት የኃጢአት ስርሄት ይሰጠው ነበር።

ከዚህ መንፍሳዊ ስርዓት በመነጨ መልኩ ባለፈው አመት አክብረነው በነበረው የሆሳህና በዓል ወቅት “ሆሳህና ለእግዚኣብሔር ልጅ ምስጋና” በማለት የወይራ ዛፍ ዝንጣፊ ይዘን የዘመርንበትን የወይራ ዛፍ ዝንጣፊ ደርቆ እንዲቃጠል ይደረግና ይህ ዐመድ ለአንድ አመት ያህል እንዲቀመጥ ተደርጎ ዐመዱ ዐብይ ጾም ከመጀመሩ በፊት ባለው ረቡዕ ቀን ላይ በሚደረገው የመስዋዕተ ቃዳሴ ሥነ-ሥረዓት ላይ ቅዱስ ወንጌል ተነቦ ስብከት ከተደረገ በኋላ በቀሳውስት አማካይነት በሚደረግ መንፈሳዊ ሥነ-ሥረዓት በምዕመኑ ግንባር ላይ ይቀባል። ይህ አመድ የመቀባት ሥነ-ሥረዓት የሚፈጸመው ምዕመኑ በሰራናቸው ኃጢአት መጸጸቱን እና በትህትና ዝቅ ማለቱን ለመገልጽ እና በቀጣዮቹ 40 ቀናት የዐብይ ጾም ወቅት ውስጥ በጸሎት፣ በጾም እና ምጽዋዕት በመስጠት መንፈሳዊ የሆነ እውነተኛ ለውጥ በማምጣት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳሴ በዓል ወቅት በኃጢአታችን ምክንያት ተቀብረንበት ከነበረው መጥፎ ሕይወት ተላቀን፣ ከኃጢአታችን ነጽተን፣ ከእርሱ ጋር ከሞት ወደ ሕይወት መሻገር የሚያስቸለንን ጸጋ ይሰጠን ዘንድ ይህንን ጸጋ እንድንጎናጸፍ በሚረዳን መልኩ የዐብይ ጾም ወቅትን በተገቢው መልኩ መጠቀም እንድንችል እንዲያስችለን ነው።

ይህ ዐብይ ጾም ከመጀመሩ በፊት በዐመድ ግንባርን የመቀባት መንፈሳዊ ሥረዓት ዐመዱ በጸበል ከተባረከ እና ይህንን መንፈሳዊ ሥነ-ስረዓት በተመለከተ የተዘጋጀው ጸሎት ከተደረገ በኋላ ምዕመኑ በሰልፍ ወደ ካህኑ በመምጣት ካህኑ “አንተ አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ!” የሚለውን ቃል በመድገም በምዕመኑ ግንባር ላይ የተባረከውን እና በጸበል የተለወሰውን አመድ የመስቀል ምልክት በማድረግ የቀባዋል። በዚህ መልኩ የዐብይ ጾም በይፋ መጀመሩ ይገለጻል።

የዐመድ መቀባት ሥነ-ሥረዓት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትርጉም

ዐመድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሁለት ዓይነት ትርጉሞች አሉት። በቅድሚያ የሰው ልጅ በጌታ ፊት ደካማ እና ያልተገባ መሆኑን የሚያመለክት ሲሆን በዚህ ረገድ አብርሃም “እኔ ከንቱ ትቢያና ዐመድ ሆኜ ሳለሁ ከጌታ ጋር ለመነጋገር እንዴት እደፍራለሁ” (ኦዘፍ. 18፡27) በማለት የሰው ልጆች ለእግዚኣብሔር ያልተገቡ ደካሞች መሆናቸውን ይገልጻል። ኢዮብ አበበኩሉ የሰው ልጅ ውስን መሆኑን ለመግለጽ በማሰብ “እርሱ በጭቃ ውስጥ ጣለኝ፥ አፈርና አመድም መሰልሁ” (ኢዮብ 30፡19) በማለት ስብዕናችን ውስን መሆኑ ይገልጻል። በመጽሐፈ ጥበብ ውስጥ ደግሞ “እኛ በከንቱ ተፈጥረናልና፣ ከእዚያን በኋላ እንዳልተፈጠርን እንሆናለን፣ በአፍንጫችን ያለ ትንፋሻችን እንደ ጢስ ነውና። በልቡናችንም እንቅስቃሴ የብል ጭልጭታ ቃል አለና። ከሞት በኃላ ሥጋችን ትቢያ ይሆናል፣ መነፈሳችንም እንደ ጉም ተን የበተናል” (ጥበብ 2፡2-3)። የሰው ልጅ ከአፈር መሰራቱን ወደ አፈር እንደ ሚመለስ የገልጻል። ሲራክ በትንቢቱ “እንግዲህ ትቢያ እና ዐመድ የሚሆን በሕይወትም ሳለ ሰውነት የሚተላ ሰው ስለምን ይታበያል?” (ሲራክ 10፡9) በማለት የትዕቢት መጀመሪያ ሰውን ከእዚኣብሔር እንደ ሚለይ ልቦናውንም ከእግዚኣብሔር እንደ ሚያርቅ፣ ትዕቢት የኃጢአት መጀመሪያ መሆኑን እና በሰው ልጅ ላይ እርኩሰትን የማብዛት አቅም እንዳለው በመግለጽ፣ በተቃራኒው ደግሞ እግዚኣብሔር ትዕቢተኞችን ሰለማይወድ እና ስለሚያጠፋቸው ጭምር ከትዕቢት ርቀን ወደ እግዚኣብሔር እንድመለስ ጥሪ ያቀርባል።

ዐመድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለው ሁለተኛ ትርጉም ደግሞ የሰው ልጅ በሰራው ኃጢአት መጸጸቱን የሚያሳይ ምልክት ነው። ለዚህም በዋቢነት የሚቀርበው ምሳሌ የነቢዩ ዮኖስ ታሪክ ሲሆን ነቢዩ ዮናስ እግዚኣብሔር በላከው መሰረት በወቅቱ በሰሩት ከፍተኛ ኃጢአት ምክንያት ከእግዚኣብሔር ርቀው የነበሩ የነኔዌ ሰዎችን በሰሩት ኃጢአት ምክንያት ተጸጽተው ማቅ ለብሰው በዐድ ላይ ቁጭ እንዲሉ እግዚኣብሔር በዛዘው መሰረት ይህንን የትንቢት ቃል እንደ ነገራቸው የሚታወስ ሲሆን እነርሱም ከነኔዌ ንጉሥ ጭምር ሁሉም በሰሩት ክፉ ነገር እና ኃጢአት ምክንያት ተጸጽተው ማቅ ለብሰው በዐመድ ላይ በመቀመጣቸው የተነሳ እግዚኣብሔር ምሕረትን እንዳደረገላቸው ይታወቃል።  በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳ ነው እንግዲህ ዐብይ ጾምን ከመጀመራችን በፊት ባለው ረቡዕ ቀን የሰው ልጆች ደካሞች፣ ያለእግዚኣብሔር ድጋፍ ከንቱ መሆናችንን በማስተወስ እና በመቀጠልም በኃጢአታችን መጸጸታችንን ለመግለጸ በማሰብ ዐብይ ጾም ከመጀመራችን በፊት በዐመድ ግንባራችንን የምንቀባው በዚሁ ምክንያት ነው።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
26 February 2020, 16:04