የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ 

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ

ክፍል ሦስት

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ በሚል አርእስት በተከታታይ አንድ ዝግጅት በማቅረብ ላይ እንደ ምንገኝ ይታወሳል። በክፍል ሁለት ዝግጅታችን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በማኅበራዊ ጉዳዮች ውስጥ ትሳተፋለች ሲባል በአንድ አገር ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ ትገባለች ማለት እንዳልሆነ ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ መሆኑን፣ ነገር ግን በተለያዩ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ጫናዎች ምክንያት በሰው ልጆች ላይ የሚደርሱትን በደሎች፣ ኢፍታዊ ተግባሮች፣ በተለይም ደግሞ ዝቅተኛ እና ድሃ በሚባሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ የሚደርሰውን በደል በመቃወም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ድምጹዋን ለዓለም እንደ ምታሰማ መግለጻችን ይታወሳል።

በዛሬው እለት በክፍል ሦስት ዝግጅታችን ደግሞ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን “ማኅበራዊ አስተምህሮ” የተሰኘውን አርእስት ውስጥ የሚገኙትን ቃላት አንድ በአንድ በማንሳት ትርጉማቸውን እንደ ሚከተለው እናቀርብላችኋለን። የካቶሊክ ማኅበራዊ አስተምህሮ (Social doctrine of the church) የሚለውን አርእስት በመጠቀም Social (ማኅበራዊ) Doctrine (በግርድፉ ሲተረጎም የእምነት አስተምህሮ) Church (ቤተክርስቲያን) የሚሉትን ቃላት ትርጉባቸውን በአጭሩ እንመለከታለን።

1.     Social ወይም ማኅበራዊ፡ የሚለውን ግስ ስንመለከት ማኅበራዊ የሚለው ቃል በራሱ የአንድ ማኅበረሰብ አመሰራረት እና ማኅበራዊ መዋቅሩን ለየት ባለ ሁኔታ የሚያመለክት ጽንሰ-ሐሳብ ሲሆን በአጠቃላይ የአንድ ማኅበረሰብ መልካም የሆኑ የጋራ እሴቶችን የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥን ሐሳብ ነው። ማኅበረሰብ ስንል በተደራጀ ሁኔታ በጋራ የሚኖሩ በርካታ ሰዎችን የሚያመለክት ሲሆን፣ ይህም በእዚህ ማኅበረሰብ ውስጥ የሚፈጸሙ የጋራ ተግባሮች እና ሥራዎች እንዴት መከናወን እንደ ሚገባቸው በመወሰን የሥራ ክፍፍል በማድረግ የተለያዩ ማኅበራዊ ውሳኔዎች የሚወሰኑበት፣ ሰዎች በጋራ የሚሳተፉበት የሰዎች ስብስብ የሚለውን ትርጉም ያሰማል። በተጨማሪም በአንድ አገር ውስጥ ወይም በአጠቃላይ በሌላ አገራት የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ማኅበረሰብ ተብለው ሊጠሩ ይችላሉ። በአጠቃላይ “ሰዎች በጋራ የሚኖሩበት ሥፍራ እንደ ሆነም ያሳያል” (Cambridge online dictionary፡ 2018፡ ritrieved 02/02/2018) ይህ ትርጉም ከካብሪጂ መዝገበ ቃል የተወሰደ ነው። በጠቃላይ ማኅበረሳባዊ የሆኑ ጉዳዮችን የሚያመለክት ነው። በዚሁ መሰረት ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ በተከታታይ የምትሰጥበት ምክንያት ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደ ሞከርኩት “የሰው ልጆችን ማዕከል” ባደርገ መልኩ ነው። የሰው ልጆች ባሉበት ማኅበረሰብ አለ፣ ማኅበረሰብ ባለበት ደግሞ እምነት አለ፣ እምነት ባለበት ቦታ ደግሞ ቤተ ክርስቲያን አለች፣ ቤተ ክርስቲያን እና ማኅበረሰብ ባሉበት ቦታ ደግሞ መልካም እና ክፉ የሆኑ ነገሮች ይንጸባረቃሉ፣ ቤተ ክርስቲያን ስነ-ምግባራዊ የሆኑ እሴቶች ተጠብቀው እንዲሄዱ፣ ሰዎች በስላም እና በመከባበር እንዲኖሩ፣ መልካም የሆኑ ነገሮችን እና የሰው ልጅ ተፈጥሮአዊ የሆኑ እሴቶችን በማበረታታት በተቃራኒው ደግሞ የማኅበርሰቡን ሰላም የሚነሳውን ክፉ የሆኑ ነገሮችን በብርቱ ትቃወማለች፣ እንዳይስፋፉም በቅዱስ ወንጌል እና ሰብአዊ ምርሆች ላይ የተመሰረቱ አስተምህሮችን ትሰጣለች።

2.     Doctrine (በግርድፉ ሲተረጎም የእመነት አስተምህሮ)፡ Doctrine የሚለው ቃል መስረቱን ያደርገው “Docere” በሚለው የላቲን ቋንቋ ቃል ላይ ሲሆን ይህም ማስተማር የሚለውን ትርጉም ይሰጠናል። ይህም የፖለቲካ፣ የፍልስፍና እና ሃይማኖታዊ አስተሳሰቦችን የተመለከቱ ጽንሰ-ሐሳቦችን ማስተማር የሚለውን ቃል ያሰማል። በተወሰነ የማኅበረሰብ ክፍል ተቀባይነት ያገኙ ፖለቲካዊ እና ሐይማኖታዊ የሆኑ አስተምህሮችን፣ ወይም የእመንት አንቀጾችን፣ ወይም የአንድ ማኅበረሰብ ክፍል ርዕዮተ ዓለም ተቀብሎ ማስተማር ወይም ማራመድ የሚለውን ያሰማል። በእዚህ መሰረት ቤተ ክርስቲያናችን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ፣ በሕገ ቀኖና፣ በእመንት አንቅጽ፣ በትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ፣ የቤተ ክርስቲያን አባቶች በጻፉዋቸው ሐዋሪያዊ መልእክቶች እና ቃለ ምዕዳኖች ላይ በመመስረት በአጠቃላይ ክርስትያናዊ እና ሰብዓዊ የሆኑ እስቶአች ይከበሩ ዘንድ፣ ማኅበረሰቡ በሰላም እና በደስታ በአንድነት ይኖር ዘንድ ታስተምራለች።

3.     Church ወይም (ቤተ ክርስቲያን) የሚለውን ቃል እናገኛለን።  ቤተ ክርስቲያን የሚለው ቃል  Exlexia (ሄክሌዚያ) ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን አጠቃላይ የሆነ ትርጉሙ አንድ አዓይነት እምነት ያላቸው የሰዎች ስብስብን ያመለክታል። በእዚህም መስረት አንድ ዓይነት እመንት ያላቸው ሰዎች የሚመሰርቱት የጋራ ስብስብ ማለት ነው። በአጠቃላይ አንድ እመንት፣ ተስፋ እና ፍቅር በጋራ የሚጋሩ የማኅበረስብ ክፍሎችን ያመልክታል።

አዘጋጅ እና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

27 January 2020, 14:52