ስደተኛን ከሞት አደጋ በማትረፍ ለሕይወት የማብቃት አገልግሎት፣ ስደተኛን ከሞት አደጋ በማትረፍ ለሕይወት የማብቃት አገልግሎት፣  

ካርዲናል ባሴቲ፣ “ለስደተኞች መልካም አቀባበል እና ጥራቱን የጠበቀ መኖሪያ ሊሰጣቸው ይገባል”።

የጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደርት ብጹዕ ካርዲናል ጓልቲዬሮ ባሴቲ፣  ጥር 13/2012 ዓ. ም. በሮም በተካሄደው ስብሰባ ላይ ተገኝተው ባሰሙት ንግግር ስደተኞችን ተቀብሎ ተገቢውን መስተንግዶ መስጠት እና ከሚኖሩበት አገር ማሕበረሰብ ጋር ተጎራብተው እና ተዋድደው መኖር እንዲችሉ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል። ወደ ጣሊያን ለሚደርሱ ስደተኞች የሚደረግ አቀባበል ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ጓልቲዬሮ ባሰቲ ጥራቱን የጠበቀ የስደተኞች ማረፊያ ሥፍራን ማዘጋጀት ያስፈልጋል ብለዋል። በሮም ከተማ  ጥር 13/2012 ዓ. ም. የተካሄደውን ስብሰባ የጣሊያን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ክቡር አቶ ሉቺያኖ ላሞርጌሰ መካፈላቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ስደተኞችን መቀበል፣ ከለላን መስጠት፣ ማበረታታት እና ከማሕበረሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉ ማድረግ፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በ2018 ዓ. ም. በተከበረው ዓለም አቀፍ የስደተኞች ቀን ስደተኞችን መቀበል፣ ከለላን መስጠት፣ ትኩረትን ሰጥቶ ከማሕበረሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉ ማድረግ በሚሉ አራት ርዕሠ ጉዳዮች ላይ በማትኮር መልዕክት ማስተላለፋቸውን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ፣ ስደተኞችን መቀበል፣ ጥበቃን ማድረግ፣ አገልግሎትን ማሳደግ እና ከሚኖሩበት ማሕበረሰብ ጋር ተቀራርበው እንዲኖሩ ማድረግ የተሟላ ማሕበራዊ አገልግሎትን መስጠት የሚጠይቅ መሆኑን አስረድተዋል። ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ አክለውም ለስደተኞች የተሟላ ማሕበራዊ አገልግሎቶችን ማቅረብ ስደተኞች ከሚኖሩበት ማሕበረሰብ ጋር በሚገባ ተዋውቀው፣ ባሕላዊ እና ሐይማኖታዊ እሴቶቻቸውን እንዲለዋወጡ ያግዛል ብለው ይህን ለማመቻቸት የማሕበራዊ ተቋማት የጋራ ጥረት ሊኖር ያስፈልጋል ብለዋል። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን መልዕክት በማስታወስ ንግግራቸውን ያሰሙት ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ፣ እንግዳን ተቀብሎ ማስተናገድ ለስደተኛ እና ለጥገኝነት ጠያቂ ብቻ ሳይሆን ካገሩ ርቆ በችግር ላይ ለሚገኝ ማንኛውም ሰው ሊቀርብ የሚገባ ዕርዳታ ነው ብለዋል።

እያንዳንዱ ነፍስ የተቀደሰ ነው፣

በጣሊያን ውስጥ የሚገኙ አነስተኛ ብድር ሰጭ ተቋማት ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ለማሕበረሰቡ የሚያቀርቡትን አገልግሎት መቋረጡን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ፣ እያንዳንዱ የሰው ልጅ ነፍስ የተቀደሰ በመሆኑ አደጋ ላይ በሚገኝበት ጊዜ ዘወትር መታደግ እንደሚያስፈልግ አሳስበው፣ የአውሮፓ አገሮች ተጋግዘው፣ ሃላፊነትንም ተቀብለው በስደተኞች ዙሪያ የሚከሰቱትን ችግሮች በጋራ መወጣት እንደሚያስፈልግ አሳስበው፣ ችግሩን ለስደተኞች የመጀመሪያ መዳረሻ በሚሆኑ አገሮች ላይ ብቻ መተው ተገቢ አይደለም ብለዋል። ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ አክለውም የስደተኞችን ችግር አንድ አገር ብቻውን እንዲወጣው የሚል አስተያየት በፖለቲካ መሪዎች አካባቢ የሚንጸባረቅ መሆኑን ገልጸው፣ አደጋ ላይ ለሚገኝ ሰው የሚደረግ የመጀመሪያ እርዳታ ፈጽሞ መታገድ የለበትም ብለዋል።

በሐሰት የተሞላ ምኞት፣

ስደተኞች በሚስተናገዱበት አገር የሚጀምሩት አዲስ ሕይወት አስመልክተው አስተያየታቸውን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ፣ ስደተኞቹ በሚሄዱበት አገር ኑሮ ይመቻች ወይም አይመቻች ይሆናል ብለው በሐሰት ምኞት ከመሞላት በፊት በቅድሚያ መገንዘብ ያለባቸው ነገር ቢኖር፣ ለምሳሌ ወደ ጣሊያን በሚደርሱበት ጊዜ ምን ይጠብቀኛል ብሎ ማሰብ መልካም ነው ብለዋል። ካርዲናል ባሴቲ ከዚህ ጋር በማያያዝ ስደተኞች ይዘው ለሚመጡት ልዩ ባሕል እና እምነት እውቅናን እና ዋጋን   የሚሰጥ ማሕበረሰብ መገንባት ያስፈልጋል ብለው፣ ከዚህም በተጨማሪ እያንዳንዱ ሰው እኩል መብት እና ክብር እንዳለው የሚያረጋግጥ ሕጋዊ እና ኤኮኖሚያዊ ማዕቀፍ ሊኖር ያስፈልጋል ብለዋል። የሕዝቦች ከአገር ወደ አገር መሰደድ የሚሰደዱበትን ምክንያት በውል ማወቅን፣ የስደተኞችን ሰብዓዊ መብት ማክበርን፣ ክብራቸውን ማስጠበቅን ይመለከታል ብለው፣ ይህን እውነታ ሁሉም ወገን እንዲያውቀው ማገዝ፣ ሕዝቦች የሚሰደዱበትንም ምክንያት በግልጽ ማስረዳት ያስፈልጋል ብለው፣ ስደተኞችም በበኩላቸው ወደ አውሮፓ በሚደርሱበት ጊዜ የሚያጋጥማቸው ማሕበራዊ ችግሮች መኖራቸውን ቢረዱ መልካም ነው ብለዋል።

ለስደተኞች የሚደረግ ያልተመቻቸ መስተንግዶ፣

ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ወደ አውሮፓ የሚመጡት ስደተኞች ቁጥር መቀነሱን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ፣ ለዚህም ምክንያቱ ለስደተኞች የሚደረግ ያልስተካከለ የጉዞ መስመር እና መስተንግዶ መሆኑን አስረድተው፣ ይህ ብቻ ሳይሆን በቂ የዕለት ቀለብ እና መጠለያ ሥፍራ አለመመቻቸት እና ከሚኖሩበት ማሕበረሰብ ጋር የጠበቀ ግንኙነት አለመኖር መሆኑን ገልጸዋል። ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ አክለውም ስደተኞችን ከሚኖሩበት ማሕበረሰብ ጋር በቀላሉ እንዲቀራረብ የሚያደርግ የቋንቋ ትምህርት እና የሞያ ስልጠና መስጠት አስፈላጊ መሆኑን አስረድተው ይህም ስደተኞች ተጠግተው በሚኖሩባቸው አገራት ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ እንዲያገኙ፣ የበታችነትን ስሜት እንዲያስወግዱ እና በሚኖሩበት ማሕበረሰብ መካከል የተፈጠረውን ስጋት ለማስወገድ ያግዛል ብለዋል።

ስደተኞች ላይ የሚፈጸም የጉልበት ብዝበዛ፣

በጣሊያን ውስጥ በቁጥር ከስድስት መቶ ሺህ እስከ ሰባት መቶ ሺህ የሚደርሱ ስደተኞች ሕጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ የሌላቸው ወይም ከአንድ ጊዜ በላይ የማይታደስ የመኖሪያ ፍቃድ ያላቸው ናቸው ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ፣ የመኖሪያ ፍቃድ የማይታደስላቸው ከሆነ ሕጋዊ ሥራ መሥራት የማይችሉ እና በሕገ ወጥ ሥራ ሲሰማሩ ለጉልበት ብዝበዛ የሚጋለጡ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ዜግነት የማግኘት መብት እንዲከበር፣

ዓለም አቀፍ ሕግን በተከተለ መልኩ እና ሰብዓዊ መብትን ባስጠበቀ አካሄድ፣ ስደተኞችን ለሚደርስ ችግር መፍትሄ ይሆናል በማለት የጣሊያን ሪፓብሊክ መንግሥት ፕሬዚደንት የሆኑት ክቡር አቶ ሴርጆ ማታሬላ ያቀረቡትን የዜግነት መብት ማስጠበቅ ሃሳብ ቤተክርስቲያን በደስታ የምትቀበለው መሆኑን ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ ገልጸው፣ በተለይም በጣሊያን ውስጥ ከሚኖር ስደተኛ ቤተሰብ ለሚወለዱት ሕጻናት የዜግነት መብት ማስጠበቅ ከአገሩ ዜጋ ጋር እኩል መብት እንዲኖር ያስችላል በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያቀረቡትን ሃሳብ አስታውሰዋል። የጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደርት፣ ብጹዕ ካርዲናል ጓልቲዬሮ ባሴቲ በመጨረሻም የስደተኞችን ችግር ለመቅረፍ መንግሥት እና ቤተክርስቲያን በጋራ ሆነው የሚያቀርቡት ማሕበራዊ አገልግሎት በስደተኞች እና በጣሊያን ማሕበረሰብ መካከል ያለውን የባሕል እና የእምነት ሃብት ከማሳደግ በተጨማሪ፣ ስደተኛ ቤተሰቦች ይዘው የመጡትን በርካታ ልምድ ከሚኖሩበት አካባቢ ማሕበረሰብ ጋር እንዲለዋወጡ ያግዛቸዋል ብለዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
23 January 2020, 16:33