የነፍሳችን ቀንደኛ ጠላቶች የነፍሳችን ቀንደኛ ጠላቶች 

የነፍሳችን ቀንደኛ ጠላቶች

የነፍሳችን ቀንደኛ ጠላቶች ሶስት ናቸው፡፡ ሰይጣን፣ ዓለም እና ሥጋችን፡፡ ሰይጣን እና ዓለም ከእኛ ውጪ ሆነው ጦርነት ያካሂዱብናል፤ ሥጋችን ደግሞ በውስጥ ሆኖ ይዋጋናል፡፡ ከነዚህ ከሶስቱ ጠላቶቻችን መካከል በነፍሳችን ላይ ያየለውና የበረውታ ዘወትር የሚፈታተነን ከእኛ ጋር ሁልጊዜ አብሮ የሚጓዘው ሥጋችን ነው፡፡ “ከሁሉ አስቀድሞ ውጊያችን ከሥጋችን ክፉ ምኞች ጋር ነው፤ ቀጥሎ ደግሞ በዚህ አንጻር ከጨለማ ገዢዎች ጋር” ይለናል ቅዱስ አምብሮስዮስ፡፡ እርሱ እንደተናገረው ዓለምንና መንፈሱን እየናቅን ልናሸንፋቸው እንችላለን፡፡ የሥጋችንን ኃይለኛ ፈተናን፣ መጥፎ ዝንባሌውንና አመሉን ማሸነፍ በጣም ከባድና ብርቱ ጥረት የሚጠይቅ ነው፤ ሰይጣንን ደግሞ በጸሎትና በተጋድሎ ልናሸንፈው እንችላለን፡፡ ከአዳም ኃጢአት በፊት ሥጋችን በቁጥጥራችን ሥር በመዋል ይታዘዘን ነበር፡፡ ከአዳም ኃጢአት በኋላ ግን ለነፍሳችን መታዘዝ እምቢ አለ ፈረጠጠ፣ ተቃራኒም መሆን ጀመረ፡፡

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

የነፍሳችን እና የሥጋችን አፈጣጠራቸው የተለየ ነው፡፡ ሥጋችን ምድራዊና ጊዜያዊ ሲሆን ነፍሳችን ግን መንፈሳዊትና ዘለዓለማዊት ናት፡፡ “ከመንፈስ የተወለደ መንፈስ ነው፣ ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው” (ዮሐ. 3፣17) ይለናል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡፡ መንገዳቸው፣ ሐሳባቸውና ፍላጐታቸው የተለያየ ነው፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ በነፍስና በሥጋና አለመግባባትን፣ ተቃራኒ በመሆናቸው የተነሳ ሰለሚያደርጉት ውጊያ ሲናገር እንዲህ ይላል “የሥጋ ምኞት ከመንፈስ ምኞት ጋር ተቃራኒ ነው፣ የመንፈስ ምኞት ከሥጋ ምኞት ጋር ተቃራኒ ነው” መንፈስና ሥጋ እርስ በርሳቸው ይቃረናሉ፡፡ የሥጋ ሥራዎች የታወቁ ሲሆኑ እነርሱም «ዝሙት፣ ርኩሰት፣ መዳራት፣ ጣዖትን ማምለክ፣ ሟርት፣ ጠላትነት፣ ንትርክ፣ ቅንዓት፣ ቁጣ፣ ራስ ወዳድነት፣ ጥላቻ፣ መለያየት፣ አድመኝነት፣ ምቀኝነት፣ ስካር፣ ዘፋኝነት እነዚህን የመሳሰሉ ናቸው፡፡ ይህን የሚያደርግ ደግሞ የእግዚአብሔርን መንግሥት አያይም፡፡

የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች ግን “ፍቅር፣ ደስታ፣ ትእግሥት፣ ደግነት፣ በጐነት፣ ታማኝነት፣ ገርነት፣ ራስን መግዛት” (ገላቲያ 5፡ 16-17) ናቸው፡፡ የሥጋ ፍላጐት ምኞች ከነፍስ ፍላጐትና ምኞች ይበረታል እጅግ ያይላል፡፡ ይህን ለነፍስ መልካምና አስፈላጊ መሆኑን እየተረዳን ብዙ ጊዜ ችላ እንለዋለን፡፡ ለሥጋ ግን ብርቱና ክፉ መሆኑን እያወቅን ዓይናችንን ጨፍነን እናደርገዋለን፡፡ የሥጋ ምኞት ወደ ሞት ሲወስደን የነፍስ ፍላጐት ግን ወደ ሕይወትና ሰላም ያደርሰናል፡፡

“ሥጋቸውን የሚያገለግሉ እግዚአብሔርን ለማስደሰት አይችሉም” (ሮሜ 3፣ 8-12) ይላል ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ፡፡ ቀጥሎ ደግሞ የሚከተለውን ምክር ይሰጠናል፡፡ “ወንድሞች ሆይ ሥጋ በእናንተ ላይ ምንም ሥልጣን የለውም የእናንተ ገዥ አይደለም፡፡ በሥጋ መንገድ እንድትሄዱ የሚያስገድዳችሁን የሥጋችሁን ፍላጐት በመንፈስ ብታሸንፉት ድል ብትመቱ ግን ሕይወት ታገኛላችሁ፡፡ እነዚያ በመንፈስ የሚመሩ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው፡፡ እግዚአብሔር ሥጋችንን ለነፍሳችን እንዲታዘዝላትና እንዲያከብራት ሲል የፈጠረው ጓደኛዋና አጋዥ እንዲሆን ነው፡፡ እንግዲህ ሥጋችን አምላክ የሰጠውን ውሳኔ እንዲጠብቅ እናደርግው መንፈሳዊ መወዳደሪያና መሰናከያ እናድርግለት፡፡   

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
13 December 2019, 16:01