በሊባኖስ ውስጥ ከተካሄዱ ሕዝባዊ የተቃውሞ ሰልፎች መካከል፣ በሊባኖስ ውስጥ ከተካሄዱ ሕዝባዊ የተቃውሞ ሰልፎች መካከል፣ 

ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በሊባኖስ ፍትህ እና የአስተዳደር ግልጽነት እንዲኖር ተማጸነች።

በሊባኖስ ውስጥ ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ በመካሄድ ላይ ባለው የሕዝብ አመጽ እና የተቃውሞ ሰልፎች በርካታ ሰዎች መጎዳታቸው እና ለእስር መዳረጋቸው ታውቋል። የሰልፉ ዋና ዓላማ በሀገሪቱ ውስጥ የታየውን ኤኮናሚ ቀውስ በመቃወም መሆኑ ታውቋል። በሊባኖስ የአንጾኪያ ማሮናዊያን ስርዓተ አምልኮን የምትከተል ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በሃገሪቱ የፖለቲካ ግልጽነት እንዲኖር በማለት ጠንካራ አቋሟን የገለጸች ሲሆን፣ በሃገሪቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ልዩ ልዩ የፖለቲካ ቡድኖች ከመንግሥት ጋር እንዲመክሩ በማስተባበር እንዲሁም ለችግር የተጋለጡትን በመርዳት ላይ መሆኗ ታውቋል። 

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሊባኖስ የአንጾኪያ ማሮናዊያን ስርዓተ አምልኮን የምትከተል ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ካርዲናል ቤካራ ቡትሮስ ራይ፣ ለአገሪቱ የፖለቲካ መሪዎች ባቀረቡት ጥሪ በአገሪቱ ለተስፋፋው ሙስና እና ብልሹ አስተዳደር ሃላፊነትን ወስደው የተከሰተውን የፖለቲካ እና የኤኮኖሚ ቀውስ የሚያረጋጋ አስተዳደርን በመዘርጋት መፍትሄን እንዲያገኙ ጥሪ አቅርበዋል። የፓትርያርኩ የውጭ ግንኙነት ምክትል ጸሐፊ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሳያ በበኩላቸው ካለፉት ሁለት ወራት ጀምሮ በመካሄድ ላይ ባለው የተቃውሞ ሰልፍ ሕዝቡ ወደ መተባበር መድረሱን ገልጸው ወደ አደባባይ የወጣበትንም ምክንያት ገልጸዋል። ሊቀ ጳጳስ ፖል ሳያ በገለጻቸው በሃገሪቱ ረጅም ጊዜን ያስቆጠረ ሙስና መኖሩን፣ ከሐይማኖት አባቶች የሚቀርበውን አቤቱታ እና የሕዝብ ብሶት መንግሥት ችላ ማለቱን ተናግረዋል። ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሳያ በማከልም ድህነት ሊባኖስን እጅግ መጉዳቱን ገልጸው ባሁኑ ጊዜ ሊባኖስ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የአጎራባች አገሮች ስደተኞችን ማስተናገዷ በቅድሚያ የሚነገሩ ርዕሠ ጉዳዮች መሆናቸውን አስረድተዋል። ሃገሪቱ ካላት አራት ሚሊዮን ዜጎች ሌላ ሁለት ሚሊዮን ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች መኖራቸው የተናገሩት ሊቀ ጳጳስ ፖል ሳያ የሥራ አጥ ቁጥርም 30 ከመቶ በላይ የሆነባትን ሊባኖስ ድህነት እያጠቃት መሆኑን አስረድተዋል። በማከልም ሃገሪቱ በዚህ ሁኔታ ላይ ባለችበት ወቅት መንግሥት የግብር መጠንን መጨመሩ ሕዝቡን አስቆጥቷል ብለዋል። መንግሥት እንዲወርድ የሚለውን የሰልፈኛ ጥያቄ መንግሥት ቢቀበልም ለ45 ቀናት ያህን አዲስ መንግሥት አልተቋቋመም ብለው የሕዝቡ የኑሮ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን ሊቀ ጳጳስ ፖል ሳያ አስረድተዋል።

በዚህ መካከል የቤተክርስቲያን ሚና ምንድር ነው?

የሕዝብን አመጽ ተከትሎ የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ካርዲናል ቤካራ ቡትሮስ ራይ፣ በሊባኖስ የሚገኙትን አብያተ ክርስቲያናት ማለትም የካቶሊክ፣ የኦርቶዶክስ እና የወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መሪዎችን ለስብሰባ መጥራታቸውን ሊቀ ጳጳስ ፖል ሳያ ገልጸዋል። በስብሰባቸው ማጠቃለያ ላይ ባወጡት የአቋም መግለጫ፣ የሕዝቡን ጥያቄ ትክክለኛነት አረጋግጠው ለተቀሰቀሰው አመጽ የሕዝብ እንቅስቃሴ ተጠያቂ ሊሆን አይችልም ብለዋል። ብጹዕ ካርዲናል ቤካራ ቡትሮስ ራይ በሃገሪቱ ውስጥ የሚከሰቱ ማሕበራዊ ችግሮችን በቅርብ በመከታተል፣ ሕዝቡ ላይ የሚደርሱ በደሎችን ወደ ከፍተኛ የመንግሥት ተወካዮች ዘንድ በማቅረብ ድምጻቸውን ሲያሰሙ መቆየታቸውን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሳያ ገልጸዋል።

የተቃውሞ ሰልፍ ሕዝብን ያስተባብራል፣

በሊባኖስ የተቀሰቀሰው አመጽ የተለያዩ ሕዝባዊ እና መንፈሳዊ ማሕበራትን አንድ አድርጓቸዋል ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሳያ በዚህ የተቃውሞ ሰልፍ ሕዝቡ ድምጹን በማስተባበር በአገሪቱ እየተስፋፋ የመጣው ሙስና እና ብልሹ አስተዳደር እንዲያበቃ፣ በሃገሪቱ ፍትሐዊ እና ግልጽ ኤኮኖሚያዊ መዋቅር እንዲዘረጋ ጠይቀዋል።

ቤተክርስቲያን አስታራቂ ናት፣

በሊባኖስ የአንጾኪያ ማሮናዊያን ስርዓተ አምልኮን የምትከተል ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ካርዲናል ቤካራ ቡትሮስ ራይ የሕዝቡን ብሶት ወደ መንግሥት መሪዎች እንደሚያቀርቡ ገልጸው ይህን በማድረጋቸው በሕዝቡ ዘንድ አመነታን ያገኙ መሆናቸውን ብጹዕ አቡነ ፖል ሳያ አስረድተዋል። ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በሊባኖስ ውስጥ በሕዝብ እና በመንግሥት መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት የአስታራቂነት አገልግሎቷን በማበትርከት ላይ እንደምትገኝ ገልጸው በልዩ ልዩ የፖለቲካ ቡድኖች ማካከል ለሚታየው አለመግባባት የመፍትሄ መንገዶችን በመጠቆም ለእርቅ የምታቀርባቸው መሆኑን ገልጸዋል። 

የመንግሥት ስልጣንን ያለ ብቃት መያዝ፣

አዲስ መንግሥት እንዲመሠረት ከሕዝቡ የሚቀርብ ጥያቄ ብዙ ነው ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሳያ ነገር ግን እስካሁን ድረስ ከመንግሥት በኩል የተሰጠ ምላሽ አለመኖሩን ገልጸው፣ የሕዝቡ ስሜት አሁን በመንግሥት ስልጣን ላይ የሚገኙት አባላት የአስተዳደር ብቃት የሚያንሳቸው፣ ሃገሪቱ የምትገኝበት የፖለቲካ እና የኤኮኖሚ ቀውስ ምንም የማያስጨንቃቸው የሚል መሆኑን ብጹዕ አቡነ ፖል ሳያ አስረድተዋል።

ለደሆች መጨነቅ፣

ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በችግር ውስጥ ለወደቁት ዜጎች ዕርዳታን በማዳረስ አገልግሎት ላይ ተሰማርታ ትገኛለች ያሉት ብጹዕ አቡነ ፖል ሳያ በሥራ ማጣት ምክንያት የርካታ ቤተሰብ ሕይወት በአደጋ ላይ የሚገኝ መሆኑን አስረድተዋል። በመሆኑም በሃገሪቱ የእርዳታ አገልግሎቶችን በማበርከት ላይ የሚገኙ ወደ 40 የሚጠጉ ካቶሊካዊ ድርጅቶችን በማስተባበር የተቸገሩትን ለመርዳት ዕቅድ መያዙን ሊቀ ጳጳሳ ብጹዕ አቡነ ፖል ሳያ አስረድተዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
18 December 2019, 15:21