የታኅሳስ 05/2012 ዓ.ም 1ኛ የስብከተ ገና ሳምንት ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የታኅሳስ 05/2012 ዓ.ም 1ኛ የስብከተ ገና ሳምንት ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ 

የታኅሳስ 05/2012 ዓ.ም 1ኛ የስብከተ ገና ሳምንት ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የስብከተ ገና ወቅት ከተጠናወተን የግድዬለሽነት መንፈስ ነጻ የምንወጣበት ወቅት ነው!

የእለቱ ምንባባት

1.     ኢሳያስ፡ 2:1-5

2.    መዝ. 121

3.    ሮም 13፡11-14

4.    ማቴ. 24፡37-44

የእለት ቅዱስ ወንጌል

ልክ በኖኅ ዘመን እንደሆነው የሰው ልጅ መምጣትም እንደዚሁ ይሆናል፤ ከጥፋት ውሃ በፊት ኖኅ ወደ መርከቡ እስከገባበት ቀን ድረስ ሰዎች ሲበሉና ሲጠጡ፣ ሲያገቡና ሲጋቡ እንደ ነበሩ፣ እስከዚያ ጊዜ ድረስም ምን እንደሚመጣ ሳያውቁ ድንገት የጥፋት ውሃ እንዳጥለቀለቃቸው፣ የሰው ልጅ ሲመጣም እንደዚሁ ይሆናል። በዚያን ጊዜ ሁለት ሰዎች በዕርሻ ላይ ይውላሉ፤ አንዱ ይወሰዳል፤ ሌላው ይቀራል። ሁለት ሴቶች በወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዷ ትወሰዳለች፣ ሌላዋ ትቀራለች።

“እንግዲህ ጌታችሁ የሚመጣበትን ቀን ስለማታውቁ ነቅታችሁ ጠብቁ። ይህን ልብ በሉ፤ ባለቤት ሌሊት ሌባ በየትኛው ሰዓት እንደሚመጣ ቢያውቅ ኖሮ፣ በነቃ፣ ቤቱም እንዳይደፈር በተጠባበቀ ነበር። የሰው ልጅም ባላሰባችሁት ሰዓት ይመጣልና እናንተም እንደዚሁ ዝግጁ ሁኑ።

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

ዛሬ የመጀመሪያው የስብከተ ገና ሳምንት እና እንዲሁም አዲሱ የዓመቱ የስረዓተ አምልኮ አቆጣጠር ስረዓት ይጀመራል። በስበከተ ገና ሣምንታት ውስጥ የሚደረጉት ሥርዓተ አምልኮዎች በእያንዳንዱ ቀን ኢየሱስ ወደ ሕይወታችን ውስጥ እንደ ሚመጣ እና እርሱም በኋለኛው ዘመን በክብር እንደ ሚመጣ፣ እኛን በማስታወስ በእዚህ በአራት ሳምንታት ውስጥ ኢየሱስ የሚወለድበትን ቀን በአግባቡ እንድናከብር ያደርገናል። ይህ እርግጠኝነት ነቢዩ ኢሳያስ እንደተናገረው ከእርሱ አፍ በሚወጣው ድምጽ በመታገዝ በእዚህ በያዝነው የስብከተ ገና ወቅት ጎዞ ላይ ከእኛ ጋር በመሆን የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት እንድንጠባበቅ ያደርገናል።

ዛሬ በተነበበው የመጀመሪያው ምንባብ ውስጥ ነቢዩ ኢሳይያስ “በዘመኑም ፍጻሜ፣ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተራራ ከተራሮች ከፍ ብሎ ይመሠረታል፤ ከኰረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፤ ሕዝቦችም ሁሉ ወደዚያ ይጐርፋሉ” (ኢሳ 2፡2) በማለት ያቀረበውን ትንቢት አዳምጠናል። በኢየሩሳሌም ያለው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሁሉም ህዝቦች መሰባሰቢያ እና የሚገናኙበት መዕከላዊ የሆነ ሥፍራ እንደ ሆነ ሆኖ ቀርቡዋል። የእግዚአብሔር ልጅ ሥጋ ለብሶ ከተወለደ በኋላ ፣ ኢየሱስ ራሱ እንደ እውነተኛው ቤተ መቅደስ ራሱን በእዚያው ስፍራ ይገልጻል። ስለዚህ ነቢዩ ኢሳያስ አስደናቂ ራዕይ መለኮታዊ ተስፋን ለእኛ በመግለጽ እንደ መንፈሳዊ ነጋዲ በመሆን ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚደረገውን ጉዞ በእዚህ መልኩ እንድናከናውን ይመራናል። ፍትህ የተራቡ እና የተጠሙ ሰዎች ስንት ናቸው! እነዚህን ነገሮች ማግኘት የሚቻለው ደግሞ የጌታን መንገድ በመከተል ብቻ ነው፣  ግጭትና ኃጢአት ወደ እዚህ ምድር የሚመጣው ግለሰቦች እና ማህበራዊ ቡድኖች ግጭቶችን እና ጦርነቶችን የሚያስከትሉ በራስ ወዳድነት ፍላጎቶች የተያዙ ዱካዎችን መከተል ስለሚመርጡ ነው። መጪው ጊዜ የእግዚአብሔርን መንገድ ሊያሳየን የሰላም መልእክተኛ ሆኖ የሚመጣውን የኢየሱስን መምጣት ለመቀበል ትክክለኛ ጊዜ ነው።

በዛሬው ቅዱስ ወንጌል (ማቴ 24፡33-44) ውስጥ  “ጌታችሁ በየትኛው ቀን እንደሚመጣ አታውቁምና ተዘጋጅታችሁ ኑሩ” (ማቴ 24፡44) በማለት ለመጪው ጊዜ ዝግጁ እንድንሆን ኢየሱስ ያሳስበናል። ነቅቶ መጠበቅ ማለት እንዲያው በግርዱፉ በአካላችን ላይ የሚገኘውን ዓይናችንን ገልጠን ወይም ከፍተን መጠበቅ ማለት አይደለም፣ ነገር ግን ልባችንን ነፃ ማደረግ እና በትክክለኛው አቅጣጫ ላይ መጓዝ፣ ማለትም ለጋሽ ለመሆን እና ለማገልገል ፈቃደኛ መሆን ማለት ነው። ይህ ነቅቶ መጠበቅ ይባላል! እኛ ልንነቃበት የሚገባው የእንቅልፍ ዓይነት መሆን የሚገባው የግድዬለሽነት፣ ከንቱነት ፣ እውነተኛ በሆነ መልኩ ከሰዎች ጋር ግንኙነቶችን መመሥረት ካለመቻል፣ በብቸኝነት፣ በሽታ የሚሰቃየውን፣ ገለልተኛ የሆነውን ወንድማችንን እንዳንቀርብ ከሚያደርገን እነዚህን ከመሳሰሉ የእንቅልፍ ዓይነቶች መንቃት ይኖርብናል። ስለዚህ የሚመጣውን ኢየሱስ በተስፋ ንቅቶ መጠበቅ ማለት ቁርጠኛ ወደ ሆነ አግልግሎት መተርጎም አለበት። ከሁሉም በላይ ጥያቄው ለእግዚአብሔር ሥራ፣ ለእርሱ ድንቅ ተግባር ቅድሚያ መስጠት ማለት ነው። ነቅቶ መጠበቅ ማለት ደግሞ፣ በእውነቱ በችግር ውስጥ የሚገኙትን ባለእንጀሮቻችንን በትኩረት መከታተል፣ የእነርሱን ችግር የእኛ በማድረግ ችግሮቻቸውን ለመፍታት መሞከር፣ እነርሱ ማለትም በችግር ውስጥ የሚገኙ እህት ወንድሞቻችን ጥሪ እስኪያደርጉልን ድረስ ሳንጠብቅ፣ እግዚኣብሔር ለእኛ እንደ ሚያደርገው ዓይነት እኛም ችግሮቻቸውን ቀድመን በመተንበይ እና በመረዳት ከጎናቸው ልንሆን ይገባናል።

ንቁ እና የተስፋ እናት የሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የኢየሱስ መገለጫ ወደ ሆነው “የጌታ ተራራ ላይ” ትኩረታችንን ሙሉ በሙሉ ማደረግ እንችል ዘንድ ወደ እዚያው በምናደርገው ጉዞ ትደግፈን ዘንድ እንድትመራን አማላጅነቷን ልንማጸን ይገባል።

ምንጭ፡ ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮስ በኅዳር 21/2012 ዓ.ም ካደረጉት አስተንትኖ የተወሰደ።

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

14 December 2019, 10:19