+ ካርዲናል ብርሃነየሱስ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት፣ + ካርዲናል ብርሃነየሱስ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት፣ 

ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የደስታ መግለጫ መልዕክት ላኩ።

ለክቡር ዶ/ር አብይ አህመድ

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ

ጉዳዩ፡ የደስታ መግለጫ

“በሰዎች መካከል ዕርቅና ሰላም የሚያደርጉ የእግዚአብሔር ልጆች ስለሚባሉ የተባረኩ ናቸው” (ማቴ 5፡9)

እጅግ የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር አብይ አህመድ

በሀገራችን እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ ዙሪያ ለሰሯቸው የሠላም እና የእርቅ ሥራዎችዎ እውቅና በመስጠት የኖቤል የሰላም ሽልማት ኮሚቴ በያዝነው እ.ኤ.አ. 2019 ዓ.ም. 100ኛ ተሸላሚ አድርጎ እርስዎን በመምረጡ ቤተክርስቲያናችን ታላቅ ደስታ ተሰምቷታል፡፡ ሰላም የሁሉ ነገር መሠረት መሁኑን ገና ከጅምሩ ተረድተው በኢትዮጵያውያን መሀል ሰላም እንዲሰፍን እንዲሁም ከጎረቤት አገሮች በተለይ ከኤርትራ ጋር የነበረንን የዝምታ ዘመን ሰብረው በህዝቦች መሀከል ሰላም እንዲሰፍን ለሠሩት ሥራ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ማግኘት ለእኛ ለኢትዮጵያውያን እንዲሁም ለመላው አፍሪካ ኩራት ነው፡፡

ለሀገራችን ቀጣይ እድገት እና ለጀመሯቸው የሰላምና የእርቅ ጉዞ ውጤታማነት ቤተክርስቲያናችን የበኩሏን አስተዋጽዖ ለማበርከት ከጸሎት ጀምራ በምትችለው ሁሉ ከጎንዎ ትቆማለች፡፡

በድጋሚ ለዚህ ታላቅ ሽልማት በመብቃትዎ እርስዎንና ቤተሰብዎን እንኳን ደስ ያላችሁ እያልን የሰላም መሳሪያ እንዲሆኑ የሾመዎት የኢትዮጵያ አምላክ አገልግሎትዎትን ይባርክ፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ያባርክ!

+ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት

የብሔራዊ እርቀ ሠላም ኮሚሽን ሰብሳቢ

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

 

12 October 2019, 16:35