የአፍሪቃ ካቶሊካዊ ጋዜጠኞች ስልጠና፤ የአፍሪቃ ካቶሊካዊ ጋዜጠኞች ስልጠና፤  

የቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት፣ የአፍሪቃ ካቶሊካዊ ጋዜጠኞችን ማበረታታቱ ተገለጸ።

የቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት፣ በአፍሪቃ በምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የሚሰሩ የቤተክርስቲያኒቱ ጋዜጠኞች በሙሉ የሰላም መልዕክተኞች እንዲሆኑ አሳሰበ። ጽሕፈት ቤቱ ይህን ያሳሰበው፣ የአፍሪቃ ካቶሊካዊ ጋዜጠኞች ማሕበር፣ በአይቮሪ ኮስት ዋና ከተማ በአቢጃን፣ ከነሐሴ 2-10 ቀን 2011 ዓ. ም. ባዘጋጀው ስልጠና ወቅት መሆኑን የቫቲካን ዜና ዘጋቢ ባርባራ ካስቴሊ የላከችልን ዜና አመልክቷል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የአፍሪቃ ካቶሊካዊ ጋዜጠኞች ማሕበር እና የአይቮሪ ኮስት ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጋዜጠኞች ማሕበር በጋራ ሆነው ባዘጋጁት ስልጠና ላይ ለተሳተፉት ካቶሊካዊ ጋዜጠኞች መልዕክታቸውን የላኩት፣ የቅድስት መንበር የመገናኛ ክፍል ተጠሪ፣ ክቡር አቶ ፓውሎ ሩፊኒ፣ በአፍሪቃ ውስጥ የሚገኙ ካቶሊካዊ ጋዜጠኞች ለሚያበረክቱት የሰላም ጥረቶች ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ የቤተክርስቲያኒቱ ጋዜጠኞች እስካሁን ባስመዘገቧቸው መልካም ውጤቶች የተደሰቱ መሆናቸውንም ተናግሯል። በአይቮሪ ኮስት ዋና ከተማ በአቢጃን በመካሄድ ላይ የሚገኘውን ስልጠና በንግግር የከፈቱት፣ በአይቮሪ ኮስት፣ የግራንድ ባሳም ሀገረ ስብከት ጳጳስ እና በአይቮሪ ኮስት ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ውስጥ የማሕበራዊ መገናኛ ምክር ቤት ተጠሪ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ራይሞንድ ኦውዋ፣ የስልጠናው ርዕስ፣ “በአፍሪቃ የምርጫ ሂደቶች፣ ማሕበራዊ ሰላምን በማስጠበቅ የብዙሃን መገናኛዎች ሃላፊነት እና ሚና የሚል መሆኑን ገልጸዋል።

ከሰዎች ለሰዎች የሚውል ጋዜጠኝነት፣

በቅድስት መንበር የመገናኛ ክፍል ተጠሪ የሆኑት ክቡር አቶ ፓውሎ ሩፊኒ ለስልጠናው ተካፋዮች በላኩት መልዕክታቸው፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ 52ኛውን ዓለም አቀፍ ማሕበራዊ መገናኛ ቀን ምክንያት በማድረግ ያስተላለፉትን መልዕክት በመጥቀስ እንደገለጹት፣ ሰላምን የሚፈጥር ጋዜጠኝነትን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አሳስበው፣ ትክክለኛ ጋዜጠኛ የሚባለው ችግሮች እየተስፋፉ መምጣታቸውን እየተመለከተ የችግሩን አስከፊነት በመሰወር፣ ጥሩ ጥሩ የሆነውን ብቻ በመዘገብ ለማረጋጋት የሚሞክር ሳይሆን፣ ወደ ሕዝቡ መድረስ ያለባቸው መረጃዎች ተረስተው እንዳይቀሩ በማድረግ፣ የችግሮች ትክክለኛ መነሻ የሆኑ ምክንያቶችን በጥልቀት መርምሮ በማውጣት፣ አመጽ እና ጦርነት እንዲገታ የሚያደርግ ጋዜጠኛ የሚያስፈልግ መሆኑን አስረድተዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
13 August 2019, 17:27