ወጣቶች በሜጁጎሪ የወጣቶች ክብረ በዓል በላይ፤ ወጣቶች በሜጁጎሪ የወጣቶች ክብረ በዓል በላይ፤ 

ቅዱስ ወንጌል፣ የሰው ልጆች በሙሉ ነጻነትን እንዲያገኙበት የተሰጠ ስጦታ ነው።

በቦስኒያ ሄርዘ ጎቪና፣ በሜጁጎሪ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የንግደት ስፍራ፣ ዓመታዊው የወጣቶች ክብረ በዓል መከበሩ ታውቋል። ዘንድሮ ለ30ኛ ጊዜ የተከበረውን ክብረ በዓል ከተለያዩ የዓለማችን አካባቢዎች የመጡ በቁጥር ከ50.000 በላይ ወጣቶች መካፈላቸው ታውቋል። ለስድስት ቀናት በጸሎት በዝማሬ እና በመንፈሳዊ ትምህርቶች በመታገዝ የተከናወነው ይህ ይወጣቶች ክብረ በዓል ዛሬ ማክሰኞ ሐምሌ 30/2011 ዓ. ም. ከመጠናቀቁ አስቀድሞ ትናንት በቀረበው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ስነ ስርዓት ላይ የወንጌል አስተምህሮአቸውን ያሰሙት፣ በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚዳንት፣ ብጹዕ ሞንሲኞር ሪኖ ፊዚኬላ “የክርስቲያን ፍቅር ለሰው ሕይወት ትርጉም እንዲሰጥበት፣ የሞት ግድግዳን ተሻግረን ለመሄድ የሚያስችለን መንገድ ነው” በማለት አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ በስብከታቸው፣ መልካም ዜናን ለማብሰር በምንሽቀዳደምበት ወቅት በትህትና እና በአክብሮት፣ የቅዱስ ወንጌልን ውበት ገልጦ በማሳየት፣ ከእግዚአብሔር የራቁት ሰዎች ልብን እና አእምሮን የሚነካ መሆን አለበት በማለት፣ በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚዳንት፣ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ፣ ለወጣቶች ባስተላለፉት መልዕክታቸው አስገንዝበዋል። ዛሬ ሐምሌ 30/2011 ዓ. ም.፣ ጠዋት በክሪዠቫክ ተራራ ላይ በሚቀርብ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ስነ ስርዓት፣ በዓሉ የሚጠናቀቅ መሆኑን የቫቲካን ዜና አገልግሎት ባልደረባ፣ ቤነዴታ ካፔሊ የላከችልን ዘገባ አመልክቷል።

ለጸጋ ስጦታ ልብን መክፈት ያስፈልጋል፣

በሐዋርያት ሥራ በምዕ. 8. ከቁ. 26 ጀምሮ የተጻፈውን እና ሐዋርያው ፊሊጶስ ኢትዮጵያዊውን ጃንደረባ እንዳጠመቀው የሚገልጸውን በመጥቀስ ለወጣቶች ስብከተ ወንጌልን ያቀረቡት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ፣ ሰዎች የኢየሱስ ክርስቶስን መልካም ዜና አብሳሪዎች እንዲሆኑ፣ እግዚአብሔር በታላቅ ሥራው ልባቸውን የሚከፍት መሆኑን አስረድተዋል። ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፊዚኬላ ከዚህ ጋር በማማያዝ፣ “ቅዱስ ወንጌል፣ የሰው ልጆች በሙሉ ነጻነትን እንዲያገኙ በማለት ከእግዚአብሔር የተሰጠ ስጦታ ነው” ብለው “ለሕይወታቸው ሙሉ ትርጉም መስጠት ለሚፈልጉ፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከላቸውን የጸጋ ስጦታ በደስታ ለመቀበል ልባቸውን ከፍተው ለሚጠብቁት በሙሉ የተላከ ነው” ብለዋል።

ቅዱስ ፊሊጶስ የወንጌል ሰባኪ ነው፣

ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ቅዱሳት መጽሐፍትን አንብቦ የመረዳት ችሎታ አነስተኛ መሆኑ፣ በዘመናችንም ከሚታየው ሐቅ የራቀ አይደለም ያሉት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፊዚኬላ፣ ሐዋርያው ፊሊጶስ ግን ለኢትዮጵያዊው ቅዱሳት መጽሐፍትን እንዲያብራራለት   ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከ፣ ወንጌልን ለመስበክ ልባዊ ፍላጎት ያደረበት፣ ይህንንም ለማከናወን በቆራጥነት የተነሳ አዲስ የወንጌል ልኡክ ነው ብለዋል። “መልካም ዜናን ለማብሰር በምንነሳበት ጊዜ ለወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ትህትናን ማሳየት፣ ክብርንም መስጠት አስፈላጊ ነው ብለው ምክንያቱን ሲገልጹ፣ መልካም ዜናን ለምንመሰክርላቸው በሙሉ ትህትናን ማሳየት፣ ክብርንም መስጠት ያስፈለገበት ምክንያት ነጻነታቸውን በሙላት መጠቀም እንዲችሉ መንገድ ስለምንከፍትላቸው ነው ብለው ሐዋርያው ፊሊጶስም ኢትዮጵያዊውን የቀረበው በዚህ መልክ ነበር ብለዋል። ይህን ካደረገ በኋላ በፍቅር እና በእምነት ተነሳስቶ፣ የኢየሱስ ክርስቶስን አዳኝነት መስክሮለታል ብለዋል። ሐዋርያው ፊሊጶስም ያያቸውንና የሰማቸውን ሁሉ በጥበብ እና በማስተዋል መናገር የቻለው የእግዚአብሔር ልጅ ስለሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚናገር ስለሚያውቅ፣ እርሱንም ለማገልገል እንደተነሳ ከልብ ያውቅ ስለነበር ነው ብለዋል።

የተጠመቁት በሙሉ ማድረግ ያለባቸው አዲስ ግዴታ፣

በመንፈስ ቅዱስ በመመራት የወንጌል ምስክርነቱን ለኢትዮጵያዊው ያቀረበው ሐዋርያው ቅዱስ ፊሊጶስ፣ የዚህን ሰው ልብ እና አእምሮን መማረክ የቻለው የሕይወት ምስክርነትም በማሳየት መሆኑን ያስረዱት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፊዚኬላ፣ በሐዋርያው ቅዱስ ፊሊጶስ ምስክርነት የተማረከው ኢትዮጵያዊ፣ ካደረበት የመጠመቅ ፍላጎት በተጨማሪ የወንጌል አብሳሪም ለመሆን በቅቷል ብለዋል። ለመንፈስ ቅዱስ መታዘዝን ከእነዚህ ሰዎች እንማር፣ መንፈስ ቅዱስ የሚያሳየንን መንገድ እንከተል፣ እግዚአብሔርን ለማግኘት ትልቅ ምኞት ያደረባቸውን ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ለማግኘት እንነሳ፣ የመዳንን እና የምሕረት ቅዱስ ቃሉን እንመስክር። ይህ ቃልም የፍቅር ምንጭ የሆነው፣ የእግዚአብሔር አምሳል፣ ለእኛ ሲል የሞተው እና ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው እንደሆነ አስረድተዋል።

ሰው የመሆን ምስጢር ነው፣

“ለመሆኑ ሰው ማነው? ከእግዚአብሔር ጋር የሚያገናኘው ምንድር ነው”?  በማለት ጥያቄአቸውን ያቀረቡት፣ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ፣ ሰው ሁል ጊዜ በሳይንስ ሲመራ የኖረ፣ ጽንስን ሳይቀር በሚፈልገው መንገድ መመራመር የቻለ ነው ብለው፣ በዚህን ጊዜ የእምነት ምሳሌ የሆነች፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን መመልከት እንደሚያስፈልግ አሳስበው፣ እርሷ የእግዚአብሔር ታዛዥ፣ የተጠራችበትንም ምክንያት ማወቅ የፈለገች እና ስብዕናዋንም ጥልቅ በሆነ ምስጢራዊ መንገድ መረዳት የቻለች መሆኗን አስረድተዋል። የሰው ልጅ ለራሱም ምስጢር እንደሆነ፣ ሕይወቱ እና ሞቱ ብቻ የራሱን ማንነት እንዲያውቅ፣ እንቆቅልሹንም እንዲፈታው ያስችላል ብለዋል። “የሰው ልጅ የራሱን ማንነት ለመግለጽ የሚያስችል እንቆቅልሽን መፍታት ቢችል ኖሮ፣ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚወስደው ጎዳና ላይ ራሱን ማስቀመጥ ይችል ነበር። ነፃ ሆኖ እንዲኖር ወደ ሚያስችልበት ደረጃ ሊደርስ ይችል ነበር። የተለያዩ እንቅፋቶችን አልፎ የሕይወቱን ትርጉም ወደ ማወቅ ሊደርስ ይችል ነበር” ብለዋል። 

የሕይወትን ትርጉም ማወቅ እፈልጋለሁ፣

በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚዳንት የሆኑት ብጹዕ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ፣ እውነተኛ የሕይወት ትርጉምን ለማወቅ፣ ሕይወትን ዞር ብለን መመልከት እና ማዳመጥ፣ በእውነተኛ የልብ መለወጥ፣ በፍቅር መኖር መቻል አለብን ብለዋል። የሕይወትን ትርጉም ማወቅ የሚቻለው ምንም ዓይነት ግንኙነት ከሌለን ዓለም ጋር ራሳችንን በማዛመድ ሳይሆን በታሪክ እና በባሕል ውስጥ ራሳችንን አስገብተን መመልከት ስንችል ነው ብለዋል።

የሕይወታችን ትርጉም የሚታወቀው እምነት ሲኖረን ነው፣

ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ገላቲያ ሰዎች በጻፈው መልዕክቱ፣ በምዕ. 2. 19 “አሁንም በሥጋ የምኖረው ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን አሳልፎ በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለኝ እምነት ነው” ያለውን ያስታወሱት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፊዚኬላ፣ መላውን ትውልድ ወደ ጥፋት የሚመራውን ባዶ ሕይወት ማስወገድ እንዲቻል፣ ካህናትን ጨምሮ፣ ወድደፊት ሊመጣ የሚችለውን ጥፋት መመልከት ለሚችሉት በሙሉ ጥሪያቸውን አቅርበውላቸዋል።

የፍቅር ማኅተም፣

ማፍቀር እና መፈቀር ምን ትርጉም አለው በማለት ጥያቄያቸውን ያቀረቡት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፊዚኬላ፣ ጥያቄው ከባድ ቢሆንም ለመመለስ ትንሽ ሙከራ በማድረግ ብቻ የሕመምን እና የሞትን ምንነት መረዳት ይቻላል ብለዋል። በመሐልየ መሐልይ ምዕ. 8. 6 ላይ “ፍቅር እንደ ሞት የበረታች ናት” ተብሎ የተጻፈውን የጠቀሱት ብጹዕ አቡነ ፊዚኬላ፣ ሞትን መቋቋም እንደማይቻል ሁሉ  ፍቅርንም መቋቋም እንደማይቻል፣ የሞት ግድግዳን ተሻግሮ መሄድ የሚችል ነው ብለዋል። የፍቅር እና የእምነት ተመሳሳይነትን ያስረዱት አቡነ ፊዚኬላ፣ ግባቸውም አንድ ነው ብለዋል።

ለመፈቀር አፈቅራለሁ፣

እግዚአብሔር ሲያፈቅረን እርሱም በእኛ ዘንድ ከመፈቀር ሌላ ምንም ፍላጎት የለውም የሚለውን የቅዱስ ቤርናርዶን ንግግር ያስታወሱት አቡነ ፊዚኬላ፣ አንድ ሰው አፈቅርሃለሁ ወይም አፈቅርሻለሁ በሚልበት ጊዜ “በፍጹም አትሞትም” ከማለት ጋር አንድ ነው ብለው ሁለት ሰዎች በመካከላቸው የሚያስቀምጡት የፍቅር ማሕተም የማይፋቅ፣ ከሞት ባሻገር የሚዘልቅ የእውነተኛ ፍቅር መገለጫ መሆኑን፣ በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚዳንት የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ አስረድተዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
06 August 2019, 16:47