የ2011 ዓ. ም. የፍለስታ ጾም በማስመልከት የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን መልእክት የ2011 ዓ. ም. የፍለስታ ጾም በማስመልከት የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን መልእክት 

የ2011 ዓ. ም. የፍለስታ ጾም በማስመልከት የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን መልእክት

ከሁሉ አስቀድሜ ለመላው ኢትዮጵያውያን ካቶሊካውያን ምእመናንና የፍልሰታ ማርያም ክብረ በዓል ለሚያከብሩ ሁሉ እንኳን ለ2011 ዓ/ም ለፍልሰታ ጾም በሰላም አደረሳችሁ እያልኩ የተቀደሰ የተባረከ የፍልሰታ ጾም እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ። የ2011 ዓ.ም የፍልሰታ ማርያም ጾም በማስመልከት ለመላው ካቶሊክ ምእመናን ምኞቴንና ቡራኬዬን በምሰጥበት ጊዜ ታላቅ ደስታ እየተሰማኝ ነው።

የፍልሰታ ማርያም ክብረ በዓል፤ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋዋና በነፍሷ ወደ ሰማይ የወጣችበት፤ ከእመቤታችን ድንግል ማርያም በዓላት ሁሉ ከፍ ያለ በዓል ነሐሴ 16/ 2011 ዓ.ም በካቶሊካዊያን ምእመናን ዘንድ ይከበራል። ከነሐሴ 1 እስከ ነሐሴ 15 ለእመቤታችን ፍልሰታ ክብረ በዓል ምእመናን ከፍተኛ መንፈሳዊ ዝግጅት በማድረግ በጾምና በጸሎት በመትጋት ያሳልፋሉ። ይህ ጾምና ምህለላ በሙሉ ልብ መሆን እንዳለበትና ንስሐን በመግባት የተቸገሩትን በመርዳትና የተጣሉትን በማስታረቅ እንዲሁም የበደልናቸውም ካሉ ይቅርታን በመጠየቅ ለክብረ በዓሉ መዘጋጀት አስፈላጊ እንደሆነ ለመግለጽ እፈልጋለሁ። በዚህ አጋጣሚ የሰላም ንግስት የሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለአገራችን እውነተኛ የሆነውን የልጇን ሰላም እንድታሰጠን ከልብ እንድንማፀናት አደራ እላለሁ።

የተቸገሩትንና ድሆችን መርዳት አስፈለጊ እንደሆነ አስተምራናለች። በርሷ የፍቅር ሥራና ትሕትና የተሞላበት ሕይወት ልንማረክ ይገባናል። በአሁን ሰዓት በየቤቱ በችግር ላይ ያሉ ወገኖችን ማሰብ አለብን። ሁላችንም ክርስቲያኖች እግዚአብሔር ከሰጠን በረከት ለድሆች በማካፈል ጾማችንን በተግባር መኖር አለብን። ነገር ግን ይህ በጾም ወቅት ብቻ የሚደረግ የአንድ ጊዜ ተግባር ሳይሆን ለዘለቄታ መለማመድ ያለብን ተግባር ነው። በተለይም እያንዳንዱ ማህበራዊ ውሳኔዎቻችን ድሆችን ከግንዛቤ ውስጥ ያስገባ ማድረግ አለብን።

በተለይ በዚህ ጊዜ በአገራችን የተለያዩ ክፍሎች በሚከሰቱ ግጭቶች ምክንያት ከየቀያቸው ተፈናቅለው በችግር ላይ የሚገኙ በርካታ ቤተሰቦች አሉ። ቤተሰብ ሲፈናቀል ደግሞ በቅድሚያ የሚጠቁት ሕጻናትና እናቶች ናቸው፤ በዚህ የጾም ወቅት ለነዚህ ወገኖች ልዩ ጸሎትና ድጋፍ ማድረግ አለብን። ቤተክርስቲያናችን እንደተለመደው ከሕዝብ ጎን በመቆም ተፈናቃዮች ባሉበት ቦታ ተገኝታ ለተጎዱ ወገኖች አስፈላጊውን መንፈሳዊና ቁሳዊ ድጋፍ በማድረግ ላይ ትገኛለች። ምእምናንም ይህንኑ ተግባር በመደገፍ በጸሎትና በተግባር ከቤተክርስቲያን ጋር እንዲተባበሩ እንዲሁም በየአቅራቢያቸው ለሚያጋጥሟቸው ተጎጂዎች የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ አደራ እንላለን።

በመጨረሻም

1. ክርስቲያኖች ከሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር በሰላም፣ በመከባበር እና እርስ በርስ ተዋደው በመኖር የጾምና የጸሎት መንፈስለብሰው እንዲጓዙ አሳስባለሁ። 

2. ሁላችንም የሰላም መሳሪያ በመሆን ለአገራችን ብሎም ለመላው ምስራቅ አፍሪካ ሰላማዊ አንድነት መረጋገጥ እንድንተጋ አደራ እላለው።

3. ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ቀርቶ ሰዎች በአገራቸው ሠርተው እንዲበለጽጉና አገራቸውን እንዲያሳድጉ ለማሳሰብ እፈልጋለሁ። 

4. እግዚአብሔር ክረምቱን ባርኮ ዝናቡን በሚያስፈልግበት ቦታ ሁሉ እንዲሰጠን መጸለይ እንድንቀጥል አደራ እላለው። የጾም ወራትን በጾምና በጸሎት በተጋድሎም በማሳለፍ ለበዓለ ፍልሰታዋ በሰላም ለመድረስ ያብቃን። አምላክ የተቀደስ የተባረከ ጾመ ፍልሰታ ለመላው ካቶሊካዊያን ምእምናን ያድርግልን እያልኩ የአፍሪካ እመቤት፣ የሰላም ንግስት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለኛ ለልጆቿ ትለምንልን። አሜን

ቸሩ አምላካችን በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ኢትዮጵያን ይባርካት።

†ካርዲናል ብርሃነየሱስ 

ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን የካቶሊካውያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
08 August 2019, 10:06