ፍልሰታ ማሪያም ፍልሰታ ማሪያም 

ፍልሰታ ማሪያም

እንደ አገራችን ሥርዓተ አምልኮና መንፈሳዊ ልማድ በእመቤታችን በኩል እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ስለገለጠው ተስፋና በእርስዋም ጸጋ መሞላት ላደረገልን ቸርነት በተለየ ሁኔታ በየዓመቱ ለ16 ቀናት የሚዘለቀወን ጾምና ምህለላ የምናደርግበት የፍልሰታ ዘመን ላይ እንገኛለን። እግዚአብሔር አብ በእርሱ ለኖሩት ሁሉ ሊያደርግላቸው ቃል የገባውን እውነታ እርሱ በፈቀደው መልኩ በእመቤታችን የተገበረበትን ጸጋ እንወድሳለን፤ ለእኛም ይሆንልን ዘንድ “ሰአሊ ለነ ማርያም ኀበ ወልደኪ ኄር መድኃኔ ዓለም” /ማርያም ሆይ! ቸር፣ የሰው ልጆች ሁሉ አዳኝ ወደ ሆነው ልጅሽ ለምኝልን/ በማለት የእናትነት አማላጅነቷን እንማጠናለን። 
በኢትዮጵያ የሚገኙ በተለይ የምሥራቃዊ ሥርዓተ አምልኮ የሚከተሉ አገረ ስብከቶች ማለትም የአዲስ አበባ፣ የዓዲግራትና የእምድብር አገረ ስብከት ምእመናን በነዚህ ቀናት የሚደረገውን ጾምና ልዩ መንፈሳዊነት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ያን ምእመናን ጋር የሚጋሩ ሲሆን ከበስተጀርባ ያለውን የአገራችንን ትውፊት አውቀን ይህን ወቅት የመጠቀሙን አስፈላጊነት ስላመንበት ከ http://www.zeorthodox.org/ ድረ ገጽ ያገኘነውንና ከቃሉ ትርጉም በመነሣት ከትውፊትና ከቅዱስ መጽሐፍት በማጣቀስ የፍልሰታ ለማርያምን ትርጉምና መንፈሳዊነት የሚገልጸውን ጽሑፍ ቃል በቃል ከዚህ በታች አስፍረነዋል። 
• ፍልሰታ ማለት ፈለሰ ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ማዛወር የነበሩበትን ሀገር ለቆ ወደ ሌላ ሀገር መሰደድ መፍለስ ማለት ነው፡፡ ጾመ ፍልሰታ ሲባልም የእመቤታችን ሥጋ ከጌቴሰማኒ ወደ ገነት መፍለስን በኋላም በገነት በእፀ ሕይወት ሥር ከነበረበት መነሣቱን ለማመልከት የሚነገርነው፡፡
• እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም 64 ዓመት በዚህ ዓለም ኖራ በሞት ከተለየች በኋላ እንደ አንድ ልጅዋ ሞታ መነሣቷንና እርገቷን ያዩ ዘንድ ሐዋርያት ከነሐሴ 1 እስከ 16 የጾሙት ጾም ነው፡፡ ጾመ ፍልሰታ ከሰባቱ አበይት አጽዋማት አንዱ ሆኖ በቀኖና እንዲጾም ከተወሰነበት ጊዜ ጀምሮ ምእመናን ይጾሙታል፡፡
• እመቤታችን በ5485 ዓ.ዓ ከአባቷ ከኢያቄም ከእናቷ ከሐና “እም ሊባኖስ ትወጽእ መርዓት፡፡ ከሊባኖስ ሙሽራ ትወጣለች” ተብሎ በተነገረው መሠረት ነሐሴ 7 ቀን ተጸነሰች፡፡ ግንቦት አንድ ቀን ሊባኖስ በምትባል ወረዳ በብጽአት እንደተወለደች የቤተክርስቲያን ታሪክ በሰፊው ያስረዳል፡፡ በጾም በጸሎት በአስተብቁዖት የተገኘችናት፡፡ ንጽሕት በመሆኗም ማኅደረ እግዚአብሔር ሆናለች፡፡

እመቤታችን ከእናትና ከአባቷ ዘንድ ሦስት ዓመት፣ በቤተ መቅደስ 12 ዓመት፣ ከልጅዋ ከወዳጅዋ ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ 33 ዓመት ከሦስት ወር፣ ከዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድ ዘንድ 14 ዓመት ከዘጠኝ ወር ጠቅላላ ድምር 64 ዓመት ሲሆናት ጥር 21 ቀን በ49 ዓመተ ምሕረት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች፡፡

• ወዳጁን ውበቱን ተነሺ ነይ እያለ የተጣራው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ተጠሪዋም እመቤታችን ናት፡፡ እነሆ ክረምት አለፈ ማለት በስደት በአይሁድ የዘወትር ጠላትነት በልጅዋ መከራና ስቅላት ስምዖን በቤተ መቅደስ እንደተናገረ ልቧ በሀዘን ሠይፍ የተከፈለበት በሀዘን ፍላጻ የተወጋበት የመከራ ክረምት /ወቅት/ አልፎ የክርስቶስ ሕማሙ ፣ ሞቱ፣ ቤዛነቱ ተፈጽሟል፡፡ ትንሣኤው በምድር ላይ ተገልጧል፣ ተሰብኳል ማለት ነው፡፡ በምድራችን አበባ ታይቷል ማለት የሐዋርያት ድምፅ በምድር ሁሉ ደርሷል ማለት ነው፡፡
• የእግዚአብሔር መልአክ የእመቤታችን ሥጋ ከሐዋርያው ዮሐንስ ጋር ተድላ ደስታ ወደ አለባት ገነት በመንፈስ ቅዱስ ተነጠቁ፡፡ ጌታም የእመቤታችንን ሥጋ ታወጣ ዘንድ ምድርን እንዲጠሩዋት ሰባቱን የመላእክት አለቆች አዘዛቸው፡፡ እነርሱም ትወጪ ዘንድ እግዚአብሔር አዞሻል አሏት፡፡ ያን ጊዜም ከእፅ ሕይወት በታች ካለ መቃብር የእመቤታችን የማርያም ሥጋዋ ወጣ፡፡ ጌታችንም ዘላለማዊ ወደሆነ መንግሥተ ሰማያት መላእክት እና ሰማእታት እየሰገዱላት አሳረጓት፡፡

• የእመቤታችን ትንሣኤና እርገት መታሰቢያ - በጾመ ፍልሰታ ወቅት ብዙዎች ከቤታቸው ተለይተው በመቃብር ቤት ዘግተው፣ አልጋና ምንጣፍ ትተው፣ በመሬት ላይ ተኝተው ዝግን ጥሬ እፍኝ ውኃ እየቀመሱ በጾምና በጸሎት በመትጋት በታላቅ ተጋድሎ ይሰነብታሉ፡፡ በሰሙነ ፍልሰታ ምእመናን ለእመቤታችን ያላቸውን ጽኑና ጥልቅ ፍቅር የሚያሳዩበት ነው፡፡

• ጌታችን ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሰ መቃብር ቆይቶ ሙስና መቃብር ሳያገኘው፣ መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል በሥልጣኑ እሑድ በመንፈቀ ሌሊት እንደተነሣ ሁሉ እርሷም በተቀበረች በሦስተኛው ቀን ማኅደረ መለኮት ናትና ሰውነቷ ሳይበሰብስ መቃብር ሳያገኛት መግነዝ ፍቱልኝ፣ መቃብር ክፈቱልኝ ሳትል የልጅዋ ሥልጣን ኃይል ሆኗት መነሣቷን ትንሣኤዋ “ከመ ትንሣኤ ወልዳ፤ እንደ ልጅዋ ትንሣኤ” ነው ተብሎ ሲከበርላት ይኖራል፡፡

• በዚሁ በነሐሴ 16 ቀን የሰማእቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ፍልሰቱ ነው፡፡ ሥጋው ከፋርስ ሀገር ወደ ሀገሩ ወደ ልዳ በክብር የፈለሰበት ነው፡፡ ፍልሰቴን ከፍልሰትሽ አድርጊልኝ፣ ብሎ ለምኗት ስለነበር ፍልሰቱ ከእመቤታችን ፍልሰት ጋር እንዳሰበው ሆኖለታል፡፡ ስለዚህም እርሷን መውደዱ የሚያውቁ ሥእሉን ከሥእሏ አጠገብ ይስላሉ፡፡ በስሙ ለሚማጸኑ የድኅነት ወደብ ይሆን ዘንድ፡፡ 

ምንጭ፦ በኢትዮጲያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የሲታዊያን ማኃበር ድህረ ገጺ ከሆነው http://www.ethiocist.org በነሐሴ 6/2009 ዓ.ም. የተወሰደ።

10 August 2019, 09:05