የነሐሴ 26/2011 ዓ.ም ዘክረምት 9ኛ እለተ ሰንበት ቅ.ወንጌል እና የቅ. አስተንትኖ። የነሐሴ 26/2011 ዓ.ም ዘክረምት 9ኛ እለተ ሰንበት ቅ.ወንጌል እና የቅ. አስተንትኖ። 

የነሐሴ 26/2011 ዓ.ም ዘክረምት 9ኛ እለተ ሰንበት ቅ.ወንጌል እና የቅ. አስተንትኖ።

የእለቱ ምንባባት

1.     ዕብ. 3:1-19

2.     ያዕ.5:1-11       

3.     ሐዋ.22:1-21         

4.     ዮሐ.6:41-71

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

አይሁድም፣ “ከሰማይ የወረደ እንጀራ እኔ ነኝ” በማለቱ ያጒረመርሙበት ጀመር። ደግሞም፣ “ይህ አባቱንና እናቱን የምናውቃቸው፣ የዮሴፍ ልጅ ኢየሱስ አይደለምን? ታዲያ አሁን እንዴት፣ ‘ከሰማይ ወረድሁ ይላል’” አሉ። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “እርስ በርሳችሁ አታጒረምርሙ፤ የላከኝ አብ ካልሳበው በቀር ማንም ወደ እኔ መምጣት አይችልም፤ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ። በነቢያትም፣ ‘ሁሉም ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ’ ተብሎ ተጽፎአል፤ አብን የሚሰማና ከእርሱም የሚማር ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል። ከእግዚአብሔር ዘንድ ከሆነው በቀር አብን ያየ ማንም የለም፤ አብን ያየው እርሱ ብቻ ነው። እውነት እላችኋለሁ፤ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት አለው። የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ።  አባቶቻችሁ በምድረ በዳ መና በሉ፤ ይሁን እንጂ ሞቱ። 50ነገር ግን ሰው እንዳይሞት ይበላው ዘንድ ከሰማይ የሚወርድ እንጀራ ይህ ነው። ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ፤ ማንም ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል፤ ይህም እንጀራ፣ ለዓለም ሕይወት እንዲሆን የምሰጠው ሥጋዬ ነው።”

አይሁድም፣ “እንበላ ዘንድ ይህ ሰው ሥጋውን እንዴት ሊሰጠን ይችላል?” እያሉ እርስ በርሳቸው አጥብቀው ይከራከሩ ጀመር። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ የሰውን ልጅ ሥጋውን ካልበላችሁና ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም። ሥጋዬን የሚበላ፣ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፤ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ፤ ሥጋዬ እውነተኛ ምግብ፣ ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና፤ ሥጋዬን የሚበላ፣ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል፤ እኔም በእርሱ እኖራለሁ። ሕያው አብ እንደ ላከኝ፣ እኔም ከእርሱ የተነሣ በሕይወት እንደምኖር፣ የሚበላኝም እንዲሁ ከእኔ የተነሣ በሕይወት ይኖራል። ከሰማይ የወረደ እንጀራ ይህ ነው፤ አባቶቻችሁ መና በሉ፤ ሞቱም፤ ይህን እንጀራ የሚበላ ግን ለዘላለም ይኖራል።” ይህን የተናገረው በቅፍርናሆም፣ በምኲራብ እያስተማረ ሳለ ነበር።

ብዙ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስን መከተል ተዉ

ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎች ይህን ሲሰሙ፣ “ይህ የሚያስጨንቅ ቃል ነው፤ ማንስ ሊቀበለው ይችላል?” አሉ።

ደቀ መዛሙርቱም በዚህ ነገር ማጒረም ረማቸውን ኢየሱስ በገዛ ራሱ ተረድቶ፣ እንዲህ አላቸው፤ “ይህ ዕንቅፋት ይሆንባችኋልን? ታዲያ፣ የሰው ልጅ ቀድሞ ወደነበረበት ሲወጣ ብታዩ ምን ልትሉ ነው? መንፈስ ሕይወትን ይሰጣል፤ ሥጋ ግን ምንም አይጠቅምም። እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስም ሕይወትም ነው፤ ይሁን እንጂ ከእናንተ የማያምኑ አንዳንዶች አሉ።” ይህም፣ ኢየሱስ እነማን እንዳላመኑና ማን አሳልፎ እንደሚሰጠው ቀድሞውኑ ያውቅ ስለ ነበር ነው። ቀጥሎም፣ “ ‘ከአብ ካልተሰጠው በቀር፣ ማንም ወደ እኔ ሊመጣ አይችልም’ ያልኋችሁ ለዚህ ነው” አለ።

ከዚህም በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎች ወደ ኋላ ተመለሱ፤ ከዚያም ወዲያ አልተከተሉትም። ኢየሱስም ዐሥራ ሁለቱን፣ “እናንተም ደግሞ መሄድ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። ስምዖን ጴጥሮስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ጌታ ሆይ፤ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ፤ አንተ አንድያ የእግዚአብሔር ቅዱስ እንደሆንህ አምነናል፤ ዐውቀናልም።” ኢየሱስም መልሶ፣ “ዐሥራ ሁለታችሁንም የመረጥኋችሁ እኔ አይደለሁምን? ነገር ግን ከእናንተ አንዱ ዲያብሎስ ነው” አላቸው። የአስቆሮቱ የስምዖን ልጅ ይሁዳ፣ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ቢሆንም፣ ኋላ አሳልፎ ስለሚሰጠው ስለ እርሱ መናገሩ ነበር።

የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

ለዚህ ሰንበት አስተንትኖ ያግዘን ዘንድ በወንጌል ያሉትን አንዳንድ ነጥቦች እንውሰድ። የዛሬው ወንጌል ንባብ የዘወትር የክርስቶስ ትምህርት ባህርይንና የሰው ልጅም ለርሱ ትምህርት የሚሰጠውን ግብረ ምላሽ ያንጸባርቃል። መቼም ቢሆን የክርስቶስ ትምህርት ወይም መልእክት ቀላል ሆኖ አያውቅም፤ ከዚህም የተነሣ ዘወትር ብዙዎች ይከራከሩበታል ፦ “ይህ ሰው ሥጋውን እንበላ ዘንድ እንዴት ሊሰጠን ይችላል? በማለት አይሁዳውያን ተከራከሩ”(ዮሐ.6:52)፣ ሌሎች ብዙዎችም እሱን መከተል ጀምረው ወደ ኋላ ያፈገፍጉበታል ወይም ይደናቀፉበታል ፦ “…ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎቹ ወደ ኋላ ተመለሱ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ኢየሱስን መከተል ተዉ”(6:66)፣ የተወሰኑ ወይም ጥቂቶች ደግሞ ንግግሩ ከባድና እንዴት ይሆናል የሚያስብል ቢሆንም ተናጋሪው እሱ ራሱ ክርስቶስ ነውና ከርሱ ጋር አብረው መሆንን ይመርጣሉ ፦ “ጌታ ሆይ! ወደ ማን እንሄዳለን፤ አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ። እኛስ አምነናል፤ ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ አንተ እንደሆንህም ዐውቀናል።”(6:68)።  ምናልባት እኛ ራሳችንን በቀጥታ ከነዚህ ጋር ማመሳሰሉ ሊከብድ ይችላል። ነገር ግን በተግባራዊ መልኩ ይህን ሀሳብ ስናየው ልናያይዘው የምንችለው በቀጥታ ለቅዱስ ቁርባን ወይም ለቅዳሴ ካለን ግንዛቤ፣ እምነትና ልምምዳችን አንጻር ነው።

በዚህ ሃሳብ ዙሪያ ማለትም ቅዱስ ቁርባንን በሚመለከት የሆነ ነጥብ ሲነሣ ባብዛኛው የተለመዱ አባባሎች አሉ ፦ "የተወሰነ ጊዜ አዘወትር ነበር፣ ማመንማ አምነዋለሁ ግን፤ እስቲ ወደፊት…ወዘተ" እና መሳይ አቋሞች ናቸው። ቅዱስ ቁርባን በምግብ መልክ ለዘላለማዊነት የተሰጠን ቅዱስ ማዕድ ስለሆነ እንደማንኛውም ምግብ ሁሉ የአሁን ጉዳይ ነው። አንድ ሰው ከምግብ አሁን ርቄያለሁ፣ ትቻለሁ፣ ድሮ እበላ ነበር...ቢለን ቆም ብለን ይህ ሰው ጤነኛ ነው እንደዚህ እንዴት ሊኖር ይችላል ብለን ሃሳቡን መቀበሉ ይከብደናል። ስለ ቅዱስ ቁርባንም በክርስቶስ ፊት እንደዚያ ስንል እሱ ነፍሳችን ያለርሱ ምንም መሆኗን ይውቃልና “ሥጋዬን የሚበላና ደሜን የሚጠጣ ሁሉ በእኔ ይኖራል፤ እኔም በእርሱ እኖራለሁ” ይለናል።

እዚህ ላይ ለቅዳሴ ያለንን ግንዛቤና አቋም እናስተውል። ምን ያህልስ የሕይወታችን ተቀዳሚ ነገር አድርገን እናስበዋለን? ትርፍ ጊዜ ሲኖረን፣ የቤተ ክርስቲያን ትእዛዝ ጉዳይ ብቻ ሆኖብን ሌላ ሌላ ሳይሆን ክርስቶስ “እውነት እውነት እላችኋለሁ የሰው ልጅ የሆነውን የክርስቶስን ሥጋ ካልበላችሁ፤ ደሙንም ካልጠጣችሁ ሕይወት የላችሁም”  በማለት በፍቅር የመከረንን ግብዣ ለመሳተፍ መሆን አለበት።

ወንጌል ውስጥ ክርስቶስ መሠረታዊ የሆነ አዲስ ትምህርት ሲያስተላልፍ “እውነት እውነት እላቸኋለሁ” ብሎ ይጀምራል፤ ስለ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙም ይህንኑ ነው ያለው። ብዙ ክርስቲያኖች ይህን ግብዣ እውን ለማድረግ ብዙም አንጥርም፤ በጊዜ ሰሌዳችን ወይም በቀናት ፕሮግራማችን ውስጥም ቦታ አንይዝለትም። እስቲ ቦታ ከሌለው ሌላ መሰረዝ የምንችለውን ነገር ሰርዘን ክርስቶስ “እውነት እውነት እላቸኋለሁ” ብሎ የመከረንን ነገር ለመተግበር እንወስን።

ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊው በራሱ የአነጋገር ዘይቤ በወንጌሉ መጀመሪያ ምዕራፍ ውስጥ ሲነግረን:- “ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፤ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነውን ክብሩን አየን” ይለናል። ይህ ንግግር በቀጥታ ከቅዱስ ቁርባን እውነታ ጋር ይያያዛል። ቤተ ክርስቲያን ዛሬ በቅዳሴ የምትደግመው የእግዚአብሔር ቃል በመካከላችን በጸጋውና በክብሩ በመካከላችን ክርስቶስ ያድራል። በሌላ አባባል የክርስቶስ መወለድና ሰው መሆንን ማመን በቅዱስ ቁርባን የእሱ መገኘትን ከማመን ጋር ይተሳሰራል ማለት ነው። እንደኛ ሥጋን የለበሰውና ሰው ሆኖ የተገለጠው ክርስቶስ እኛን መሰል ከሆነው ይታይና ይጨበጥ በነበረው ሰዋዊ አካሉ የእግዚአብሔር ልጅ ነው፤ እንዲሁም ዛሬ በኅብስትና ወይን መልክ የክርስቶስ ሥጋና ደም አለ። ይህ የቅመማ ውጤት የሳይንስ ክፍል ወይም ሌላ እውቀት ሳይሆን የእምነት ጉዳይ ነው። ያመኑ ተከተሉት፣ ጊዜም ሰጡት ያላመኑት ግን ተዉት ጊዜም  ነሡት።

ለቅዱስ ቁርባን መታደማችን ታዛቢ የክብር እንግዶች እንድንሆን ሳይሆን የፍቅር ተሳታፊዎች እንድንሆን ነው። ፍቅር የልብ ጉዳይ ነውና ልባችንን ለርሱ እናነሣሳ። ከልባችን ውስጥ ክርስቶስን ለማራቅ ከምንጥር ይልቅ እሱ እንዳይገባ የሚያደርጉ ነገሮችን እናርቅ። በዚህ ሃሳብ በጸሎት ደካማነታችንን ታምነን በቀረብነው መጠን ሊያበረታንና ሊያቆመን ዝግጁ ነው። ያለርሱ በድካም ላይ ድካምን እናበዛለን፤ ከርሱ ጋርም በድካም ላይ ኃይልን እንጨምራለን ።

28 August 2019, 12:59