የሰሜን አሜርካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ብጹዕ ካርዲናል ዳንኤል ዲናርዶ፤ የሰሜን አሜርካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ብጹዕ ካርዲናል ዳንኤል ዲናርዶ፤ 

ብጹዕ ካርዲናል ዳንኤል አዲሱን የስደተኞች መመሪያ ድንብ መቃወማቸው ተገለጸ።

የሰሜን አሜርካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ብጹዕ ካርዲናል ዳንኤል ዲናርዶ ለአሜርካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በላኩት መልዕክት መንግሥታቸው የስደተኞችን ጉዳይ አስመልክቶ ያወጣውን አዲሱን ደንብ ተመልሰው እንዲያጤኑት አሳስበዋል። የአሜርካ መንግሥት የደህንነት ቢሮ ባለፈው ሳምንት ይፋ ያደረገው አዲሱ ደንብ በአሜርካ የሚኖሩትን ስደተኞች ማስደንገጡ ታውቋል። ብጹዕ ካርዲናል ዳንኤል ዲናርዶ አዲስ በወጣው ደንብ ያላቸውን ተቃውሞ በመግለጽ እንደተናገሩት ደንቡ ቤተሰብን ከቤተሰብ የሚነጥል፣ ሕጻናትን ከወላጆቻቸው የሚነጥል መሆኑን ገልጸው ባሁኑ ወቅት ከቤተሰቦቻቸው ጋር፣ ከወላጆቻቸው ጋር ለመገናኘት ፈልገው ድንበር ለመሻገር የአሜርካን መንግሥት ፈቃድ በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ በርካታ የደቡብ አሜርካ እና የሌሎች አገሮች ዜጎች መኖራቸውን አስታውሰዋል። ብጹዕ ካርዲናል ዳንኤል በማከልም የሰሜን አሜርካ መንግሥት ኢሚግሬሽን ቢሮ አዲስ ባወጣው ደንብ በኩል የመካከለኛው አሜሪካ ነዋሪዎች ከአገራቸው እንዳይወጡ ለማድረግ የታሰበ እቅድ ነው ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

አዲሱ የስደተኞች መመሪያ ደንብ ሕጋዊነት ያጠራጥራል፣

ብጹዕ ካርዲናል ዳንኤል ለሰሜን አሜርካው ፕሬዚደንት በላኩት መልዕክታቸው፣ ሕይወታቸውን ከአደጋ ለማትረፍ፣ ለቤተ ሰባቸው የሕይወት ዋስትናን ለማግኘት ብለው ወደ ሰሜን አሜርካ ለሚመጡትን ስደተኞች በር መዝጋት የሰሜን አሜርካን ክርስቲያናዊ እሴቶችን ይቃረናል ብለዋል። ብጹዕ ካርዲናል ዳንኤል በመልዕክታቸው ይህን ካሳሰቡ በኋላ ከዚህ በፊት ይቀርብ የነበረው የጥገኝነት ማመልከቻ ጥያቄን የአሜርካ መንግሥት ተሻሽሎ እንዲቀርብ ማድረጉ ተጨማሪ እንቅፋቶችን ማስከተሉን እና የውሳኔውን ሕጋዊነት እና ተግባራዊነት ጥርጣሬ ውስጥ እንዲገባ ማድረጉን አስረድተዋል።

ደንቡ የጥገኝነት ጥያቄ መብትን ይጥሳል፣

እንደ አዲሱ ሕግ መሠረት ወደ ደቡብ ምዕራብ የሰሜን አሜርካ ድንበር የሚደርሱ ስደተኞች በጥገኝነት ጥያቄ ማመልከታቸው ውስጥ ሌላ ሦስተኛ አገር ካልጠቀሱ በስተቀር ማመልከታቸው ተቀባይነትን እንደማያገኝ ያሳስባል ተብሏል። ሦስተኛ አገር መጠቀሱ ሰሜን አሜርካን ለመሸጋገሪያ እንጂ እንደ ቋሚ መኖሪያ አገር እንዳይወስዱት ያደርጋል ተብሏል። ካርዲናል ዳንኤል በማከልም ይህ የኢሚግሬሽን ጉዳይ አዲሱ ሕግ የስደተኞችን የጥገኝነት ጥያቄ መብት የሚቃረን በመሆኑ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብም ቢሆን የጉዳዩን አስከፊነት በመገንዘብ ለሰሜን አሜርካ መንግሥት ተቃውሞን እንዲያቀርብ አሳስበዋል። ካርዲናል ዳንኤል በማከልም ለችግሩ ሕጋዊ እና ትክክለኛ መንገድን የተከተለ መፍትሄን ማፈላለግ እንደሚያስፈልግ ገልጸው የሚደርስባቸውን ችግር እና መከራን ሸሽተው ካገራቸው ወጥተው በስደት ላይ የሚገኙት ቤተሰቦች ሰብዓዊ ክብር እና መብት ማክበር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
18 July 2019, 16:06