በሶርያ የደማስቆ ሕጻናት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ፣ በሶርያ የደማስቆ ሕጻናት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ፣  

በሶርያ ውስጥ የፍራንችስካዊያን ወንድሞች መኖር ተስፋን የሚሰጥ መሆኑ ተገለጸ።

ላለፉት ስምንት ዓመታት ጦርነት እና አመጽ ባልተለያት ሶርያ ውስጥ ከኢየሩሳሌም የተላኩት ፍራንችስካዊያን ወንድሞች በሕዝቡ መካከል ተገኝተው የሚያበረክቱት የጸሎት ድጋፍ እና ሌሎች ሐዋርያዊ አገልግሎቶች ተስፋን የሚሰጥ መሆኑ ተገለጸ።  

“ሕዝቡ አስቸጋሪ ጊዜን በትዕግስት አሳልፈው ለምስክርነት እንዲበቁ በማበረታታት ላይ እንገኛለን” ያሉት የፍራንችስካዊያን ማሕበር አባል አባ ባያት ኤሊያስ ካራካሽ፣ የማሕበራቸው አባላት በሶርያ ሕዝብ መካከል መገኘት የተስፋ ምልክት መሆኑን ለቫቲካን የዜና አገልግሎት ገልጸዋል። የማሕበራቸው መቀመጫቸው በኢየሩሳሌም ቅድስት አገር እንደሆነ የተናገሩት አባ ኤሊያስ በደማስቆ ለሚገኝ የማሕበራቸው መኖሪያ ቤት አለቃ እና የላቲን ስርዓተ አምልኮን ለምትከተል ለደማስቆ ከተማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን መሪ ቆሞስ መሆናቸው የቫቲካን የዜና አገልግሎት ባልደረባ ኤውጄኒዮ ሰራ የላከልን ዜና አመልክቷል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ደማስቆ ያለችበት ሁኔታ፣

የደማስቆ ከተማ በተረጋጋ ሁኔታ እንደምትገኝ የገለጹት አባ ኤሊያስ፣ ከአካባቢው ሕዝብ አእምሮ ውስጥ የጦርነት እና የሽብር ጥቃት አደጋ ፍርሃት መወገዱን አስታውቀው ነገር ግን የኤኮኖሚ ቀውስ ባለመወገዱ ምክንያት ሕዝቡ ተስፋን በማጣት የተሻለ ኑሮ ፍለጋ በማለት፣ የሚኖርበትን አካባቢ ለቆ በመሰደድ ላይ ይገኛል ብለዋል።

በማሕበረሰቡ መካከል የክርስቲያኖች ጥንካሬ፣

በደማስቆ ከተማ ውስጥ ለሚገኝ ካቶሊካዊ ቁምስና መሪ ካህን የሆኑት አባ ኤሊያስ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንደገለጹት በደማስቆ ከተማይቱ ውስጥ የሚገኙትን ክርስቲያኖች የእምነት ጽናት እና በማሕበራዊ ኑሮአቸውም፣ በመካከላቸው በሚያደርጉት መተጋገዝ እና የጋራ ውይይት መልካም ተሳትፎን እያሳዩ መሆናቸውን አስታውቀው ምንም እንኳን በደማስቆ ከተማ የሚገኝ የክርስቲያን ማሕበረሰብ በቁጥር ዝቅተኛ ቢሆንም ማሕበራዊ ተሳትፎአቸው የሚያስመሰግን ነው ብለዋል።

እምነት ካለ የስቃይ ኑሮም የክርስትና ምስክርነት ይሆናል፣

እምነት ካለ ነገሮች በሙሉ ሌላ መልክ ይኖራቸዋል ያሉት አባ ኤሊያስ ክርስቲያኖች የሚያሳልፉት የመከራ እና የስቃይ ሕይወት ተመልሶ ክርስቲያናዊ ተልዕኮ እና ምስክርነት ይሆናል ብለዋል። በሶርያ ወስጥ የሚገኙት ክርቲያኖች የሕይወት ትርጉም ይህ መሆኑን ያስረዱት አባ ኤሊያስ ለሶርያ ሕዝብም ማስገንዘብ የምንፈልገው መልዕክት ይህ ነው ብለዋል። በስዎች ላይ የሚደርሰውን ስቃይን በምድራዊ ዓይን ብቻ መመልከት ተገቢ እንዳልሆነ ያስረዱት አባ ኤሊያስ ዓለምን ለማዳን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተቀበለው ስቃይ እና መከራ ጋር ማዛመድ ያስፈልጋል ብለዋል።

ከተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት ጋር ውይይት እንዲኖር ያስፈልጋል፣

አባ ኤሊያስ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት ከእስልምና እምነት ወንድሞች እና እህቶች ጋር የጋራ ውይይት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው በአካባቢያቸው ይፋ የሆነ የጋራ ውይይት እየተካሄደ አይደለም ብለው ቢሆንም ማሕበራዊ ሕይወትን በጋራ እየኖሩ መሆናቸውን አስረድተዋል። በምዕራቡ ዓለም የበለጠ ውይይት ይደረግ ይሆናል ያሉት አባ ኤሊያስ በሶርያ ውስጥ አንዱ ወገን ከሌላው ሳይለይ ሁሉም ተመሳሳይ ሕይወት እየኖረ መሆኑን አስረድተው ይህን የመሰለ ማሕበራዊ ሕይወት ለመኖር የጋራ ውይይት እጅግ አስፈላጊ ነው ብለዋል። በሶርያ ውስጥ የሚገኙት ክርስቲያኖች ዋና መለያቸው ለጋራ ውይይት ዝግጁ በመሆን ለኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ሲሉ ምስክርነትን መስጠታቸው ነው ብለዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
16 July 2019, 17:12