አረንጓዴ ምድራችን፣ አረንጓዴ ምድራችን፣ 

የፊሊፒን ብጹዓን ጳጳሳት የአየር ንብረት ለውጥ አደጋን የተመለከተ ሐዋርያዊ መልዕክት አስተላለፉ።

የፊሊፒን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በሰላሳ ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለስምንተኛ ጊዜ ይፋ ባደረገው ሐዋርያዊ መልዕክት በአካባቢያቸው የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ላለው አደጋ ፈጣን ምላሽ መስጠት እንደሚያስፈልግ አሳስቧል። የብጹዓን ጳጳሳቱ ጉባኤ መልዕክትም የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሚለውን ሐዋርያዊ መልዕክት መሠረት ያደረገ እና የአየር ለውጡበፍጥረታት ላይ እያሳከተለ ላለው አደጋ ምላሽ ለመስጠት ያለመ መሆኑ ታውቋል። የፊሊፒን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በ1980 ዓ. ም. ያወጣው የመጀመሪያው  ሐዋርያዊ መልዕክትም “በውብ ምድራችን ምን እየተከሰተ ይገኛል?” የሚል መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የፊሊፒን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በጋራ ሆነው ይፋ ያደረጉት ጠንካራ ሐዋርያዊ መልዕክት ዓላማ የአየር ንብረት ለውጥ በፍጥረታት ላይ እያስከተለ የሚገኘውን አደጋ ማሕበረሰቡ ተገንዝቦ፣ ለሚኖርባት ምድር የሚገባውን እንክብካቤ እንዲያደርግ ለማሳሰብ መሆኑ ታውቋል።   

የፊሊፒን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ አቡነ ሮሙሎ ቫሌስ የፈረሙበት የጉባኤው ሐዋርያዊ መልዕክት ይፋ የወጣው ማክሰኞ ሐምሌ 9/2011 ዓ. ም. መሆኑ ታውቋል። በዘጠኝ ገጾች የተቀመጠው የፊሊፒን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ሐዋርያዊ መልዕክት በስምንት ምዕራፎች የተከፈለ ሲሆን የመጀመሪያዎቹ ግማሽ ምዕራፎች ምድራችን አሁን የምትገኝበትን ሁኔታ የሚዘረዝር ሲሆን በሁለተኛው አጋማሽ ምዕራፎች ደግሞ የአየር ንብረት ለውጥ በምድራችን እያስከተለ ላለው አደጋ ፈጣን ምላሽ መስጠት እንደሚያስፈልግ የሚያሳስብ መሆኑ ታውቋል።

ማሕበራዊ ፍትህን በተመለከተ፣

የፊሊፒን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ድህነት እና የአካባቢ መመናመን የጋራ መኖሪያ የሆነች ምድራችንን ክፉኛ እየጎዳት ይገኛል ብለው፣ የምድራችን እና የድሆችን ጩሄት አድምጦ ማሕበራዊ ፍትህን ማምጣት ያስፈልጋል ብለዋል። የብጹዓን ጳጳሳቱ ቀዳሚ ምርጫቸው የአየር ንብረት ለውጥ ባስከተለው አደጋ ምክንያት ጉዳት የደረሰበት ደሃ ማሕበረሰብ ወደ እግዚአብሔር ለሚያሰማው ድምጽ ፈጣን ምላሽ መስጠት መሆኑን አስታውቀው ሞራላዊ ግዴታም ይህን እንድናደርግ ያስገድደናል ብለዋል። በፊሊፒን በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የመጣውን የድህነት ኑሮ መቀነስ እንዲቻል አካባቢያዊ ሁኔታን መቆጣጠር እና በአግባቡ ማስተዳደር ወሳኝ መሆኑን የፊሊፒን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ገልጸዋል። ብጹዓን ጳጳሳቱ በሐዋርያዊ መልዕክታቸው የአካባቢ መመናመን እና ድህነት እርስ በእርስ የሚገናኙ ናቸው ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በግንቦት ወር 2007 ም ዓ. ም. “ውዳሴ ላንተ ይሁን” በተባለው ሐዋርያዊ መልዕክት የአየር ንብረት ለውጥ ለዓለም ለድሆች ከፍተኛ ስጋት መሆኑን በጥብቅ መናገራቸው ይታወቃል።

የድርጊት መርሀ - ግብር፣

ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤያቸውን በፊሊፒን መዲና ማኒላ ከሰኔ 29 እስከ ሐምሌ 1/2011 ዓ. ም. ያካሄዱት የፊሊፒን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት፣ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሚለውን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ መልዕክት ተግባራዊ ለማድረግ የሕዝባቸውን እምነትና ባሕል ያገናዘበ እና በተግባር ላይ ሊውሉ የሚችሉ የድርጊት መርሃ ግብርን በሐዋርያዊ መልዕክታቸው ይፋ አድርገዋል። ቫቲካን ከዚህ በፊት የፊሊፒን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሚለውን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ መልዕክት ተግባራዊ ለማድረግ ያደረገው እንቅስቃሴ ወይም ጥረት ካለ መጠየቁ ታውቋል። የፊሊፒን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት መልዕክት፣ በሀገሪቱ ላይ የተደቀኑትን ችግሮች ጠቅሶ ከእነዚህም መካከል ሃላፊነት የጎደለው የማዕድናት ቁፋሮ፣ የግድብ ሥራ፣ የድንጋይ ከሰልን እንደ ነዳጅ ኃይል መጠቀሙ እየጨመረ መምጣቱን አስታውቀዋል። በፊሊፒን የተካሄዱት በርካታ ጥናቶች፣ አገሪቱ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ለአደጋ መጋለጧን በመገንዘብ በአደጋ ምክንያት ጉዳት የደረሰበት ደሃ ማሕበረሰብ ወደ እግዚአብሔር ለሚያሰማው ድምጽ ፈጣን ምላሽ የመስጠት ግዴታ እንዳለባቸው ብጹዓን ጳጳሳቱ በመልዕክታቸው ገልጸዋል።  

ሕገ ወጥ የነዳጅ ኃይል ምርት እና ፍጆታን በተመለከተ፣

የፊሊፒን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ካቶሊካዊ የገንዘብ ተቋማት ሃላፊነት ከጎደላቸው ማዕድን ቆፋሪ ድርጅቶች፣ የድንጋይ ከሰል አምራች ኩባንያዎች ጋር ግንኙነት ሊኖር እንደማይገባ አሳስበዋል። እንደዚህ ካለው የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ጋር መተባባር አያስፈልግም ብለው ዜጎቻቸው ያልተጋነነ ሕይወት እንዲኖሩ፣ ፍጆታን በመጠኑ በማድረግ ለአካባቢያቸው ጥበቃን እና እንክብካቤ በማድረግ ተግባር ላይ እንዲሰማሩ፣ የወረቀት እና የፕላስቲክ ምርቶች አጠቃቀምን መቀነስ እንዳለባቸው አሳስበዋል። ብጹዓን ጳጳሳቱ በማከልም አስተማማኝ፣ ንጹህ እና ተለዋዋጭ የኃይል ምንጭ የሆነውን የፀሐይ ኃይልን መጠቀም እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ግንዛቤን ማስጨበጥ ያስፈልጋል፣

የፊሊፒን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በየሀገረ ስብከቶቻቸው የአካባቢ ጥበቃን የሚከታተሉ ማእከላትን እንደሚያቋቋሙ አስታውቀው “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሚለው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክት በአገራቸው ውስጥ በሚገኙ ካቶሊካዊ ትምህርት ቤቶች፣ በዘርዓ ክህነት ትምሕርት ቤቶች እና በመንፈሳዊ ትምህርት መስጫ ተቋማት ውስጥ በስርዓተ ትምህርት እቅድ ውስጥ የሚጠቃለል መሆኑን አስታውቀዋል።

የፊሊፒን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት፣ የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ያለውን አደጋ ለመከላከል ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ፍራንችስኮስ ጋር በጋራ የሚሰሩ መሆናቸውን ገልጸው በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ጉዳት የደረሰባትን የጋራ መኖሪያ ምድራችንን ከአደጋ ማትረፍ ክርስቲያናዊ ሕላፊነት እና ሞራላዊ ግዴታ መሆኑን በሐዋርያዊ መልዕክታቸው አስገንዝበዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
18 July 2019, 16:13