የሐምሌ 07/2011 ዓ.ም ዘክረምት ሁለተኛ ሰንበት አስተንትኖ የሐምሌ 07/2011 ዓ.ም ዘክረምት ሁለተኛ ሰንበት አስተንትኖ 

የሐምሌ 07/2011 ዓ.ም ዘክረምት ሁለተኛ ሰንበት አስተንትኖ

“እንግዲህ የዘሪውን ምሳሌ ስሙ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት ቃል ሰምቶ ከማያስተውል ከማንኛውም ሰው ልብ ውስጥ ክፉው መጥቶ የተዘራውን ዘር ይነጥቃል።

የእለቱ ምንባባት

1.    ዕብ 6:7-20

2.   1ጴጥ 3:8-14

3.   ሐዋ 14:8-18

4.    ማቴ 13:1-30

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

የዘሪው ምሳሌ

በዚያኑ ቀን ኢየሱስ ከቤት ወጥቶ በባሕሩ ዳር አጠገብ ተቀመጠ። ብዙ ሕዝብም ስለ ከበበው በባሕሩ ዳር ትቶአቸው ጀልባ ላይ ወጥቶ ተቀመጠ። ብዙ ነገሮችን በምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “አንድ ገበሬ ዘር ሊዘራ ወጣ። ሲዘራም ሳለ፣ አንዳንዱ ዘር መንገድ ዳር ወደቀ፤ ወፎችም መጥተው ለቅመው በሉት። አንዳንዱ ዘር ዐፈሩ ስስ በሆነ፣ ድንጋያማ መሬት ላይ ወደቀ፤ ዐፈሩ ስስ ስለ ሆነም ፈጥኖ በቀለ። ነገር ግን ፀሓይ ሲመታው ጠወለገ፤ ሥር ባለ መስደዱም ደረቀ። አንዳንዱም ዘር በእሾኽ መካከል ወደቀ፤ እሾኹም አደገና ቡቃያውን አንቆ አስቀረው፤ ሌላው ዘር ደግሞ በጥሩ መሬት ላይ ወደቀ፤ ፍሬም አፈራ፤ አንዱ መቶ፣ አንዱ ሥልሳ፣ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ። ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ!”።

ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው፣ “ለምን ለሕዝቡ በምሳሌ ትናገራለህ?” አሉት። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማይን ምስጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም። ላለው ይጨመርለታል፤ ይበዛለትማል፤ ከሌለው ግን ያ ያለው እንኳ ይወሰድበታል። ስለዚህ እንዲህ በማለት በምሳሌ የምነግራቸው ለዚህ ነው፤

“እያዩ ስለማያዩ፣

እየሰሙ ስለማይሰሙ ወይም ስለማያስተውሉ ነው።

እንዲህ ተብሎ የተነገረው የኢሳይያስ ትንቢት በእነርሱ ይፈጸማል፤

“ ‘መስማትንስ ትሰማላችሁ፤ ነገር ግን አታስተውሉም፤

ማየትንም ታያላችሁ፤ ነገር ግን ልብ አትሉም።

የሕዝቡ ልብ ደንድኖአልና፤

ጆሮአቸውም አይሰማም፤

እንዳያዩም ዐይናቸውን ጨፍነዋል፤

ይህ ባይሆን ኖሮ፣ በዐይናቸው አይተው፣

በጆሮአችው ሰምተው፣

በልባቸውም አስተውለው፣

ወደ እኔ በተመለሱና በፈወስኋቸው ነበር።’

 የእናንተ ዐይኖች ስለሚያዩ፣ ጆሮዎቻችሁም ስለሚሰሙ ግን የተባረኩ ናቸው። እውነት እላችኋለሁ፤ ብዙ ነቢያትና ብዙ ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ለማየትና የምትሰሙትንም ለመስማት ተመኝተው ነበር፤ ግን አልሆነላቸውም።

 “እንግዲህ የዘሪውን ምሳሌ ስሙ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት ቃል ሰምቶ ከማያስተውል ከማንኛውም ሰው ልብ ውስጥ ክፉው መጥቶ የተዘራውን ዘር ይነጥቃል። ይህ እንግዲህ በመንገድ ዳር የተዘራው ዘር ነው። በድንጋያማ መሬት ላይ የተዘራው፣ ቃሉን ሰምቶ ወዲያውኑ በደስታ የሚቀበለውን ሰው ይመስላል። ነገር ግን ሥር መስደድ ባለመቻሉ ብዙ አይቈይም፤ በቃሉ ምክንያት መከራ ወይም ስደት ሲመጣ ወዲያውኑ ይሰናከላል። በእሾኽ መካከል የተዘራው ዘር ቃሉን ሰምቶ ለዚህ ዓለም በመጨነቅና በብልጽግና ሐሳብ በመታለል ታንቆ ያላፈራውን ሰው ይመስላል። በጥሩ መሬት ላይ የተዘራው ዘር ግን ቃሉን ሰምቶ የሚያስተውለውን ሰው ይመስላል፤ በርግጥም ፍሬ ያፈራል፤ አንዱ መቶ፣ አንዱ ሥልሳ፣ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ።”

የእንክርዳዱ ምሳሌ

ኢየሱስም ሌላ ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “መንግሥተ ሰማይ በዕርሻው ቦታ ጥሩ ዘር የዘራን ሰው ትመስላለች። ነገር ግን ሰው ሁሉ ተኝቶ ሳለ፣ ጠላቱ መጥቶ በስንዴው መካከል እንክርዳድ ዘርቶ ሄደ። 26ስንዴው በቅሎ ማፍራት ሲጀምር እንክርዳዱም አብሮ ብቅ አለ።

 “የዕርሻው ባለቤት አገልጋዮችም ወደ እርሱ ቀርበው፣ ‘ጌታ ሆይ፤ በዕርሻህ ቦታ ጥሩ ዘር ዘርተህ አልነበረምን? እንክርዳዱ ከየት መጣ?’ አሉት።

“እርሱም፣ ‘የጠላት ሥራ ነው’ አላቸው።

“አገልጋዮቹም፣ ‘እንክርዳዱን ሄደን እንድንነቅለው ትፈልጋለህ?’ ብለው ጠየቁት።

 “እርሱ ግን፣ ‘አይሆንም፤ ምክንያቱም እንክርዳዱን እንነቅላለን ስትሉ ስንዴውንም አብራችሁ ልትነቅሉ ትችላላችሁ፤ ተዉአቸው፤ እስከ መከር ጊዜ አብረው ይደጉ። በዚያን ጊዜ አጫጆቹን እንክርዳዱን አስቀድማችሁ ንቀሉ፤ በእሳትም እንዲቃጠል በየነዶው እሰሩት፤ ስንዴውን ግን ሰብስባችሁ በጐተራዬ ክተቱ እላቸዋለሁ’ አላቸው።”

የእልቱ የእግዚኣብሔር ቃል አስተንትኖ

የተከበራችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እና በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ! እነሆ ዘመነ ክረምትን ክጀመርን ሁለተኛ ሳምንት ይዘናል።

ዛሬ በተነበቡልን ምንባባቶች የአለም ሁሉ መምህር የሆነው ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዘሪውና የዘሩ ምሳሌ በመጥቀስ በዘር ወራት እንዴት እንደሆነና በምን መልኩ ውጤት ማምጣት እንደሚችል ያስረዳበት መንገድ ነው። እንደዚሁም ለደቀ መዛሙርቱና ለሚሰሙት ሁሉ አብዛኛውን ጊዜ ያስተምር የነበረው በምሳሌ እንደነበር ለማስገንዘብ ወንጌላውያን ትምህርቱንና ምሳሌውን ትርጉሙንም ጭምር በወንጌል ጽፈውት ይገኛል።

ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምሳሌ ያስተማረው ትምህርት ብዙ ከመሆኑ የተነሳ ሁሉም ወቅቱን ጠብቆ የሚነበብና የሚተረጎም ቢሆንም ለማስረጃ ያህል ከነዚሁ ውስጥ መምህራንን በገበሬ የእግዚአብሔርን ቃል በዘር የአድማጮቹን ልቦና በአራት አይነት መሬቶች መስሎ ያስተማረውንና ወንጌላዊ ማቴዎስ በምእራፍ 13:3-23 ጽፎት የሚገኘውን በዘር ወራት ወቅቱን ጠብቆ በዛሬው ቀን ሲነበብ ሰምተናል።

እነሆ ዘሪ ሊዘራ ወጣ ሲዘራም በመንገድ ዳር የወደቀ ዘር ነበር የሰማይ ወፎችም መጥተው በሉት። ብዙ አፈር በሌለበት በጭንጫማ መሬት ላይም የወደቀ ነበር ለመሬቱም ብዙ አፈር ስላልነበረው ወዲያውኑ በቀለ። ጸሃይ በወጣ ጊዜ ግን ጠወለገ ስር ስላልነበረውም ወዲያውኑ ደረቀ። በእሾህ መካከል የወደቀ ዘርም ነበረ በበቀለም ጊዜ እሾሁ አንቆ አስቀረው። በመልካም ምድር ላይም የወደቀ ዘር ነበረ በቀለና ብዙ ፍሬ አፈራ አንዱ መቶ አንዱ ስልሳ አንዱም ሰላሳ ፍሬ ሰጠ ካለ በሁዋላ ጆሮ ያለው መስማትን ይስማ በማለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዘሪውንና የዘሩን ምሳሌ አጠቃልሎአል። (ማቴ 13:3-9)

ይህ ምሳሌያዊ ትምህርት ለእነማንና ስለምን እንደተናገረ የትምህርቱ ጽንሰ ሀሳብ ምን እንደሆነ ሲገልጽ ስለዚህ እያዩ ስለማያዩ እየሰሙም ስለማይሰሙ ስለማያስተውሉም በምሳሌ እነግራቸዋለሁ በማለት ዝርዝር ሁኔታውን ከአስረዳ በሁዋላ መስማት ትሰማላችሁ ግን አታስተውሉም ማየትም ታያላችሁ ግን አትመለከቱም በአይናቸው እንዳያዩ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ በልባቸውም እንዳያስተውሉ ተመልሰውም እንዳይፈውሳቸው የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአልና ጆሮአቸውም ደንቁሮአል አይናቸውንም ጨፍነዋል ሲል ነቢዪ ኢሳይያስ የተናገረውን ቃል ጠቅሶአል። ኢሳ 7:9-10

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ በዘር ምሳሌ ትምህርቱ ያስተማርው አይን እያላቸው ለትምህርቱ ትኩረት ሰጥተው ለማይመለከቱ እየሰሙም ለማያስተውሉት ሰዎች እንደሆነ ጥቅሱ በደንብ ያስተምራል። በዚሁ ምዕራፍ ቁ.18-23 ተጽፎ በሚገኘው ቃል እንደምንረዳው ደግሞ ቀደም ሲል የሰውን ልቦና በአራት የመሬት ዓይነቶች መስሎ ተናግሮ ነበርና ይህንኑ ምሳሌ ክርስቶስ ራሱ አንድ በአንድ እንደተረጎመው መመልከት ይቻላል።

1ኛ/ በመንገድ ዳር የወደቀ ዘር ምሳሌ ነው የዚህ ምሳሌ ትርጉም እንደሚያስረዳው ዘሩን ወፎች ስለለቀሙትና ፈጽሞም ስላልበቀለ ፍሬ ሊሰጥ እንዳልቻለ ሁሉ መንገድ የተባለውም የእግዜአብሔርን ቃል ሰምተው ወዲያውኑ የሚዘነጉ ሰዎች ልቦና ምሳሌ መሆኑ ተገልጦአል። ዘሩን ወፎች እንደለቀሙትና ፍሬም እንዳልሰጠ በምሳሌው ተጠቅሶአል። በወፍ የተመሰለው ሰይጣን ሲሆን እሱም በመምህራን አንደበት የሚነገረው የእግዚአብሔር ቃል በሰው ልቦና ውስጥ በቅሎ የጽድቅ ፍሬ እንዳያፈራ ከሰው ልቦናና አእምሮ የሚነጥቅ ክፉ ባላጋራ እንደሆነ ከምሳሌውና ክርስቶስ ራሱ ከተረጎመው መረዳት ይቻላል።

2ኛ/ በጭንጫማው መሬት ላይ የወደቀ ዘር ምሳሌም የሚያመለክተው ትምህርቱን ለጊዜው ሰምቶ በደስታ ከተቀበለና ከተረዳ በሁዋላ የተለያየ ፈተና ሲያጋጥመው የሚሰናከል ፈጥኖም የሚክድ ሰው ልቦና እንደሆነ በትርጉሜው ተብራርቶአል። ጭንጫው መሬት ባለው ጥቂት አፈርና ርጥበት ምክንያት ዘሩ ለጊዜው ቢበቅልም መሬቱ ጥልቀት ስለሌለውና ስር ስላልሰደደ ጸሐይ በወጣና ድርቅ በሆነ ጊዜ ቡቃያው ወዲያውኑ እንደሚጠወልግና እንደሚደርቅ ሁሉ በሃይማኖት ምክንያት መከራ ወይም ስደት ባጋጠመ ጊዜ ወዲያው የሚሰናከልና የሚክድ ሰው ምሳሌ ነው። ይህ ሰው ቃሉን ሰምቶ ለጊዜው ቢያምንም እስከ መጨረሻው ድረስ ጸንቶ ካልተገኘ ከእግዚአብሔር ዘንድ ዋጋ የሌለው መሆኑን ከምሳሌው መገንዘብ ይቻላል።

ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን አስመልክቶ እንዲህ ይላል ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? በማለት ከጠየቀ በሁዋላ መከራ ወይስ ጭንቀት? ወይስ ስደት? ወይስ ረሃብ? ወይስ መራቆት? ወይስ ፍርሃት? ወይስ ሰይፍ ነውን? በማለት ብሃይማኖት ምክንያት ከሚደርሱት ችግሮች ጥቂቶቹን በመዘርዘር አብራርቶ ሞትም ቢሆን ሕይወትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንደማይችል ተረዳሁ በማለት ያረጋገጠው ሰዎች ስለ ክርስቶስ ተረድተናል ዐውቀናል አምነናል ብለው ቃሉን ከተቀበሉና ከአመኑ በሁዋላ ምንም ዓይነት ችግር ቢያጋጥማቸው እስከ መጨረሻ መጽናት እንዳለባቸው ለመመስከርና ይህ ባይሆን ግን በጭንጫ ምድር ላይ እንደወደቀ ዘር መሆናቸውን ለማስረዳትና ለማስተማር ነው።(ሮሜ 8:35-39)።

3ኛ/ በእሾህ መካከል የወደቀው ዘር በሃይማኖትና በመልካም ስራ ጸንቶ የማይኖር ሰው ምሳሌ ነው። በእሾህ መካከል የተዘራ ዘር ለጊዜው ይበቅላል ያድጋልም። ነገር ግን እሾሁ በግራ በቀኝ ስለሚያንቀውና ከመሬት ሊያገኝ የሚገባውን የማዕድን ምግብ ስለሚሻው የጸሐይ ብርሃንም እንዳያገኝ በጥላው ስለሚጋርደው ለጊዜው ቡቃያው ቢያምርም ፍሬ ሊሰጥ አይችልም።

በዚህም ምሳሌ መሰረት ብዙ ሰዎች ቃሉን ይሰማሉ በመልካም ምግባር በሃይማኖት ጸንተው ለመኖርም ይሞክራሉ ነገር ግን በዚህ ዓለም አሳብና የባለጠግነት ስሜት ምክንያት የሰሙትን የእግዚኣብሔር ቃል ተግባራዊ ማድረግ ስለሚሳናቸው በምግባር በሃይማኖት ጸንተው መኖርና መልካም ስራ መስራት አይችሉም። በዚህም ምክንያት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዚህን ዓለም አሳብና ባለጠግነት በእሾህ መስሎ ተናግሮአል። ምክንያቱም ዘሩ ከበቀለ በሁዋላ እንዳያፈራ እሾሁ አንቆ እንደሚያስቀረው ሁሉ የዚህ ዓለም አሳብና የባለጠግነት ስሜትም የሰውን መንፈሳዊ ፍላጎትና ዕድገት አንቆ ያስቀረዋልና ነው። በአንድ ጊዜ ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው አገልጋይ እንደሌለ ሁሉ ምን ጊዜም ቢሆን ለሃብት የሚጉዋጉዋና ገንዘብንም አጥብቆ የሚወድ ሰው የእግዚኣብሔርን በጎ ፈቃድ ሊፈጽምና የጽድቅ ስራንም ሊሰራ እንደማይችል የታወቀ ነው። ለእግዚኣብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም (ሉቃ 16:13)ተብሎ የተጻፈውም ስለዚህ ነው።

4ኛ/ የእግዚኣብሔርን ቃል ሰምቶ የሚያስተውለውና ተግባራዊም የሚያደርገው ሰው በመልካም መሬት ላይ በተዘራ ዘር ተመስሎአል። መልካም መሬት የሚባለው አፈሩ ጥልቀት ኖሮት ማዳበሪያ የማያስፈልገው የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ፍግ)ያለውና ለም የሆነ በሚገባ የታረሰና የለሰለሰ መንገድ ሆኖም ያልተደመደመ ጭንጫ ያልሆነና እሾህ የሌለው መሬት ማለት ነው። በእንደዚህ ዓይነት መሬት ላይ የተዘራ ዘር ጥሩና ያማረ ሆኖ በየደረጃው አንዱ መቶ አንዱም ስልሳ ሌላው ደግሞ ሰላሳ ፍሬ እንደሚሰጥ በምሳሌው ተጠቅሶኣል። ይህ ምሳሌ የሚያመለክተው በመምህራን አንደበት የሚተላለፈውን የእግዚኣብሔርን ቃል ወቅታዊና ግብታዊ በሆነ ስሜት ምክንያት ከንፈርን በመምጠጥ ሳይሆን በማስተዋል የሚሰሙና ትምህርቱንም ሰምተው ተግባራዊ የሚያደርጉ ሰዎች በየደረጃው የሚያሳዪትን መልካም የስራ ውጤጥ የሚያመለክት ምሳሌ ነው። ባለ መቶ የተባሉትም እንደ ጻድቃንና ሰማዕታት ወይም ስለ ክርስቶስ ፍቅር ሲሉ ዓለምን ንቀው በልዪ ልዪ ገዳማት የሚገኙትንና በፍጹምነት ደረጃ ያሉትን ቅዱሳን የስራ ፍሬ የሚያመለክት ሲሆን ባለ ስልሳና ሰላሳ ፍሬ የተባሉት ደግሞ በማዕከላዊነት በወጣትነትና በጀማሪነት የሚገኙት የእውነተኛ አማኞች ምሳሌ እንደሆነ ከምሳሌው ትርጉም መረዳት ይቻላል። ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው የአባቶች አንደምታ ትርጐአሜም የሚያስረዳው ይህንኑ ነው።

በአጠቃላይ ከዚህ የዘር ምሳሌ መማርና መረዳት የምንችለው ምስጢር ቢኖር ማየትና ማስተዋል መስማትና ልብ አድርጎ መቀበል ልዪነት ያላቸው መሆኑንና ጥሩ የስራ ፍሬ ማፍራትና ጥሩ አማኝ መሆን የሚቻለውም በመስማት ብቻ ሳይሆን የሰሙትን በማስተዋልና ልብ በማድረግ ተረድቶም ተግባራዊ ማድረግ ሲቻል መሆኑን ነው።

ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ በማለት ያስተምረናል። (ያዕ 1:22)

የተወደዳችሁ የእግዚኣብሔር ቤተሰቦች ብዙውን ጊዜ ቃሉን እንሰማለን በየ ፕርግራሞች በተለያዪ ጉባኤዎች በየ ዕለቱና በየ ሳምንቱ ዕሁድ ለመስዋዕተ ቅዳሴ ተገኝተን ቃሉን እንሰማለን ነገር ግን ስንቶቻችን ነን ወደ ተግባራዊነት ለመቀየር እየተጋን ያለው? ምን ያህሎቻችን ነን ቃሉን ሰምተን ለተግባራዊነቱ የምንጥር? እራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል። ለምን ቢባል የብዙዎቻችን ልቡና እንደ መልካሙ መሬት በላዪ ላይ የተዘራውን የእግዚኣብሔር ቃል ማብቀልና ለፍሬ ማብቃትም የማይችል በመሆኑ ነው። ስለዚህ ምንም እንካን ማመን ከመስማት ነው ቢባልም ዋናው ቁም ነገር የሰሙትን በተግባር መግለጥ ስለሆነ ሁላችንም የምናስተምረውና ከመምህራን የምንሰማውን የእግዚኣብሔርን ቃል በተግባር ለመግለጥና መልካም ፍሬ ለማፍራት እንጣር። ምክንያቱም በዛሬው የመጀመሪያው መልዕክት ዕብ 7:7 ላይ ብዙ ጊዜ በእርስዋ ላይ የሚወርደውን ዝናብ የምትጠጣ መሬት ለሚያርሱአትም ደግሞ የምትጠቅምን አትክልት የምታበቅል ከእግዚአብሔር በረከትን ታገኛለችና ይላል ለዚህም የበቃን እንሆን ዘንድ ልዑል እግዚኣብሔር ይርዳን! አሜን።

ምንጭ፡ የቫቲካን ሬዲዮ የአማርኛው የስርጭት ክፍል።

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

11 July 2019, 10:50