ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን፣ ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን፣  

ካርዲናል ፒተር ታርክሰን ሐዋርያዊ አገልግሎት በርካታ ሥራዎችን የሚያካትት መሆን እንዳለበት አሳሰቡ።

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ፣ ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን፣ በኡካንዳ ዋና ከተማ ካምፓላ ላይ 18ኛውን የአፍሪቃ እና ማዳጋስካር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ባሰሙት ንግግር ጳጳሳት እና ካህናት ለእግዚአብሔር ሕዝብ የሚያቀርቡት ሐዋርያዊ አገልግሎት ሁሉን የሚያካትት መሆን እንዳለበት አሳሰቡ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን፣ ዓርብ ሐምሌ 19/2011 ዓ. ም. በኡጋንዳ ዋና ከተማ ካምፓላ ውስጥ ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት፣ ከመጽሐፈ ዘጸዓት ምዕ. 20, 1-17 በቀረበው የመጀመሪያ ንባብ ላይ በማስተንተን ባሰሙት ስብከታቸው፣ ሙሴ ለእግዚአብሔር ሕዝብ በርካታ አገልግሎቶችን ያበረክት እንደነበር አስታውሰዋል። እግዚአብሔር አምላክ ከግብፅ ባርነት ነጻ ያወጣውን የእስራኤል ሕዝብ ወደ አገሩ በመምራት፣ ቀይ ባሕርንም በማሻገር፣ በበረሃ ውስጥ በረሃብ ለሚሰቃይ ሕዝብ ከእግዚአብሔር ዘንድ የወረደለትን መና በመመገብ፣ የተጣሉትንም በማስታረቅ፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረትን በመለመን እና በማጽናናት አገልግሎት እንዲሰጥ ከእግዚአብሔር ዘንድ አደራ እንደተሰጠው አስታውሰዋል። ዛሬም ቢሆን እግዚአብሔር ለቤተክርስቲያን መሪዎች የሰጣቸው የሐዋርያዊ አገልግሎት አደራ ተመሳሳይ መሆኑን አስገንዝበው፣ የቤተክርስቲያን መሪዎችም ለእግዚአብሔር ማበርገት ያለባቸው በርካታ የአገልግሎት ዘርፎች መኖርቸውን ተናግረዋል።

ሙሴ፣ የእስራኤል ሕዝብ ቀይ ባሕርን እንዲሻገር በመራቸው ጊዜ አገልግሎቱ መንፈሳዊ ብቻ እንደሆነ ማሰቡን ያስታወሱት ካርዲናል ታርክሰን፣ ቀይ ባሕርን ከተሻገሩ በኋላ ተርበው ስለነበር ምግብ እንዲሰጣቸው በጮሁ ጊዜ፣ ሙሴ አገልግሎቱ መንፈሳዊ ብቻ ሳይሆን ስጋዊም መሆኑን በመረዳት ከእግዚአብሔር ዘንድ መናን እንደለመነ፣ የሚበላ ብቻ ሳይሆን የሚጠጣንም ውሃን ያቀረበላቸው መሆኑን አስታውሰዋል። ሙሴ ለእግዚአብሔር ሕዝብ ልዩ እንክብካቤን ያደረገበት ምክንያት ሕዝቡን ምንም ዓይነት ስቃይ እንዳይደርስበት ስለፈለገ ነው ብለዋል።

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ፣ ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን ለጉባኤው ተካፋዮች ባሰሙት ስብከት እንደገለጹት ሙሴ ላበረከታቸው አገልግሎቶች በሙሉ ዋና መነሻው የእግዚአብሔር ቃል እንደሆነ አስረድተው ጳጳሳት እና ካህናትም እንደዚሁ ለተጠሩባቸው ሐዋርያዊ አገልግሎቶች በሙሉ መሪ እና አጋዥ የሚሆነው የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ተናግረዋል።

የኒቂያው ቅዱስ ግሬጎሪ ስለ ሙሴ ሲያስተነትን፣ ሙሴ ለእስራኤል ሕዝብ ባቀረበላቸው የተለያዩ አገልግሎቶች የተነሳ እንደ አገልጋይ እንደተቆጠረ መግለጹን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን፣ የቤተክርስቲያን አገልጋዮችም አገልጋይነታቸው ለእግዚአብሔር ብቻ ሳይሆን ለሚያገለግሏቸው ሕዝቦችም ጭምር መሆኑን አስረድተዋል።       

ወደ እብራዊያን በተላከው ሦስተኛ መልዕክት ላይ ያስተነተኑት ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን የሙሴን እና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አገልግሎት በማመዛዘን እንደተናገሩት ኢየሱስ ክርስቶስ አገልግሎቱን ያበረከተው የእግዚአብሔር ልጅ በመሆን፣ ሙሴ ደግሞ የእግዚአብሔር አገልጋይ በመሆን አገልግሎታቸውን ማበርከታቸውን አስረድተዋል። ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን በማከልም ጳጳሳት እና ካህናት በአገልግሎታቸው ከሁሉ አስቀድሞ እግዚአብሔርን ማገልገል እንዳለባቸው፣ ቀጥለውም የእግዚአብሔር ሕዝብ አገልጋይ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የአፍሪቃ ታላቅ ወዳጅ የነበሩት የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ 6ኛ በ1961 ዓ. ም. ወደ ኡጋንዳ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ባደረጉበት ወቅት የአፍሪቃ እና ማዳጋስካር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ሲምፖዚየምን መመስረታቸው ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ 6ኛ የአፍሪቃ ብጹዓን ጳጳሳት ሲምፖዜም በመሠረቱበት ወቅት አፍሪቃን አስመልክተው በጻፉት “የአፍሪቃ ምድር” በተሰኘው ሐዋርያዊ መልዕክታቸው በኩል እንደገለጹት የአፍሪቃ ምድር፣ ሕዝቦቿ እድገትን የሚያዩበት የግል ይዞታዋ ነው ብለው፣ በምድራቸው የወንጌል መልዕክተኞች የሚያደርጋቸውን አዳዲስ ዘዴዎችን ማመቻቸት ይችላሉ ማለታቸው ይታወሳል። የመላው አፍሪቃ እና ማዳጋስካር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ከሃምሳ ዓመታት በፊት፣ በ1961 ዓ. ም. የተመሰረተው በሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ማግስት፣ በአፍሪቃ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በጎ ፈቃድ እና ምኞት መሆኑ ሲታወቅ ዓላማውም አንድነትን በማሳደግ የቤተክርስቲያናቸውን ድምጽ ለኩላዊት ቤተክርስቲያን እና ለቅድስት መንበር በጋራ ለማሰማት በማለት እንደሆነ ታውቋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

            

29 July 2019, 16:09