ሚያዝያ 25 አስተንትኖ ሚያዝያ 25 አስተንትኖ  

የሰው ልጆች ሆይ ለምንድነው ከንቱ ነገር የምትፈልጉት?

ሚያዝያ 25 አስተንትኖ

ከአንድ እግዚአብሔር አምላክ በስተቀር ሌላ ሁሉ ከንቱ ነው፡፡ በሰማይና ምድር የሚገኝ ነገር ሁሉ ፈጣሪ ጌታ ነው፡፡ ከኢምንት የተፈጠረ በመሆኑ በሙሉ ከእርሱ ኃይል እጅና ሊለካ ከማይቻል ዕውቀቱና ጥበቡ ወጥቶ የተገኘ ነው፡፡ እኛም ከንቱ ነን፤ ምክንያቱም እንደ ሌላ ፍጡር ሁሉ ከከንቱና ከኢምንት ተፈጥረን የመጣንና የተገኘን ነን፡፡ እግዚአብሔር እኛን ሲፈጥረን በደግነቱ ፈጠረን፤ ለዚህ አላፊ ዓለም ሳይሆን ለዘለዓለም ለሚኖር መንግሥተ ሰማያት ፈጠረን፡፡ በምድር እርሱን ልናገለግል፣ ለምድራዊ አላፊ ደስታ ሳይሆን ከዚህ ምድራዊ ዘመን በኋላ የሚጠብቀንን ሰማያዊ ደስታ እንድንፈልግ አዘዘን፡፡ በዚህ አኳያ ምድራዊ ህላዌያችን ግቡን የሚመትው መንግሥተ ሰማያተን ስንወርስ ብቻ ነው፡፡ ግን ይህ የተበላሸ ባሕሪያችን ከእግዚአብሔር ውሳኔ ሊያወጣን ይፈልጋለ፡፡ ዓለም የእግዚአብሔርን መንፈስ አጥፍቶ በጊዜያዊ ሀብትና ደስታ ምኞት ይመለሳል፡፡ አኛም መንፈሳውያን ሀብት ከመፈለግ፣ በጊዜያዊ ደስታ ተታለንና በሥጋዊ ክፉ ምኞት ተገፋፍተን ሥጋዊውን ጠቀሜታብቻ እንፈልጋለን፡፡

በዓለም ላይ የሚገኝ ሀብት፣ ተድላና ደስታ በማታለል መንፈሳችንን ስለሚያዘናጋብን ዋናውንና የነፍሳችንን ጉዳይ ያስረሳናል፡፡ በዚህ ሁኔታ እግዚአብሔርን ረስተን ሥጋችንን ብቻ እናስባለን፤ ብሎም እንከባከባለን፡፡ ለዚህ ፈራሽ ሰውነታችን አጥብቀን እንድንቸገር ያደርገናል፡፡ በሥጋ መልካም ጤንነነት ስናገኝ የመንፈስ ሥራችን ያስጠላናል፣ ልባችን በዓለም ሐሳብ ከደነዘዘና ከታወረ ከሰማይ ሐሳብ ይሸሻል፣ ዘለዓለማዊውን ደስታ ማስተዋል ያዳግተናል፣ አጅግ ያስቸግረናል፣ እንደ ከባድ ጫና ይከብደናል፡፡

ነቢዩ ዳዊት «ልጆቼ ሆይ ስለምንድነው ከንቱን ፍጡር የምታስቡና የምትሹ;´ (መዝሙር 4) እያለ ይገስጸናል፤ በጥብቅም ያስጠነቅቀናል፡፡ ጌታችንን እንመን በመንፈስ ሞኞች መሆን በመተው ፈጥነን እንታረም ወደ ፈጣሪያችን በማሰብ ወደ እርሱ እንመለስ፤ እርሱ ነው የሚጠቅመን ልባችን በዓለም በሚገኙ ሥጋዊ ነገሮች ከደነዘዘ ከሰማይ ደስታ ይሸሻል፡፡ ዘለዓለማዊውን ማየትና ማሰብ ያዳግተዋል፡፡ ምን ለማግኘት ነው ፈጣሪያችንን ጥለን እርሱን ትተን እንደ እኛ ፍጡር ወደ ሆነው የምናዳላ; ስለምንድነው ከሁሉ አብልጦ የሚወደንና የሚንከባከበን ደጉን ሰማያዊ አባትነት ንቀን እርሱን ተጸይፈን ከንቱ ወደ ሆነው ፍጡር የምናዘነብልና የምናዳላ; የምድራዊ ፍጡር ሰበብና ጠንቅ ለጊዜው አይገባንም በኋላ ግን መራራና የማይዋጥ እሬት ነው፡፡ በዓለም የምናገኘው ደስታ አያጠግበንም ብሎም አያረካንም፣ ፈጽሞ አይቻልም፡፡ ጊዜያዊ ለጊዜው ተአምር የሚሠራ በመሆኑም ሁሉ ጐደሎና አላፊ ነው፡፡

አዎ ከከንቱ ነገር የመጣን ብንሆንም ለከንቱ የተመደብን አይደለንም ለእግዚአብሔር እንጂ ለጊዜያዊና ለአላፊ ነገር አልተፈጠርንም፡፡ ማዕረጋችንን አናበላሽ የአምላክን ውሳኔ አንጣል፡፡ እኛ ለመንግሥተ ሰማያት የተወሰንን በመሆናችን እግዚአብሔርን መመኘት አለብን፡፡ ይህን ከንቱ ምድራዊ ገንዘብ ሀብት ብንወድ ራሳችን ከንቱ እንሆናለን፡፡ ይህ ዓለም ካለፈ የማያልፍ ስቃይ እንቀበላለን፤ ከዚህም ማምለጫና መውጫ በሌለው ለዘለዓለም በገነነመ እሳት እንቃጠላለን፡፡ እግዚአብሔርን ብንወድ ግን ከእርሱ ጋር ለዘለዓለም በመንግሥተ ሰማያት ከብረን ነግሠን እንኖራለን፡፡

03 May 2019, 16:30