የግንቦት 18/2011 ዓ.ም ዘትንሣኤ 5ኛ እለተ ሰንበት ቅዱስ ወንጌል አስተትኖ የግንቦት 18/2011 ዓ.ም ዘትንሣኤ 5ኛ እለተ ሰንበት ቅዱስ ወንጌል አስተትኖ 

የግንቦት 18/2011 ዓ.ም ዘትንሣኤ 5ኛ እለተ ሰንበት ቅዱስ ወንጌል አስተትኖ

የእለቱ ምንባባት

1.     ሮሜ 4፡ 14-25

2.    ራእ 20፡ 1-15

3.    ሓዋ ሥራ 10፡ 39-43 

4.    ዮሓ 21፡ 1-14

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ደቀ መዛሙርቱ ዓሣ በታምር መያዛቸው

ከዚያም በኋላ ኢየሱስ በጥብርያዶስ ባሕር እንደ ገና ለደቀ መዛሙርቱ ታየ፤ በዚህም ሁኔታ ተገለጠ፤ ስምዖን ጴጥሮስ፣ ዲዲሞስ የተባለው ቶማስ፣ የቃና ዘገሊላው ናትናኤል፣ የዘብዴዎስ ልጆችና ከደቀ መዛሙርቱ ሌሎች ሁለት አንድ ላይ ነበሩ፤ ስምዖን ጴጥሮስም፣ “ዓሣ ላጠምድ መሄዴ ነው” አላቸው፤ እነርሱም፣ “እኛም ከአንተ ጋር እንሄዳለን” አሉት። ወጥተውም ወደ ጀልባዋ ገቡ፤ በዚያ ሌሊት ግን ምንም አላጠመዱም። ሲነጋም፣ ኢየሱስ በባሕሩ ዳርቻ ቆመ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ኢየሱስ መሆኑን አላወቁም ነበር። እርሱም፣ “ልጆች፣ ዓሣ አላችሁ?” አላቸው። እነርሱም፣ “የለንም” አሉት።

እርሱም፣ “መረባችሁን ከጀልባው በስተ ቀኝ ጣሉ፤ ዓሣ ታገኛላችሁ” አላቸው። እነርሱም በጣሉ ጊዜ ከዓሣው ብዛት የተነሣ መረቡን መጐተት አቃታቸው። ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀ መዝሙርም፣ ጴጥሮስን፣ “ጌታ እኮ ነው!” አለው። ስምዖን ጴጥሮስም፣ ‘ጌታ እኮ ነው!’ የሚለውን ቃል በሰማ ጊዜ፣ አውልቆት የነበረውን መደረቢያ ልብስ ታጠቀና ዘሎ ወደ ባሕሩ ገባ። 8ሌሎች ደቀ መዛሙርት ግን ከባሕሩ ዳርቻ የራቁት ሁለት መቶ ክንድ ያህል ብቻ ስለ ነበር፣ ዓሣ የሞላበትን መረብ እየሳቡ በጀልባዋ መጡ። 9ወደ ምድርም በደረሱ ጊዜ፣ ዓሣ በላዩ የነበረበት የከሰል ፍምና እንጀራ አዩ። ኢየሱስም፣ “አሁን ካጠመዳችሁት ዓሣ እስቲ አምጡ” አላቸው። ስለዚህ ስምዖን ጴጥሮስ ወደ ጀልባዋ ወጥቶ መረቡን ወደ ምድር ጐተተው፤ መረቡንም መቶ አምሳ ሦስት ትልልቅ ዓሣ ሞልተውት ነበር፤ ይህን ያህል ቢይዝም መረቡ አልተቀደደም። ኢየሱስም “ኑ፤ ቍርስ ብሉ” አላቸው። ጌታ እንደሆነ ዐውቀው ስለ ነበር፣ ከደቀ መዛሙርቱ፣ “አንተ ማን ነህ?” ብሎ ለመጠየቅ የደፈረ አልነበረም። ኢየሱስም መጥቶ እንጀራውን አንሥቶ ሰጣቸው፤ዓሣውንም ሰጣቸው። እንግዲህ ኢየሱስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ሲታይ ይህ ሦስተኛ ጊዜ ነው።

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

በክርሰቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም መልካም ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ ዛሬ እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር የትንሳኤ ኣምስተኛ ሰንበትን እናከብራለን።

እግዚአብሔር ሁሌም ሕይወታችን የተቀደሰ የተስተካከለ እንዲሆን ይፈልጋል ስለዚህ ዘወትር በሚሰጠን ጸጋና በረከት ብቻ ሳይሆን በየዕለቱ በተለይም በየሰንበቱ በሚሰጠን የመጽሓፍ ቅዱስ ንባባት ኣማካኝነት የእርሱን መንገድ ያሳየናል ለየዕለቱ የሚሆን የሕይወት መመሪያ ይሰጠናል። እኛም ይህንን የሕይወት መምሪያ ማዳመጥ ብቻ ሳይሆን ካዳመጥንም በኋላ በሕይወታችን ለመተግበር ብርቱ ጥረት እንድናደርግ ያስፈልጋል።

በዚህም መሠረት እንግዲህ ዛሬ በመጀመሪያ ንባብ እንዳዳመጥነው ቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ በሮሜ ሰዎች ኣድርጎ ወደ እያንዳዳችን ይመጣል እንዲህም ይለናል እምነት የክርስትና ሕይወታችንን የምንመራበት ሥር መሠረት በመሆኑ በሕይወታችን ውስጥ ትልቅ ቦታ ልንሰጠው እንደሚገባ ያሳስበናል።

እንግዲህ እምነት ስንል ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የእግዚኣብሔር ልጅ መሆኑን የሰውን ልጅ ከኃጢያት ለማንፃት በኣባቱ መልካም ፈቃድ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በኩል ኣድርጎ ወደ ምድር መምጣቱን ስለሰው ልጅ ኃጢያት ሲል መሰቃየቱን መሞቱን መቀበሩን በሦስተኛ ቀንም ከሙታን ተለይቶ መነሳቱን ማመንና ከዚህም እምነት የሚመነጨውን መንፈሳዊ ቡራኬ በዕለት ተዕለት ኑሮኣችን ተግባራዊ ማድረግ ማለት ነው። በዚህ በመጀመሪያው ንባብ ቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ ሰለ እምነትና ሕግ ዘርዘር ኣድርጎ ያስረዳናል። እውነት ነው ሕግን መጠበቅ ሕግን መፈጸም ተገቢ ነገር ሆኖ ሳለ ሰው ግን የሚጸድቀው ሕግን በመጠበቁ ብቻ ኣይደለም ይልቁንም ከእግዚኣብሔር ከሚመጣ ምሕረትና ከእርሱ ቸርነት የተነሳ ብቻ ነው። ሰው ምን ያሕል ጠንካራና ጥንቁቅ ቢሆንም በዕድሜ ልኩ ሁሉ ሕግን ብቻ ጠብቆ ሊኖር ኣይችልም የምንኖረው ገና በዚህ ምድር በመሆኑ ይህ ምድር ደግሞ በብዙ ክፋትና ኃጢያት የተተበተበ በመሆኑ በክርስትና ጉዞኣችን ሁሌም ሕግን ብቻ ጠብቀን ለምጓዝ ኣንችልም። በጉዞኣችን መውደቅና መነሳት መድከምና መበርታት ኣለ ነገር ግን ትኩረታችን ሕግ ላይ ብቻ ከሆነ የምንሰጠው መንፈሳዊ ኣገልግሎት ይሁን መንፈሳዊ ጉዞኣችን ልክ የሙሴ መምሕራንና ፈሪሳውያኑ ያደርጉት እንደነበረው ለታይታና ከሰው ዘንድ ምስጋናና ከበሬታ ለመሰብሰብ ብቻ ይሆናል።

ሁልጊዜም ትኩረታችን ሕግ ላይ ብቻ ከሆነ ሕግን ባፈረስን ጊዜ ቁጣና ቅጣት ይኖራል ይህም ከእግዚኣብሔር ጋር ያለንን መልካም ግንኙነት ያደፈርሳል እግዚኣብሔር ደግሞ ለልጆቹ ያለውን የምሕረትና የኣባትነት ባሕሪ ዋጋ ያሳጣል። ስለዚህ ቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ ሕግን ብቻ ለመጠበቅ ሳይሆን እምነታችንን ከጊዜ ወደ ጊዜ ከቀን ወደቀን እያጠነከርንና እያበረታን እንድንሄድ ያሳስበናል ምክንያቱም ቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ ወደ ገላትያ 3፡29 ላይ እንደጻፈው ወራሽ የመሆን መብት ወይም ዋስትና የሚገኘው በእምነት ብቻ መሆኑን ይገልፃል። ስለዚህ በእምነት በኩል ጸጋና በረከት እናገኛለንና እምነታችንን በየጊዜው ለማሳደግ ብርቱ ጥረት ማድረግ ይጠበቅብናል። ሕግን  ብቻ ለመፈፀም የምንጥር ከሆነ ግን በስተመጨረሻ ከቅጣትና ከፍርድ ኣናመልጥም።

ቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ የኣብርሃምን እምነት እንደ ምሳሌ ኣድርጎ ይወስዳል እንዲሁ የእኛም እምነት የኣብርሃምን እንዲመስል ይፈልጋል። ኣብርሃም በሕይወቱ ብዙ መከራና ፈተና ደርሶበታል ነገር ግን በእነዚህ ፈተናዎች ሁሉ ለእግዚኣብሔር ያለውን ታማኝነትና የእምነቱን ጠንካራነት ኣስመሰከረበት። ዛሬም ከእኛ የሚጠበቀው ይኸው ነው በየትኛውም ዓይነት ፈተናና መከራ ውስጥ ብናልፍ ይህ መከራና ፈተና ምን ያህል ታማኞችና በእምነታችን ጠንካሮች መሆናችንን የምናስመሰክርበት ኣጋጣሚ እንጂ የውድቀታችን መገለጫ ሊሆን ኣይገባም።

ኣለማመን የእግዚኣብሔርን ክብር ይቀንሳል ኣለማመን ወደ ተስፋ መቁረጥ ይመራል ኣለማመን ሰውን ወደ ግዴለሽነት ይመራል ኣለማመን የሕሊናን ድምጽ እንዳንሰማ ይከለክላል ኣለማመን ሰው የተፈጠረበትን ዓላማ እንዲስትና በስሜታዊነት ብቻ እንዲመራ ያደርጋል ኣለማመን ሰውን ወደ ኃጢኣትና ወደ ጨለማ ውስጥ ኣንዲወርድ ያደርጋል ስለዚህ እኛ በየጊዜው እምነታችንን በመፈተሽ ከእንደዚህ ዓይነቱ የጥፋት መንገድ ራሳችንንም ሆነ በክርስቶስ ያገኘናቸውን ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን እንድንታደግ ያስፈልጋል።

ቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ ኣብርሃም እምነቱ ጽድቅ ሆኖ እንደተቆጠረለት በዚሁም ምክንያት የዘለዓለም ሕይወት ወራሽ እንደሆነ ሁሉ እኛም እምነታችን ጠንካራ ሆኖ እንደ ጽድቅ እንዲቆጠርልን በዚሁም ምክንያት የዘለዓለም ሕይወት ወራሾች እንድንሆን ያበረታታናል። በዮሓንስ ራዕይ ላይም ወንጌላዊው ዮሐንስ በራዕዩ ለእግዚኣብሔር በመታመንና እግዚኣብሔርን በመፍራት የኖሩ ሰዎች ሁሉ መጨረሻቸው ያማረና በመንግስተ ሰማይ ከሰማዕታትና ከቅዱሳን ጋር ዳግመኛ ሞት በሌለበት እንደሆነ ይናገራል። እንዲሁም ሰዎች ሁሉ የሚድኑት በእምነታቸው ቢሆንም የእውነተኛ እምነት መገለጫው ደግሞ በመልካም ሥራ ነውና እኛም በምድር ላይ እያለን የሰራነው መልካም ሥራ ሁሉ በኋላ በመልካም ሥራ መዝገብ ውስጥ እንደሚጠብቀን ይናገራል። መልካም ያልሰራን ከሆነ ደግሞ ሥማችን በሕይወት መዝገብ ላይ ሰፍሮ ኣይገኝምና ከወዲሁ የመልካም ሥራ ሁሉ ተካፋዮች በመሆን የምድራዊም ሆነ የሰማያዊ ቤታችንን አንድናዘጋጅ ይጋብዘናል። የዛሬው የዮሓንስ ወንጌልም የሚያስረዳን ነገር ቢኖር እምነታችንን በእግዚኣብሔር ላይ ጥለን የምናደርገው ነገር ሁሉ ሁል ጊዜም ውጤታማና የተሳካ እንደሚሆን ያስተምረናል። በዛሬው በዮሓንስ ወንጌል እንዳዳመጥነው ሓዋርያቶች ሌሊቱን ሙሉ ዓሣ ለማጥመድ ሲደክሙ ኣድረው ምንም ዓይነት ዓሣ ለማጥመድ ኣልቻሉም ነገር ግን ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በዚህ በስተቀኝ በኩል መረባቸውን እንዲጥሉ ነገራቸው እነርሱም በሙሉ እምነት መረባቸውን በስተቀኝ በኩል ጣሉት ሌሊቱን ሙሉ ሲደክሙ ምንም ዓይነት ዓሣ ያላገኙት ኣሁን ግን በታዘዙት መሠረት መረቡን በመጣላቸውና በእርሱም ቃል ታምነው እንዳላቸው በማድረጋቸው እጅግ በጣም ብዙ ዓሣ ኣጠመዱ  ከዓሣውም ብዛት የተነሳ መረቡን ለመጎተት ኣቃታቸው። እንግዲህ ይህ የሚያስተምረን እኛም ዘወትር በምናደርገው ነገር ሁሉ የጌታችን እየሱስ ክርስቶስን እርዳታ የእርሱ ጸጋ ከእኛ ጋር ካለ የማይሳካ ነገር ኣይኖርም ስለዚህ ኣጥብቀን የእርሱን እርዳታ መለመን ወይም መጸለይ ያስፈልገናል። በምናደርገው ነገር ሆነ በምንናገረው ነገር ሁሉ የጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእኛ ጋር ካለ ሥራችን ሆነ ቃላችን የተሳካና ኣጥጋቢ እንዲሁም ገንቢ ይሆናል።

እምነታችንን እንዲጨምርልን ከእምነታችንም በምናገኘው ጸጋና ብርታት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስን በሙሉ ልብ መከተል እንድንችልና እውነተኛ ይእርሱ ደቀመዝሙር ለመሆን እንድንበቃ እመቤታችን ቅድስት ማርያም ታግዘን ከልጇ ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ይህንን መንፈሳዊ በረከት ታሰጠን።

ምንጭ፡ ራዲዮ ቫቲካን የአማርኛው ክፍል አገልግሎት

25 May 2019, 17:46