የግንቦት 11/2011 ዓ.ም የአራተኛው የፋሲካ እለተ ሰንበት ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የግንቦት 11/2011 ዓ.ም የአራተኛው የፋሲካ እለተ ሰንበት ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ 

የግንቦት 11/2011 ዓ.ም የአራተኛው የፋሲካ እለተ ሰንበት ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

“በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ፤ እኔ ዐውቃቸዋለሁ፤ እነርሱም ይከተሉኛል”

የእለቱ ምንባባት

1.     የሐዋ. 13፡14, 43-52

2.     መዝ. 99

3.     ራእይ 7፡9, 14-17

4.     ዮሐንስ 10፡27-30

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ፤ እኔ ዐውቃቸዋለሁ፤ እነርሱም ይከተሉኛል፤ እኔ የዘላለም ሕይወት እሰጣቸዋለሁ፤ ከቶ አይጠፉም፤ ከእጄም ሊነጥቃቸው የሚችል ማንም የለም።እነርሱን የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል፤ ከአባቴም እጅ ማንም ሊነጥቃቸው አይችልም። እኔና አብ አንድ ነን።”

የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

ዛሬ የተነበበልን ቅዱስ ወንጌል (ዮሐንስ 10፡27-30) ውስጥ ኢየሱስ ራሱን የእግዚአብሔር ሕዝብ መልካም እረኛ እንደ ሆነ አድርጎ ራሱን ያቀርባል። እርሱ በመንጋው ውስጥ የሚገኙ በጎችን እንዲጠብቁ ከሾማቸው ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ያለውን የግንኙነት ትስስር በመግለጽ በዚህም መሰረት መንጋው እና የመንጋው ጠባቂ መናበብ እንደ ሚገባቸው አጽኖት ሰጥቶ ይገልጻል። በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ፤ እኔ ዐውቃቸዋለሁ፤ እነርሱም ይከተሉኛል፤ እኔ የዘላለም ሕይወት እሰጣቸዋለሁ፤ ከቶ አይጠፉም፤ ከእጄም ሊነጥቃቸው የሚችል ማንም የለም” (ዩሐንስ 10፡27-28)። ይህንን ዓረፍተ ነገር በጥንቃቄ በማንበብ የኢየሱስ ሥራ በተወሰኑ ድርጊቶች የተገለጠ መሆኑን እንመለከታለን፡ ኢየሱስ ይናገራል፣ ኢየሱስ ያውቃል፣ ኢየሱስ የዘላለምን ሕይወት ነው፣ ኢየሱስ እኛን ይነካባከባል።

መልካም እረኛ - ኢየሱስ ለእያንዳንዳችን በትኩረት በመስጠት እኛን ይፈልጋል እኛን ይወደናል፣ ቃሉን ይጠብቃል፣ ልባችንን፣ ምኞቶቻችንንና ተስፋችንን እንዲሁም የእኛን ውድቀቶችና ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎች ያውቃል። እኛ ልክ አሁን እንዳለነው ከእነ ጥንካሬያችን እና ስህተቶቻችን ጭምር እኛን ይወደናል። ለእያንዳንዳችን "የዘላለምን ሕይወት ይሰጠናል" ያም ማለት ዘላለማዊ የሆነ ሙሉ ሕይወት ይሰጠናል። በተጨማሪም አስቸጋሪ በሆኑ መንገዶችን እንድንሻገር እና በህይወት ውስጥ የሚያጋጥሙንን አስቸጋሪ የሆኑ የሕይወት መንግዶችን እንድንወጣ ያግዘናል በፍቅር ይመረናል።

መልካም እረኛ የሆነውን የኢየሱስን መንገድ የሚገልጹልን ግሦች እና ተግባሮች በመጠቀም መልካሙ እረኛ ከእኛ ጋር ግንኙነት በመፍጠር በጎቹን እንዴት መንካብከብ እንደ ሚገባን እና በጎቹ ራሳቸው ከእረኛው ጋር ሊኖራቸው ስለሚገባው ግንኙነት ማለት “ድምጹን መስማት እና እርሱን መከተል” የሚሉትን ሐሳቦች በጎቹ እንዲከተሉ ያቀርባል። እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ተግባሮች ደግሞ እኛ በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ሆነን ከጌታ ጋር መዛመድ እንዳለብን የሚያሳዩ ተግባሮች ናቸው። በእርግጥ ድምፁን መስማትና መገንዘብ የሚያመለክተው ከእርሱ ጋር ያለንን ግንኙነት ነው፣ ይህም በጸሎት መንፈስ በመሆን ልባችን ጌታ እና የሕይወታችን መለኮታዊ እረኛ ከሆነው ከእርሱ ጋር እንዲገናኝ ማድረግን ያመለክታል። ከኢየሱስ ጋር የምናደርገው እንዲህ ዓይነቱ በግልጽነት የተሞላ ግንኙነት፣ ከኢየሱስ ጋር መነጋገሩ፣ እኛ እየተከተልነው ከነበረው የተሳሳተ ጎዳና ውስጥ ወጥተን ራስ ወዳድነትን የሚንጸባረቅባቸውን ስነ-ምግባሮችን በመተው፣ በአዲሱ የወንድማማችነት መንገድ እና እርሱ በአዲስ መልክ ለእኛ በስጦታ መልክ የሰጠንን መንገድ  ለመከተል ያለን ፍላጎት ያጠናክርልናል።

እኛን የሚያናገር፣ የሚያውቀን፣ የዘለአለም ህይወትን የሚሰጠንና የሚጠብቀን ብቸኛው መልካም እረኛ  ኢየሱስ ብቻ መሆኑን መርሳት የለብንም። እኛ ደግሞ የእርሱ መንጋዎች በመሆናችን የተነሳ የእርሱን ድምጽ ብቻ ለመስማት መዘጋጀት የሚጠበቅብን ሲሆን እርሱም በፍቅር እና በልበ ቅንነት ተሞልቶ በልባችን ውስጥ ያናገረናል። በዚህ ሁኔታ ከመልካሙ እረኛችን ጋር የምናደርገው ቀጣይነት ያለው ግንኙነት፣ ከእርሱ ጋር የምናደርገው ንግግር ወደ ዘለዓለም ሕይወት የምናደርገውን ጉዞ በደስታ እንድንጀምር የሚያደረግን ፍላጎት ይመነጫል።

አሁን ደግሞ የመልካም እረኛው እናት ወደ ሆነችው ወደ ማርያም እንመልከት። የእግዚአብሄርን ጥሪ በፍጥነት የተቀበለችው፣ በተለይም ለክህነት አገልግሎት እና ለተቀደሰ ህይወት ጥሪ የተጋበዙ ሰዎች ክርስቶስን በወንጌል ምስክርነት እንዲያገለግሉ እና መንግሥቱን በደስታ እንዲያገለግሉ በዚህም የአገልግሎት ሂደት ውስጥ በቀጥታ በደስታ ተሞልተው ተሳታፊ እንዲሆኑ ትረዳቸው ዘንድ አማላጅነቱዋን እንማጸናለ።

ምንጭ፡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በግንቦት 04/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ካደርጉት አስተንትኖ የተወሰደ።

18 May 2019, 11:26