የፓኪስታን ብጹዓን ጳጳሳት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ሆነው የፓኪስታን ብጹዓን ጳጳሳት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ሆነው 

የፓኪስታን ቤተክርስቲያን በወንጌል ተልዕኮ ላይ ያተኮረ የወጣቶች ዓመት እንደምታዘጋጅ አስታወቀች።

የፓኪስታን ብጹዓን ጳጳሳት የአገራቸው ወጣቶች በተያዘለት ዓመት የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ለማከናወን አቅደው በበላይነት እንዲመሩት እና በያዝነው ጎርጎሮሳዊያኑ 2019 ዓ. ም. በሚከበረው የክርስቶስ ንጉስ በዓል የሚጀምር እና በቀጣዩ ዓመት በሚከበረው ተመሳሳይ ክብረ በዓል የሚዘጋ እቅድ መዘርጋታቸውን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በፓኪስታን ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ሥር የሚገኝ የወጣቶች ሐዋርያዊ አገለግሎት አስተባባሪ ምክር ቤት በካራቺ ሀገረ ስብከት በሚገኘው በቅዱስ ፓትሪክ ካቴድራል፣ በመጋቢት 26 ቀን 2011 ዓ. ም. ባድረገው ስብሰባ የጎርጎሮሳዊው 2020 ዓ. ም. የወጣቶች ዓመት እንዲሆን መወሰኑ ታውቋል።     

ዘንድሮ በጥቅምት ወር 2011 ዓ. ም. በቫቲካን ከተማ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ  በወጣቶች ጉዳይ ላይ ያካሄደውን 15ኛ ጠቅላላ መደበኛ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤን ግንዛቤ ውስጥ ያስገባው የፓኪስታን ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የጎርጎሮሳዊው 2020 ዓ. ም. የወጣቶች ዓመት እንዲሆን መወሰኑ ታውቋል። በፓክስታን የጎርጎሮሳዊው 2020 ዓ. ም. የወጣቶች ዓመት ሆኖ እንዲቀርብ የተደረገበት ዋና ዓላማ ዓመቱ የወጣቶችን ሕይወት የምናጠናክርበት፣ ወጣቶችን የምንከባከብበት፣ የምናዳምጥበት እና በመንፈሳዊ ጉዞዋቸው በቅድስና እንዲያድጉ እገዛ የሚሰጥበት ዓመት እንደሚሆን የሐይደራባድ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሳምሶን ሹካርዲን ፊደስ ለተባለ የቫቲካን የዜና ማዕከል ገልጸዋል።

በፓኪስታን ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ፣ የወጣቶች ሐዋርያዊ አገለግሎት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ስብሰባን ካጠናቀቁ በኋላ ለፊደስ የዜና ማሰራጫ ማዕከል ሃሳባቸውን እንደገለጹት አንድ ሳምንት የወሰደው የወጣቶች ስብሰባ ዋና ዓላማ ወጣቶቹ በእምነታቸው እንዲያድጉ፣ በሚኖሩበት ሕብረተሰብ መካከል ደስተኞች ሆነው የሚኖሮበትን መንገድ ለመጠቆም እንደሆነ ገልጸዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኤማሁስ ይጓዙ ከነበሩ ደቀ መዛሙርት ጋር አብሮአቸው የመጓዙ ታሪክ እጅግ እንደማረካቸው፣ በቫቲካን ከተማ የተካሄደውን የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ 15ኛ ጠቅላላ መደበኛ የጳጳሳት ጉባኤን የተካፈሉት ብጹዕ አቡነ ሳምሶን ሹካርዲን ገልጸዋል።     

የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ከዓለም ዙሪያ ከተወጣጡ ወጣቶች ጋር ሆነው ከመስከረም 23 ቀን እስከ ጥቅምት 17 ቀን 2011 ዓ. ም. ድረስ በቫቲካን ከተማ ባደረገው የብጹዓን ጳጳሳት 15ኛ ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤ ወጣቶች፣ እምነት እና ጥሪያቸውን በጥበብ እና በማስተዋል ተገንዝበው ትክክለኛ እና ቆራጥ ውሳኔን እንዲያደርጉ በሚል ርዕሥ ሰፊ ውይይትን ካደረጉ በኋላ የጉባኤያቸውን ጠቅላላ ሃሳብ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ማቅረባቸው ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም የጉባኤውን ጠቅላላ ሃሳብ ተቀብለው ከተመለከቱት በኋላ በፊርማቸው ማጽደቃቸው ይታወሳል። ይህ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አዲሱ ቃለ ምዕዳን በመጋቢት 24 ቀን 2011 ዓ. ም. ለንባብ መብቃቱን ይታወሳል።

የፓኪስታን ብጹዓን ጳጳሳት የአገራቸው ወጣቶች በተያዘለት ዓመት የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ለማከናወን አቅደው በበላይነት እንዲመሩት እና በያዝነው ጎርጎሮሳዊያኑ 2019 ዓ. ም. በሚከበረው የክርስቶስ ንጉስ በዓል የሚጀምር እና በቀጣዩ ዓመት በሚከበረው ተመሳሳይ ክብረ በዓል የሚዘጋ እቅድ መዘርጋታቸውን ገልጸዋል።

ለዓመቱ የተመረጠው መሪ ቃልም ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ፣ ከትንቢተ ኢሳይያስ ምዕ. 6: 8 ላይ “እነሆኝ፤ እኔን ላከኝ” የሚል እንደሆነ የገለጹት ብጹዕ አቡነ ሳምሶን ሹካርዲን በዚህ መሪ ጥቅስ አማካይነት ወጣቶች እንደሌሎች የቤተክርስቲያን አገልጋዮች የተጠሩበትን የአገልግሎት መንገድ በሚገባ አውቀው የወንጌል ተልዕኮ ጥሪ አማካይነት ቤተክርስቲያናቸውን እንዲያገልግሉ ለማድረግ ነው ብለዋል። 

10 April 2019, 15:13