ፈልግ

የሚያዝያ 06/2011 ዓ.ም አምስተኛው የዐብይ ጾም ሰንበት ቃለ እግዚኣብሔር አስተንትኖ የሚያዝያ 06/2011 ዓ.ም አምስተኛው የዐብይ ጾም ሰንበት ቃለ እግዚኣብሔር አስተንትኖ 

የሚያዝያ 06/2011 ዓ.ም አምስተኛው የዐብይ ጾም ሰንበት ቃለ እግዚኣብሔር አስተንትኖ

ኢየሱስም ቀና ብሎ፣ “አንቺ ሴት፣ ሰዎቹ የት ሄዱ? የፈረደብሽ የለምን?” አላት። እርሷም፣ “ጌታ ሆይ፤ አንድም የለም” አለች። ኢየሱስም፣ “እኔም አልፈርድብሽም፤ በይ ሂጂ፤ ከእንግዲህ ግን ኀጢአት አትሥሪ” አላት።

የእለቱ ምንባባት

1.     ኢሳያስ 43፡16-21

2.     መዝ. 125

3.     ፊሊ. 3፡8-14

4.     የሐንስ 8፡1-11

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

በምንዝር የተያዘች ሴት

ኢየሱስ ግን ወደ ደብረ ዘይት ሄደ። በማለዳም በቤተ መቅደስ አደባባይ እንደ ገና ታየ፤ ሕዝቡም በዙሪያው ተሰበሰበ፤ ሊያስተምራቸውም ተቀመጠ። የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን በምንዝር የተያዘች ሴት አመጡ፤ በሕዝቡም ፊት አቁመዋት፣ ኢየሱስን እንዲህ አሉት፤ “መምህር ሆይ፣ ይህች ሴት ስታመነዝር ተያዘች፤ ሙሴም፣ እንደዚች ያሉ ሴቶች በድንጋይ እንዲወገሩ በሕጉ አዞናል፤ አንተስ ምን ትላለህ?” ይህን ጥያቄ ያቀረቡለት፣ እርሱን የሚከሱበት ምክንያት ለማግኘት ሲፈትኑት ነው።

ኢየሱስ ግን ጎንበስ ብሎ በጣቱ በምድር ላይ ይጽፍ ጀመር። በጥያቄ ሲወተውቱት ቀና ብሎ፣ “ከእናንተ ኀጢአት የሌለበት እርሱ አስቀድሞ ድንጋይ ይወርውርባት” አላቸው። እንደ ገናም ጎንበስ ብሎ በምድር ላይ ጻፈ። ይህን እንደ ሰሙ፣ ከሽማግሌዎች ጀምሮ አንድ በአንድ ወጡ፤ ሴትዮዋም እዚያው ፊቱ እንደ ቆመች ኢየሱስ ብቻውን ቀረ። ኢየሱስም ቀና ብሎ፣ “አንቺ ሴት፣ ሰዎቹ የት ሄዱ? የፈረደብሽ የለምን?” አላት። እርሷም፣ “ጌታ ሆይ፤ አንድም የለም” አለች። ኢየሱስም፣ “እኔም አልፈርድብሽም፤ በይ ሂጂ፤ ከእንግዲህ ግን ኀጢአት አትሥሪ” አላት።

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

በዚህ አሁን በጀመርነው አምስተኛው የዐብይ ጾም ሳምንት ሰንበት ስርዓተ አምልኮ ላይ የተነበበው ቅዱስ ወንጌል ስታመነዝር የተገኘችሁን ሴት ሁኔታ ያቀርብልናል (ዩሐንስ 8፡1-11)። በዚህ ታሪክ ውስጥ ሁለት አስተሳሰቦች ይነጸባረቃሉ፦ በአንድ በኩል የኦሪት የሕግ መምህራንና የፈሪሳውያን አስተሳሰብ የሚገኝ ሲሆን በሌላል በኩል ደግሞ የኢየሱስ አስተሳሰብ ይገኛል። የመጀመርያዎቹ በሴቲቷ ላይ እንዲፈረድ ይፈልጋሉ፣ ምክንያቱም የሕግ አስከባሪ እንደ ሆኑና ለሕግ ታማኝ መሆናቸውን ለማሳየት ሕጉ ተፈጻሚ እንዲሆን ስለሚፈልጉ ነው። በምትኩ ግን ኢየሱስ ሊያድናት ፈለገ፣ ምክንያቱም እርሱ የእግዚኣብሔርን የመቤዠት እና የማስታረቅ ኃይል ተላብሶ ስለነበረ ነው።

ስለዚህ ክስተቱን እንመልከት። ኢየሱስ በቤተ መቅደስ ውስጥ እያስተማረ ሳለ ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን ስታመነዝር የተገኘችውን አንዲት ሴት ወደ እርሱ አመጡ፣ በመካከላቸውም አቁመዋት፣ ኢየሱስን እንዲህ አሉት፤ “መምህር ሆይ፣ ይህች ሴት ስታመነዝር ተያዘች፤ ሙሴም፣ እንደዚች ያሉ ሴቶች በድንጋይ እንዲወገሩ በሕጉ አዞናል” በማለት ይናገራሉ። “ይህን ጥያቄ ያቀረቡለት፣ እርሱን የሚከሱበት ምክንያት ለማግኘት ሲፈትኑት ነው” በማለት ወንጌላዊው ይህን ጥያቄ ያቀረቡበትን ምክንያት ግልጽ በሆነ መልኩ ያስቀምጣል። ዓላማቸው ይህ ነበር ተብሎ ሊታሰብ ይችላል-"አይሆንም ” ካለ ኢየሱስ ለሕግ ታዛዥ አይደለም ብለው ሊከሱት አስበው ነበር፣ በተቃራኒው ደግሞ "አዎን" ትወገር ብሎ ከመለሰ ደግሞ ሮማዊያንን ሳያስፈቅድ በሕዝቡ ተወዳጅ ለመሆን ፍልጎ ፍርዱን በራሱ ቃል አጽንቱዋል ብለው ሊከስቱ ፈልገው ነበር።

ኢየሱስን ለመክሰስ ያሰቡ እነዚህ ሰዎች ሕጋዊነትን እና ሕግ የማስከበር ታሪክን እንደ ሽፋን ተጠቅመው የእግዚኣብሔርን ልጅ በእነርሱ የፍርድ አሰጣጥ ሁኔታ እና ቅጣቱን ተፈጻሚ ማድረግ ይገባል በሚል አመለካከታቸው ውስጥ ሊይዙት ፈልገው ነበር። ነገር ግን እርሱ ወደ ዓለም የመጣው ፍርድ ለመስጠትና ለመቅጣት አልነበረም፣ ነገር ግን ሰዎችን ለማዳን እና ለሰዎች አዲስ ህይወት ለመስጠት ነው። ታዲያ በዚህ ረገድ ኢየሱስ የሰጠው መልስ ምን ነበር? በመጀመሪያ ደረጃ ለትንሽ ጊዜ ዝም ብሎ ቆየ፣ እርሱ ብቸኛው ሕግ እና የሕግ ዳኛ እግዚአብሔር መሆኑን ለማስታወስ ያህል በመሬት ላይ በጣቱ መጻፉን ቀጠለ። ከዚያን በኋላ ግን ከእናንተ ኀጢአት የሌለበት እርሱ አስቀድሞ ድንጋይ ይወርውርባት” (ዮሐንስ 8፡7) በማለት መለሰላቸው። በዚህ መንገድ ኢየሱስ እነዚያ ሰዎች ሕሊናቸውን ይመረምሩ ዘንድ አሳስቡኋቸዋል፡ እነርሱ እራሳቸውን "የፍትህ ደጋፊዎች" እንደሆኑ አድርገው ይቆጥሩ ነበር፣ ነገር ግን እነሱ እነርሱ ሰዎች በመሆናቸው የተነሳ በኃጢአት ሁኔታቸው ውስጥ እንደ ሚገኙ እንዲያውቁ በማድረግ፣ በዚህም መሰረት እነርሱ ራሳቸው ኃጢአተኞች በመሆናቸው የተነሳ በተመሳሳይ መልኩ የመኖር መብት እንደ ሌላቸው እና እነርሱም ቢሆኑ በተመሳሳይ መልኩ መሞት እንደ ሚገባቸው እዲገነዘቡ ያደርጋቸዋል። ይህን እንደ ሰሙ፣ ከሽማግሌዎች (ማለትም በራሳቸው ችግሮች ውስጥ የበለጠ ልምድ ያላቸው ናቸው) ከእነርሱ ጀምሮ አንድ በአንድ ሁሉም ሴቲቷን እርግፍ አድርገው ጥለው ከዚያ ወጡ። ይህ ትዕይንት እያንዳንዳችን ኃጢአተኞች መሆናችንን እንድንገነዘብ በማድረግ እንዲሁም እኛ በእጃችን ላይ ይዘን የምንገኘውን የውግዘት እና ልክ ስታመነዝር እንደ ተገኘችው ሴት ሌሎችን በማውገዝ በእነርሱ ላይ ለመወርወር ያሰብነውን የኩነኔ ድንጋይ ከእጃችን ላይ እንድናስወግድ ያስተምረናል።

በመጨረሻም በዚያ ስፍራ የቀሩት ኢየሱስ እና ሴቲቷ ብቻ ነበሩ፣ ይህንን ሁኔታ ቅዱስ አጎስጢኖስ ምሕረት እና አሳር” በማለት ገልጾት ነበር። ምንም ዓይነት ስህተት የሌለበት እና በእርሷ ላይ የመጀመርያውን ድንጋይ መወርወር ይችል የነበረው ኢየሱስ ብቻ ነው፣ ነገር ግን እርሱ ይህንን አላደረገም ነበር፣ ምክንያቱም ጌታ እግዚአብሔር በኃጢአተኞች ሞት አይደሰትም። ከክፉ መንገዳቸው ተመልሰው በሕይወት እንዲኖሩ ይፈልጋል” (ት. ኢዚቄል 33፡11)። እናም ኢየሱስ ይህችን ሴት እኔም አልፈርድብሽም፤ በይ ሂጂ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ግን ኀጢአት አትሥሪ” በማለት የሚገርም ቃል ተጠቅሞ ያሰናብታታል። በዚህ ሁኔታ ኢየሱስ በምህረት የተፈጠረ አዲስ መንገድ በፊቷ ይከፍታል፣ ይህም ከእዚያን በኋላ ኃጢአት ላለመፈጸም ቃል መግባት የሚጠይቅ አዲስ መንገድ ነው። እያንዳንዳችን የሚመለከት ግብዣ ነው። በዚህ ባለንበት የዐብይ ጾም ወቅት እያንዳንዳችን ኃጢአተኞች መሆናችንን እንድናውቅ እና ለሰራናቸው ኃጢአቶች ደግሞ ከእግዚኣብሔር ይቅርታ የምንጠይቅበት ወቅት ሊሆን ይገባል። ይቅርታ መጠየቃችን ደግሞ እኛን በማስታረቅ እና ሰላም በመስጠት የታደሰ አዲስ ታሪክ እንድንጀምር ያደርገናል። እያንዳንዱ እውነተኛ መለወጥ ለወደፊቱ አድስ ሕይወት፣ ነጻ ሕይወት፣ ከኃጢአት ነጻ የሆነ፣ እና በልግስና የተሞላ ውብ ሕይወት እንድንኖር ያደርገናል። በኢየሱስ በኩል ምሕረታዊ ፍቅሩን ያሳየን እግዚኣብሔር አዲስ የሆነ ሕይወት እንድንኖር እና ሁሌም አዲስ የሆነ እድል በመስጠት መኖር እንችል ዘንድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በአማላጅነቷ ትርዳን።

ምንጭ፡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በመጋቢት 29/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ካደረጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የተወሰደ

13 April 2019, 17:14