“ሰብዓዊ ወንድማማችነት” በሚል ሰነድ ላይ የመጀመሪያ ውይይት መካሄዱ ተገለጸ።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ትናንት መጋቢት 30 ቀን 2011 ዓ. ም. በሮም ከተማ በሚገኝ የግሬጎሪያን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ የሐይማኖቶች ጥናት ኢንስቲትዩት እና በሮም ከተማ ውስጥ የእስልምና እምነት ጥናት ማዕከል በጋራ ሆነው ባዘጋጁት ፎሬም ላይ “ሰብዓዊ ወንድማማችነት” በሚል ሠነድ ላይ ውይይት መደረጉ ታውቋል።
በተባበሩት አረብ ኤምረቶች፣ አቡዳቢ ከተማ ላይ ጥር 27 ቀን 2011 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና በግብጽ የአል አዛር ታላቁ ኢማም አህመድ አል ጣይብ “ሰብዓዊ ወንድማማችነት” የሚል ሰነድ አስድቀው ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ባልንጀራውን እንዲያግዝ እና እንዲወድ የሚያደርግ በምእመናን ልብ ውስጥ ያለ እምነት ነው በሚል መሪ ቃል በማሰማት ጉባኤው የተጀመረ ሲሆን “ሰብዓዊ ወንድማማችነት” ለዓለም ሰላም በጋራ አብሮ ለመኖር በሚለው ሰነድ ላይ ጥናታዊ ጽሑፋቸውን ያቀረቡት ምሁራን በሕብረት ሆነው ውይይት ማድረጋቸው ታውቋል። ትናንት ከሰዓት በኋላ በግሬጎሪያን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ የሐይማኖቶች ጥናት ኢንስቲትዩት ውስጥ በተካሄደው ጉባኤ ላይ የእስልምና እምነት ስነ መለኮታዊ ጥናት ምሁር የሆኑት አቶ አድናን ሞክራኒ፣ የሐይማኖቶች ጥናት ኢንስቲትዩት ዳይሬርክተር ክቡር አባ ሎሬንት ባሳነሰ እና ጉባኤውን የመሩት ክቡር አባ ቫለንቲኖ ኮቲኒ መገኘታቸው ይታወቃል።
መልካምን መመኘት የሁሉም ሰው መብት ነው፣
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና በግብጽ የአል አዛር ታላቁ ኢማም አህመድ አል ጣይብ በፊርማቸው ያጸደቁት የ“ሰብዓዊ ወንድማማችነት” ሰነድ ለክርስትና እና ለእስልምና እምነት ተከታዮች አዲስ አድማስን በመክፈት ለውይይት እንደሚጋብዝ፣ በተለይም የለውጥ አራማጅ፣ የነገ ተስፋ፣ የነጻነት፣ የዴሞክራሲ፣ የሰብዓዊ መብት እና የሙሉ ዜግነት ናፍቆት ያደረበት ወጣቱ ትውልድ መልካምን እንዲመኝ ሙሉ መብትን የሚሰጥ መሆኑን የእስልምና እምነት ስነ መለኮታዊ ጥናት ምሁር የሆኑት አቶ አድናን ሞክራኒ ገልጸዋል።
የጋራ ሃላፊነት ነው፣
ከአቶ አድናን ሞክራኒ ትንተና ለመረዳት እንደተቻለው የ“ሰብዓዊ ወንድማማችነት” ሰነድ እያንዳንዱን ፍጥረት የሚያሳትፍ እና የሚመለከት መሆኑ ታውቋል። ዓለማችን ሰዎች በጋራ ሆነው በእግዚአብሔር፣ በሰዎች እና በሞላው ፍጥረት ፊት ሆነው በሚሰጡት ሃላፊነት የሚመካ መሆኑ አቶ አድናን ሞክራኒ አስገንዝበዋል። በሰዎች መካከል ፍቅር እና መተጋገዝ የጎደለ እንደሆነ እምነትም ይዳከምና፣ በ“ሰብዓዊ ወንድማማችነት” ሰነድ ላይ እንደተገለጸው ተስፋን በማጨለም፣ የሰው ልጆች ሊያገኙ የሚመኙት ሙሉ እና ብሩሕ የወደ ፊት ሕይወት ጠፍቶ ይቀራል ብለዋል። የ“ሰብዓዊ ወንድማማችነት” ሰነድ ዓለማችን በበርካታ አመጾች እና ግጭቶች ውስጥ በምትገኝበት ወቅት የወጣ ሰነድ እንደሆነ፣ እነዚህ አመጾች እና ግጭቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ ጥረቶች በሚደረጉበት ወቅት የወጣ ሰነድ መሆኑን አቶ አድናን ገልጸዋል። ሁላችንም ተመሳሳይ ግብ ያለን እንደመሆናችን መጠን ሃላፊነታችንም የጋራ መሆኑን አቶ አድናን ሞክራኒ አስረድተዋል።
ነጻነት እና ብዝሕነት፣
በ“ሰብዓዊ ወንድማማችነት” ሰነድ ላይ በተደረገው የመጀመሪያ ዙር ውይይት ተገኝተው ሃሳባቸውን ያካፈሉት አቶ አድናን ሞክራኒ የሃይማኖት፣ የቀለም፣ የጾታ፣ የዘር እና የቋንቋ ብዝሐነት እና ልዩነቶች መለኮታዊ ጥበብ እና ምርጫ እንደሆነ አስረድተው፣ ይህንንም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጋቢት 25 ቀን 2011 ዓ. ም. ባቀረቡት ጠቅላላ የትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ወቅት መግለጻቸውን አስታውሰዋል። በሮም ከተማ በሚገኝ የግሬጎሪያን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሐይማኖቶች ጥናት ኢንስቲትዩት ዳይሬርክተር የሆኑት ክቡር አባ ሎሬንት ባሳነሴ በበኩላቸው የ“ሰብዓዊ ወንድማማችነት” ሰነድ በእምነት ነጻነት ላይ ስምምነት የተደረገበት የመጀመሪያ ሰነድ እንደሆነ አስታውሰዋል።
“ሰብዓዊ ወንድማማችነት” አዲስ ሰነድ ነው፣
ክቡር አባ ሎሬንት ባሳነሴ ባቀረቡት የጠቅላላ ሃሳባቸው፣ በተባበሩት አረብ ኤምረቶች፣ አቡዳቢ ከተማ ላይ ጥር 27 ቀን 2011 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና በግብጽ የአል አዛር ታላቁ ኢማም አህመድ አል ጣይብ የተፈራረሙት የ“ሰብዓዊ ወንድማማችነት” ሰነድ በይዘቱ የመጀመሪያ እንደሆነ ገልጸዋል። በማከልም “ሰብዓዊ ወንድማማችነት” የተሰኘ ሰነድ በሁለቱ የሐይማኖት ተቋማት ማለትም በክርስቲያን እና በሙስሊም እምነት መካከል መደረግ ስላለበት ውይይት ብቻ የሚናገር ሳይሆን በሕሎች መካከል፣ በሚያምኑት እና በማያምኑት መካከል፣ መልካም ፈቃድ ባላቸው ሰዎች መካከል ሊደረግ ስለሚገባው የጋራ ውይይት የሚናገር ሰነድ ነው ብለዋል።
የወዳጅነት ውይይት፣
ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ ጀምሮ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ ተሻግሮ እስከ ዛሬ ድረስ፣ ከመላው ዓለም ጋር ከተለያዩ ስልጣኔዎች እስከ በእውነት እና በቸርነት ላይ የቆመ የጋራ ውይይቶች ድረስ የወዳጅነት ውይይቶች እና ግንኙነቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን ክብር አባ ባሳነሴ አስታውሰው ከዚህ በፊት ይፋ የሆኑት ሰነዶች ለምሳሌ ኖስትራ ኤታቴ ሲተረጎም በእኛ እድሜ በሚለው እና ከእምነት የሚገኝ ደስታ በተሰኙት ሰነዶች ውስጥም ወንድማማችነትን፣ ደስታን እና ሐዘንን የተመለከቱ ሃሳቦች መገለጻቸውን አስታውሰዋል።